የሐዋርያት ሥራ 26
26
ጳውሎስ በአግሪጳ ፊት የተናገረው
1አግሪጳም ጳውሎስን፥ “ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ፈቅደንልሃል” አለው፤ ከዚህም በኋላ ጳውሎስ እጁን አነሣና ይነግራቸው ጀመር፤ እንዲህም አለ፦ 2“ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ አይሁድ እኔን ስለ ከሰሱበት ነገር ሁሉ ዛሬ በአንተ ዳኝነት እከራከር ዘንድ ስለ ተገባኝ ራሴን እንደ ተመሰገነ አድርጌ እቈጥረዋለሁ። 3የአይሁድን ጠባያቸውንና ክርክራቸውን አጥብቀህ ታውቃለህና ታግሠህ ታደምጠኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
4“ከልጅነቴ ጀምሮ በወገኖች መካከል በኢየሩሳሌም የኖርሁትን ኑሮ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ። 5#የሐዋ. 23፥6፤ ፊል. 3፥5። ሊመሰክሩም ከወደዱ እኔ ፈሪሳዊ ሆኜ በአባቶቻችን ሕግ እንደምኖር ከጥንት ጀምሮ እነርሱ ያውቁልኛል። 6አሁንም ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን የተሰጠውን ተስፋ በመታመን ከፍርድ በታች ቆሜአለሁ። 7ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን በመዓልትም በሌሊትም እርሱን እያገለገሉ ወደ እርስዋ ይደርሱ ዘንድ ተስፋ ያደርጋሉ፤ አይሁድም የሚከስሱኝ ስለዚህ ተስፋ ነው። 8እንዴትስ እግዚአብሔር ሙታንን እንደሚያስነሣቸው በእናንተ ዘንድ የማይታመን ሆኖ ይቈጠራል?
9“እኔም ብዙ ጊዜ በናዝሬቱ በኢየሱስ ስም ላይ ክፉ ነገር ላደርግ ቈርጬ ነበር። 10ይህንም በኢየሩሳሌም አደረግሁት፤ ከሊቃነ ካህናትም ሥልጣን ተቀብዬ ከቅዱሳን ብዙዎችን ወደ ወኅኒ ቤት አስገባኋቸው፤ ሲገድሏቸውም አብሬ እመክር ነበርሁ። 11#የሐዋ. 8፥3፤ 22፥4-5። በየምኵራቡ ሁሉ የማስገደጃ ማዘዣ አምጥቼ፥ በግድ የኢየሱስን ስም እንዲሰድቡ ዘወትር መከራ አጸናባቸው ነበር፤ ይልቁንም ወደ ሌሎች ከተማዎች እያሳደድሁ ከፋሁባቸው።
ጳውሎስ ወደ ክርስቶስ መመለሱን ስለ መናገሩ
12“ይህንም ለመፈጸም ከሊቃነ ካህናት ሥልጣን ተቀብዬ ወደ ደማስቆ ከተማ ሄድሁ። 13ንጉሥ ሆይ፥ እኩል ቀን በሆነ ጊዜ በመንገድ ስሄድ ከፀሐይ ይልቅ የሚበራ መብረቅ በእኔና ከእኔ ጋር ይሄዱ በነበሩት ላይ ከሰማይ ሲያንፀባርቅ አየሁ። 14ሁላችንም በምድር ላይ በወደቅን ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ፦ ‘ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ? በሾለ ብረት ላይ መርገጥ ለአንተ ይብስሃል’ የሚለኝን ቃል ሰማሁ። 15እኔም፦ ‘አቤቱ አንተ ማነህ?’ አልሁ፤ ጌታም አለኝ፦ ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። 16ነገር ግን ተነሣና በእግርህ ቁም፤ እኔን ባየህበትና ወደፊትም በምታይበት ነገር አገልጋይና ምስክር አድርጌ ልሾምህ ስለዚህ ተገልጬልሃለሁና። 17እኔም ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ። 18ይኸውም ዐይናቸውን ትከፍትላቸው ዘንድ፥ ከጨለማም ወደ ብርሃን፥ ሰይጣንን ከማምለክም#ግሪኩ “ለሰይጣን ከመገዛት” ይላል። ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸው ዘንድ፥ ኀጢአታቸውም ይሰረይላቸው ዘንድ፥ በስሜም በማመን ከቅዱሳን ጋር አንድነትን ያገኙ ዘንድ ነው።’
ጳውሎስ ስለሚያስተምረው ትምህርት
19“አሁንም ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከሰማይ የተገለጠልኝን ራእይ አልካድሁም። 20#የሐዋ. 9፥20፤28፤29። አስቀድሜ በኢየሩሳሌምና በደማስቆ ላሉት፥ ለይሁዳ አውራጃዎችም ሁሉ ነገርኋቸው፤ ለአሕዛብም ንስሓ ገብተው ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ፥ ለንስሓቸውም የሚገባ ሥራን ይሠሩ ዘንድ አስተማርኋቸው። 21ሰለዚህም ብቻ አይሁድ በመቅደስ ያዙኝ፤ ሊገድሉኝም ወደዱ። 22እግዚአብሔርም አዳነኝና ለታላቁም፥ ለታናሹም እየመሰከርሁ እስከ ዛሬ ደረስሁ፤ ይደረግ ዘንድ ካለው፥ ነቢያት ከተናገሩት፥ ሙሴም ከተናገረው ሌላ ያስተማርሁት የለም። 23#ኢሳ. 42፥6፤ 49፥6፤ 1ቆሮ. 15፥20። ክርስቶስ እንደሚሞት፥ ከሙታን ተለይቶም አስቀድሞ እንደሚነሣ፥ ለሕዝብና ለአሕዛብ ሁሉ፥ ለመላውም ዓለም እንደሚያበራ።”
24ይህንም ስለ ራሱ ሲናገር ሀገረ ገዢው ፊስጦስ መለሰ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ፥ “ጳውሎስ ሆይ፥ ልታብድ ነውን? ብዙ ትምህርት እኮ ልብን ይነሣል” አለው። 25ጳውሎስም እንዲህ አለው፥ “ክቡር ፊስጦስ ሆይ፥ እውነትና የተጣራ ነገርን እናገራለሁ እንጂ ዕብደትስ የለብኝም። 26በፊቱ ገልጬ የምናገርለት እርሱ ራሱ ንጉሥ አግሪጳ ያውቅልኛል፤ ከዚህም የሚሳተው ነገር ያለ አይመስለኝም፤ ወደ ጎን የተሰወረ አይደለምና። 27ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ እነሆ፥ በነቢያት ቃል ታምናለህን? እንደምታምንም አውቃለሁ።” 28አግሪጳም ጳውሎስን፥ “አሁንስ ወደ ክርስቲያንነት ልታገባኝ ጥቂት ብቻ ቀርቶሃል” አለው። 29ጳውሎስም፥ “በጥቂትም ቢሆን፥ በብዙም ቢሆን አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ደግሞ ከዚህ ከእስራቴ በቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ።”
የአግሪጳ ንግግር
30ከዚህም በኋላ ንጉሡ፥ ሀገረ ገዥውም፥ በርኒቄም፥ ሹሞቻቸውም ተነሡ። 31ለብቻቸውም ገለል ብለው እርስ በርሳቸው እንዲህ ብለው ተነጋገሩ፥ “ይህ ሰው እንዲሞት ወይም እንዲታሰር የሚያበቃ የሠራው በደል የለም።” 32አግሪጳም ፊስጦስን፥ “ወደ ቄሣር ይግባኝ ባይል ኖሮ ይህ ሰው ይፈታ ዘንድ በተገባ ነበር” አለው።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 26: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ