የሐዋርያት ሥራ 25
25
ፊስጦስ ስለ መምጣቱና ስለ አይሁድ ልመና
1ፊስጦስም ወደ ቂሣርያ ደርሶ ሦስት ቀን ሰነበተ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። 2ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሎችም ከበቡት፤ የጳውሎስንም ነገር ነገሩት። 3ልኮም ወደ ኢየሩሳሌም አደባባይ እንዲያስመጣውና እንዲሰጣቸው ለመኑት፤ እነርሱ ግን ወደዚያ ሄደው በመንገድ ሸምቀው ሊገድሉት ፈልገው ነበር። 4ፊስጦስም ጳውሎስን በቂሣርያ እንደሚጠብቁት፥ እርሱም ራሱ ወደዚያው በቶሎ እንደሚሄድ መለሰላቸው። 5አይሁድንም፥ “ከመካከላችሁ የሚችሉ ካሉ ከከሰሳችሁት ከዚያ ሰው ጋር እንዲከራከሩ ከእኔ ጋር ይውረዱ” አላቸው።
6ስምንት ወይም ዐሥር ቀን በእነርሱ ዘንድ ከሰነበተ በኋላ ወደ ቂሣርያ ሄደ፤ በማግሥቱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ። 7ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ከኢየሩሳሌም የወረዱ አይሁድ ከብበውት ቆሙ፤ ሊረቱ በማይችሉበትም ብዙና ከባድ ክስ ከሰሱት። 8ጳውሎስም ሲመልስ፥ “በአይሁድ ሕግ ላይ ቢሆን፥ በቤተ መቅደስም ላይ ቢሆን፥ በቄሣር ላይም ቢሆን አንዳች የበደልሁት የለም” አለ። 9ፊስጦስ ግን አይሁድ እንዲያመሰግኑት ወዶ ጳውሎስን፥ “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ነገር በዚያ ከእኔ ዘንድ ልትከራከር ትሻለህን?” አለው። 10ጳውሎስም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እኔ ወደ ቄሣር ዙፋን ችሎት እቀርባለሁ፤ ፍርዴም በዚያ ሊታይልኝ ይገባል፤ በአይሁድም ላይ የበደልሁት በደል እንደሌለኝ ከሰው ሁሉ ይልቅ አንተ ራስህ ታውቃለህ። 11ከበደልሁ ወይም ለሞት የሚያበቃኝ የሠራሁት ክፉ ሥራ ካለ ሞት አይፈረድብኝ አልልም፤ ነገር ግን እነዚህ በደል የሌለብኝን በከንቱ የሚከስሱኝ ከሆነ፥ ለእነርሱ አሳልፎ ሊሰጠኝ ለማን ይቻለዋል? እኔ ወደ ቄሣር ይግባኝ ብያለሁ።” 12ከዚህም በኋላ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ፥ “ወደ ቄሣር ይግባኝ ካልህ ወደ ቄሣር ትሄዳለህ” አለው።
ጳውሎስ በአግሪጳና በበርኒቄ ፊት ስለ መቅረቡ
13ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት። 14በእርሱ ዘንድ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ ነገረው፤ እንዲህም አለው፥ “ፊልክስ በእስር ቤት ትቶት የሄደ አንድ እስረኛ ሰው በእዚህ አለ። 15በኢየሩሳሌም ሳለሁም ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች ወደ እኔ መጥተው እንድፈርድበት ማለዱኝ። 16እኔም፦ ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ሳይቆም፥ ለተከሰሰበትም ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፋንታ ሳያገኝ ማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሕግ አይደለም ብየ መለስሁላቸው። 17ከዚህም በኋላ፤ በዚሁ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳልዘገይ በማለዳ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ፥ ያን ሰው እንዲያመጡት አዘዝሁ። 18የከሰሱትም በቆሙ ጊዜ፥ እኔ እንደ አሰብሁት በከሰሱት ክስ የሠራው ምንም ነገር የለም። 19ስለ ሃይማኖታቸው ከሆነው ክርክርና ስለ ሞተው፥ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው ስለ ኢየሱስ ከሆነው ክርክር በቀር፤ 20ስለ ክርክራቸውም የማደርገውን አጥቼ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚያ ልትከራከር ትወዳለህን? አልሁት። 21ጳውሎስ ግን እንቢ ብሎ፥ እንዲድን ወደ ቄሣር ይግባኝ አለ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ቄሣር እስክልከው ድረስ እንዲጠብቁት አዘዝሁ።” 22አግሪጳም ፊስጦስን፥ “እኔም ያን ሰው ልሰማው እወዳለሁ” አለው፤ ፊስጦስም፥ “እንግዲያስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው።
23በማግሥቱም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጡ፤ ከመሳፍንቱና ከከተማው ታላላቅ ሰዎች ጋርም ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ። 24ፊስጦስም እንዲህ አለ፥ “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ወንድሞቻችን ሁላችሁ፥ ስሙ፤ አይሁድ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው በኢየሩሳሌምም ሆነ በዚህ እየጮሁ የለመኑኝ ይህ የምታዩት ሰው እነሆ። 25እኔ ግን ለሞት የሚያደርሰው በደል እንዳልሠራ እጅግ መርምሬ፥ እርሱም ራሱ ወደ ቄሣር ይግባኝ ማለትን ስለወደደ እንግዲህ ልልከው ቈርጫለሁ። 26ነገር ግን ስለ እርሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው የታወቀ ነገር የለኝም። ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን አገኝ ዘንድ ወደ እናንተ ይልቁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ ወደ አንተ አመጣሁት። 27የበደሉ ደብዳቤ ሳይኖር እስረኛን ወደ ንጉሥ መላክ አይገባምና፤ ለእኔም ነገሩም ሆነ አስሮ መላኩ አስቸግሮኛል።”#“ለእኔም ነገሩም ሆነ አስሮ መላኩ አስቸግሮኛል” የሚለው በግእዝ ብቻ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 25: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ