የሐዋርያት ሥራ 27
27
ጳውሎስ ወደ ሮም በመርከብ ስለ መሔዱ
1ከዚህም በኋላ ፊስጦስ ወደ ቄሣር ወደ ኢጣልያ በመርከብ እንሄድ ዘንድ ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስ ከሌሎች እስረኞች ጋር አብሮ የአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚባል የመቶ አለቃ ተሰጠ። 2በተነሣንም ጊዜ ወደ እስያ በምትሄድ በአድራማጢስ መርከብ ተሳፈርን፤ የተሰሎንቄ ሀገር ሰው የሚሆን መቄዶንያዊው አርስጥሮኮስም አብሮን ሄደ። 3በማግሥቱም ወደ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ አዘነለት፤ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና በእነርሱ ዘንድ እንዲያርፍም ፈቀደለት። 4ከዚያም ወጥተን ነፋስ ፊት ለፊት ነበርና በቆጵሮስ በኩል ዐለፍን። 5ወደ ኪልቅያና ወደ ጵንፍልያ ባሕርም ገብተን የሉቅያ ክፍል ወደምትሆነው ወደ ሙራ ሄድን። 6በዚያም የመቶ አለቃው ወደ ኢጣልያ የምትሄድ የእስክንድርያን መርከብ አገኘ፤ ወደ እርስዋም አስገባን። 7ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄድን፤ በጭንቅም ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ወደዚያም በቀጥታ ለመድረስ ነፋስ ቢከለክለን በቀርጤስ በኩል በሰልሙና ፊት ለፊት ዐለፍን። 8ባጠገብዋም በጭንቅ ስናልፍ ላሲያ ለምትባለው ከተማ አቅራቢያ ወደ ሆነችው መልካም ወደብ ወደምትባለው ቦታ ደረስን።
9በዚያም ብዙ ቀን ቈየን፤ የአይሁድም የጾም ወራት አልፎ ስለ ነበረ#ግእዙ “የአይሁድ ጾም እንዳለፈ ክረምቱ ስለሚገባ የባሕር ላይ ጕዞ አስቸጋሪ ነበር” ይላል። በመርከብ ለመሄድ የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ እንዲህ ብሎ መከራቸው። 10“እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ስሙኝ፤ ጕዞአችን በብዙ ጭንቀትና በከባድ ጥፋት ላይ ሆኖ አያለሁ፤ ይህንም የምለው ጥፋቱ በራሳችንም ሕይወት እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ ስላልሆነ ነው።” 11የመቶ አለቃው ግን ለመርከቡ ባለቤትና ለመሪው ይታዘዝ ነበር፤ የጳውሎስን ቃል ግን አይቀበልም ነበር። 12ያም ወደብ ክረምቱን ሊከርሙበት የማይመች ነበር፤ ስለዚህም ብዙዎች ከዚያ ይወጡ ዘንድ ይቻላቸው እንደ ሆነ በቀኝ በኩል ወደ አለው ፊንቄ ወደሚባለው ወደ ሁለተኛው የቀርጤስ ወደብ ይደርሱ ዘንድ ወደዱ።
ስለ ማዕበሉ ጽናት
13ልከኛ የአዜብ ነፋስም ነፈሰ፤ እነርሱም እንደ ወደዱ የሚደርሱ መስሎአቸው ነበር፤ መልሕቁንም አነሡ፤ በቀርጤስም አጠገብ ሄዱ። 14ከጥቂት ጊዜ በኋላም አውራቂስ#“አውራቂስ” በግእዝ “ሰልቢባ” ተብሎ ተተርጕሞአል። የሚሉት ጽኑዕ ዓውሎ ነፋስ መጣ። 15መርከባችንም ተመትታ ተነጠቀች፤ ቀዛፊዎችም በነፋሱ ፊት ለፊት መቆም አልተቻላቸውምና ተዉአት፤ ብቻዋንም ሄደች። 16ከዚህም በኋላ ቄዳ#ግሪኩ “ቀላሙዳ” ይላል። ወደምትባል ደሴት እስክንገባ ድረስ ነፋሱ ነፈሰ፤ በጭንቅም ታንኳችንን ለመግታት ቻልን። 17ከዚህ በኋላ ተጋግዘን በገመድ አጠናከርናት፤ ከዚህም ቀጥሎ ቀዛፊዎች ወደ ጥልቁ ባሕር እንዳይወድቁ በፈሩ ጊዜ ሸራውን አወረዱ፤እንዲሁም እንድንሄድ አደረግን። 18በማግሥቱም ማዕበል ጸናብን፤ ከጭነቱም ወደ ባሕር ጣልን። 19በሦስተኛውም ቀን በመርከብ ያለውን ሁሉ በእጃችን እያነሣን በባሕር ላይ ጣልን። 20ብዙ ቀንም ፀሐይንና ጨረቃን#“ጨረቃን” የሚለው በግሪኩ የለም። ከዋክብትንም ሳናይ ማዕበሉ ጸናብን፤ ለመዳንም ተስፋ ቈርጠን ነበር።
ጳውሎስ በመርከብ ላሉት ሰዎች ስለ ተናገረው ነገር
21ከእኛም መብል የበላ አልነበረም። ጳውሎስም ተነሥቶ በመካከል ቆመና እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ቀድሞ ቃሌን ሰምታችሁኝ ቢሆን ከቀርጤስም ባትወጡ ኖሮ ከዚህ ጕዳትና መከራ በዳናችሁ ነበር። 22አሁንም እላችኋለሁ፤ መርከባችን እንጂ ከመካከላችን አንድ ሰው ስንኳ አይጠፋምና አትፍሩ። 23እኔ ለእርሱ የምሆንና የማመልከው እግዚአብሔር የላከው መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና። 24እርሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ ከአንተም ጋር የሚሄዱትን ሁሉ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለአንተ ሰጥቶሃል።’ 25አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ እንደ ነገረኝ እንደሚሆን በእግዚአብሔር አምናለሁና። 26ነገር ግን ወደ አንዲት ደሴት እንደርሳለን።”
27በዐሥራ አራተኛውም ቀን በመንፈቀ ሌሊት በአድርያ ባሕር ስንጓዝ ቀዛፊዎች ወደ የብሱ የደረሱ መሰላቸው። 28መለኪያ ገመድ ጣሉ፤ በሰው ቁመትም ሃያ አገኙ፤ ከዚያም ጥቂት ፈቀቅ ብለው ዳግመኛ ጣሉ፤ በሰው ቁመትም ዐሥራ አምስት አገኙ። 29ድንጋያማ በሆነ ቦታም እንዳይወድቁ ፈሩ፤ ስለዚህም ከመርከቡ በስተኋላ አራት መልሕቅ በባሕሩ ላይ ጣሉ፤ ፈጥኖ እንዲነጋም ጸለዩ። 30ከዚህ በኋላም ቀዛፊዎቹ ከመርከብ ሊኮበልሉ በወደዱ ጊዜ ወደ ኋላ ሊመለሱ ከምድር ላይ ሆነው መርከባቸውን የሚያጠናክሩ መስለው ጀልባቸውን ወደ ባሕር አወረዱ። 31ጳውሎስም ይህን ባየ ጊዜ ለመቶ አለቃውና ለወታደሮቹ፥ “እነዚህ ቀዛፊዎች በመርከብ ውስጥ ከሌሉ መዳን አትችሉም” አላቸው። 32ወታደሮችም ወዲያውኑ ተነሥተው የታንኳዪቱን ገመድ ቈርጠው ትወድቅ ዘንድ ተዉአት።
33ሊነጋም በጀመረ ጊዜ ጳውሎስ እህል እንዲበሉ ሁሉንም ማለዳቸው፤ እንዲህም አላቸው፥ “እህል ከተዋችሁ ዛሬ ዐሥራ አራት ቀን ነው። 34አሁንም እሺ በሉኝና ምግብ ብሉ፤ ራሳችሁንም አድኑ፥ ከእናንተ ከአንዱ የራስ ጠጕር እንኳ አትጠፋምና።” 35ይህንም ተናግሮ ኅብስቱን አንሥቶ በሁሉም ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ቈርሶም ይበላ ዘንድ ጀመረ። 36ሁሉም ተጽናኑ፤ እህልም ቀመሱ። 37በመርከቡ ውስጥ የነበሩትም ቍጥራቸው ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ነፍስ ነበር። 38በልተውም በጠገቡ ጊዜ በመርከቡ ውስጥ የነበረውን ስንዴ ወደ ባሕር ጣሉት፤ መርከቡንም አቃለሉ።
39በነጋ ጊዜም ቀዛፊዎች ቦታውን አልለዩም፤ የሚሄዱበትንም አላወቁም፤ ነገር ግን ለባሕሩ አቅራቢያ የሆነውን የደሴት ተራሮች አዩ፤ መርከባቸውንም ወደ እዚያ ሊያስጠጉ ፈለጉ። 40መልሕቁንም ፈትተው በባሕር ላይ ጣሉት፤ የሚያቆሙበትንም አመቻችተው እንደ ነፋሱ አነፋፈስ መጠን ትንሹን ሸራ ሰቀሉ፤ ወደ ባሕሩ ዳርቻም ሄድን። 41መርከቢቱም በሁለት ታላላቅ ድንጋዮች መካከል ተቀረቀረች፤ ባሕሩም ጥልቅ ነበረ። ከወደፊቷም ተያዘች፤ አልተንቀሳቀሰችምም፤ ከሞገዱም የተነሣ በስተኋላ በኩል ጎንዋን ተሰብራ ተጐረደች፤ ቀዛፊዎችም ወደፊት ሊገፉአት አልቻሉም።#“ቀዛፊዎችም ወደፊት ሊገፉአት አልቻሉም” የሚለው በግሪኩ የለም። 42ወታደሮቹም ዋኝተው እንዳያመልጡ እስረኞችን ለመግደል ተማከሩ። 43የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ሊያድነው ወድዶአልና ምክራቸውን እንቢ አለ፤ ዋና የሚያውቁትንም ዋኝተው ወደ ምድር እንዲወጡ አዘዛቸው። 44የቀሩትም በመርከቡ ስብርባሪ ዕንጨትና በሳንቃው ላይ ተሻገሩ፤ ሌሎችም በመርከቡ ገመድ ላይ እየተንጠላጠሉ ተሻገሩ፤ ሁሉም እንዲህ ባለ ሁኔታ በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 27: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ