የሐዋርያት ሥራ 21
21
የጳውሎስ ጕዞ ወደ ኢየሩሳሌም
1ከእነርሱም ከተለየን በኋላ እኛ በመርከብ ተሳፍረን፥ መንገዳችንንም አቅንተን ወደ ቆስ መጣን፤ በበነጋውም ወደ ሮዶስ፥ ከዚያም ወደ ጳጥራ ገባን። 2ወደ ፊንቄም የሚያልፍ መርከብ አግኝተን በዚያ ላይ ተሳፍረን ሄድን። 3ቆጵሮስንም አየናት፤ በስተ ግራችንም ትተናት ወደ ሶርያ ሄድን፤ ወደ ጢሮስም ወረድን፤ በመርከብ ያለውን ጭነት ሁሉ በዚያ ያራግፉ ነበርና። 4በዚያም ደቀ መዛሙርትን አገኘንና በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ነገሩት። 5ከዚህም በኋላ ለመሄድ ወጣን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን። 6እርስ በርሳችንም ተሳስመን ተሰነባበትን፤ ከዚህም በኋላ ወደ መርከብ ወጣን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
7እኛም ከጢሮስ ወጥተን አካ#በግሪኩ “ጵቶሎማይስ” ይላል። ወደምትባል ሀገር መጣን፤ ወንድሞቻችንንም አግኝተን ሰላም አልናቸው፤ በእነርሱም ዘንድ አንድ ቀን አደርን። 8#የሐዋ. 6፥5፤ 8፥5። በማግሥቱም ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ ወደ ወንጌላዊው ወደ ፊልጶስ ቤትም ገባን፤ እርሱም ከሰባቱ ወንድሞች ዲያቆናት አንዱ ነው። 9ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። 10#11፥28። በእርሱም ዘንድ ብዙ ቀን ኖርን፤ ከይሁዳም አጋቦስ የሚባል አንድ ነቢይ ወረደ። 11ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ አንሥቶ እጁንና እግሩን በገዛ እጁ አስሮ እንዲህ አለ፥ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ የዚህን መታጠቂያ ጌታ አይሁድ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።” 12ይህንም ሰምተን የሀገሪቱን ሰዎች ይዘን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ጳውሎስን ማለድነው። 13ጳውሎስ ግን መልሶ፥ “ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? እያለቀሳችሁ ልቤን ትሰብሩታላችሁ፤ እኔ እኮ ተስፋ የማደርገው መከራንና እግር ብረትን ብቻ አይደለም፤ እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞትም ቢሆን የቈረጥሁ ነኝ” አለ። 14እንቢ ባለ ጊዜም ዝም አልን፤ እኛም እግዚአብሔር የፈቀደው ይሁን ብለን ተውነው። 15ከእነዚያም ቀኖች በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። 16ከደቀ መዛሙርትም ከቂሳርያ አብረውን የመጡ ነበሩ፤ ሄደንም ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ወገን ከሆነው በቆጵሮስ በሚኖረው በምናሶን ቤት አደርን።
17ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜም ወንድሞቻችን በደስታ ተቀበሉን። 18በማግሥቱም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ገባ፤ ቀሳውስትም ሁሉ በዚያ ነበሩ። 19ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ሐዋርያነት እግዚአብሔር በአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ ነገራቸው። 20እነርሱም ሰምተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ እንዲህም አሉ፥ “ወንድማችን ሆይ፥ ከአይሁድ መካከል ያመኑት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህን? ሁሉም ለኦሪት የሚቀኑ ናቸው። 21ነገር ግን የማይሆነውን እንደምታስተምር፥ የሙሴንም ሕግ እንደምታስተዋቸው፥ በአሕዛብ መካከል ያሉ ያመኑ አይሁድንም ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፥ የኦሪትንም ሕግ እንዳይፈጽሙ እንደምትከለክላቸው ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። 22አሁንሳ ምን ይሁን? ሕዝቡ ወደዚህ እንደ መጣህ ይሰሙና ይሰበሰቡ ይሆናል። 23ስለዚህም ይህን የምልህን አድርግ፦ ብፅዐት ያላቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። 24#ዘኍ. 6፥13-21። ይዘሃቸው ሂድ፤ ከእነርሱም ጋር ራስህን አንጻ፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ ስለ እነርሱ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ የሚያሙህም በሐሰት እንደ ሆነ፥ አንተም የኦሪትን ሕግ እንደምትጠብቅ ሁሉም ያውቃሉ። 25#የሐዋ. 15፥29። ስለሚአምኑት አሕዛብ ግን እርም ከሆነውና ለጣዖታት ከሚሠዉት፥ ከዝሙት፥ ሞቶ የተገኘውንና ደምን ከመብላት እንዲከለከሉ እኛ አዝዘናል።” 26ያንጊዜም ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር ነጻ። የመንጻታቸውንም ወራት መድረሱን ከነገራቸው በኋላ ሁሉም እየአንዳንዳቸው መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞአቸው ገባ።
ጳውሎስ ስለ መከሰሱ
27በሰባተኛውም ቀን ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በመቅደስ አዩት፤ ሕዝቡንም ሁሉ በእርሱ ላይ አነሳሥተው ያዙት። 28እየጮሁም እንዲህ አሉ፥ “እናንተ የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ ርዱን፤ በየስፍራው ሕዝባችንን፥ ኦሪትንም፥ ይህንም ስፍራ የሚቃወም ትምህርት ለሰው ሁሉ የሚያስተምር እነሆ፥ ይህ ሰው ነው፤ አሁንም አረማውያንን ወደ መቅደስ አስገባ፤ ቤተ መቅደስንም አረከሰ። 29#የሐዋ. 20፥4። የኤፌሶን ሀገር ሰው የሆነ ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና፤ ጳውሎስም ወደ ቤተ መቅደስ ያስገባው መስሎአቸው ነበርና። 30ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ ሄደው ጳውሎስን ጐትተው ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ በሩንም ሁሉ ዘጉ። 31ሊገድሉትም ፈልገው ብዙ ደበደቡት፤ ወዲያውም ኢየሩሳሌም በመላዋ እንደ ታወከች የሚገልጥ መልእክት ወደ ሻለቃው ደረሰለት። 32በዚያ ጊዜም ጭፍሮቹን ከአለቆቻቸው ጋር ይዞ ወደ እነርሱ ሄደ፤ እነርሱም የሻለቃውን ጭፍሮች ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታታቸውን ተዉ። 33የሻለቃውም ቀረብ ብሎ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር አዘዘ፤ “ምንድነው? ምንስ አደረገ?” ብሎም ጠየቀ። 34ሕዝቡም እኩሌቶቹ እንዲህ ነው፤ እኩሌቶቹም እንዲህ አይደለም እያሉ ይጮሁ ነበር፤ ሻለቃውም ሕዝቡ የሚታወክበትን ርግጡን ማወቅ ተሣነው፤ ወደ ወታደሮቹም ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ። 35ደረጃውንም በሚወጣበት ጊዜ ወታደሮች ተሸክመው አወጡት፤ ሰው ይጋፋ ነበርና። 36ብዙዎችም ይከተሉት ነበር፤ ሕዝቡም፥ “አስወግዱት” እያሉ ይጮሁ ነበር።
ጳውሎስ ስለ ራሱ እንደ ተከላከለ
37ወደ ሰፈርም በደረሰ ጊዜ ጳውሎስ ሻለቃውን፥ “ላነጋግርህ ትፈቅድልኛለህን?” አለው፤ ሻለቃውም፥ “የጽርዕ ቋንቋ ታውቃለህን?” አለው። 38“ምናልባት ከዚህ በፊት ወንጀል የሠራህና ከነፍሰ ገዳዮች አራት ሺህ ሰዎችን ይዘህ ወደ ምድረ በዳ የወጣህ ያ ግብፃዊ አንተ አይደለህምን?” አለው። 39ጳውሎስም፥ “እኔስ አይሁዳዊ ሰው ነኝ፤ የተወለድሁባትም ሀገር ጠርሴስ የታወቀች የቂልቅያ ከተማ ናት፤ ለሕዝቡም እንድነግራቸው ትፈቅድልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። 40በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ እጁን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ፤ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ ጳውሎስ በዕብራይስጥ ቋንቋ ተናገረ፤ እንዲህም አለ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 21: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ