የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትን​ቢተ ዳን​ኤል 4

4
የና​ቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር ሁለ​ተ​ኛው ሕልም
1ከን​ጉሡ ከና​ቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር፤ በም​ድር ሁሉ ወደ​ሚ​ቀ​መጡ ወገ​ኖ​ችና አሕ​ዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋን​ቋም ወደ​ሚ​ና​ገሩ ሁሉ፥ “ሰላም ይብ​ዛ​ላ​ችሁ። 2ልዑል አም​ላክ በፊቴ ያደ​ረ​ገ​ውን ተአ​ም​ራ​ቱ​ንና ድን​ቁን እነ​ግ​ራ​ችሁ ዘንድ ወደ​ድሁ። 3ተአ​ም​ራቱ እን​ዴት ታላቅ ነው! ድን​ቁም እን​ዴት ጽኑ ነው! መን​ግ​ሥ​ቱም የዘ​ለ​ዓ​ለም መን​ግ​ሥት ነው፤ ግዛ​ቱም ለልጅ ልጅ ነው።#ምዕ. 4 ከቍ. 1 እስከ 4 ያለው በግ​ሪክ ሰባ. ሊ. የምዕ. 3 መጨ​ረ​ሻ​ዎች ናቸው።
4“እኔ ናቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአ​ዳ​ራ​ሼም ተመ​ች​ቶኝ ነበር። 5ሕልም አለ​ምሁ፤ እር​ስ​ዋም አስ​ፈ​ራ​ችኝ፤ በአ​ል​ጋ​ዬም ላይ ታወ​ክሁ፤ የራ​ሴም ራእይ አስ​ጨ​ነ​ቀኝ። 6ስለ​ዚህ የሕ​ል​ሜን ፍቺ እን​ዲ​ያ​ስ​ታ​ው​ቁኝ የባ​ቢ​ሎን ጠቢ​ባን ሁሉ ወደ እኔ ይገቡ ዘንድ አዘ​ዝሁ። 7የዚ​ያን ጊዜም የሕ​ልም ተር​ጓ​ሚ​ዎ​ቹና አስ​ማ​ተ​ኞቹ፥ ከለ​ዳ​ው​ያ​ኑና ቃላ​ተ​ኞቹ ገቡ፤ ሕል​ሜ​ንም በፊ​ታ​ቸው ተና​ገ​ርሁ፤ ፍቺ​ውን ግን አላ​ስ​ታ​ወ​ቁ​ኝም። 8በመ​ጨ​ረ​ሻም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቅዱስ መን​ፈስ ያለ​በት እንደ አም​ላኬ ስም ብል​ጣ​ሶር የሚ​ባ​ለው ዳን​ኤል በፊቴ ገባ፤ እኔም እን​ዲህ አል​ሁት፦ 9የጠ​ቢ​ባን አለቃ ብል​ጣ​ሶር ሆይ! የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቅዱስ መን​ፈስ በአ​ንተ ውስጥ እንደ አለ፥ ከም​ሥ​ጢ​ርም ሁሉ የሚ​ያ​ስ​ቸ​ግ​ርህ እን​ደ​ሌለ ዐው​ቄ​አ​ለ​ሁና ያየ​ሁ​ትን የሕ​ል​ሜን ራእይ፥ ፍቺ​ው​ንም ንገ​ረኝ። 10በአ​ል​ጋዬ ላይ ራእይ አየሁ፤ እነሆ በም​ድር መካ​ከል ዛፍ ነበረ፤ ቁመ​ቱም እጅግ ረዥም ነበረ። 11ዛፉም ትልቅ ሆነ፤ በረ​ታም፤ ቁመ​ቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ቅር​ን​ጫ​ፉም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ደረሰ። 12ቅጠ​ሎ​ቹም የተ​ዋቡ ነበሩ፤ ፍሬ​ውም ብዙ ነበረ፤ ሁሉም ከእ​ርሱ ይመ​ገብ ነበረ፤ ከጥ​ላ​ውም በታች የዱር አራ​ዊት ያር​ፉ​በት ነበር፥ በቅ​ር​ን​ጫ​ፎ​ቹም ውስጥ የሰ​ማይ ወፎች ይቀ​መጡ ነበር፤ ሥጋ ለባ​ሹም ሁሉ ከእ​ርሱ ይበላ ነበር።
13“በአ​ል​ጋ​ዬም ላይ በሌ​ሊት ራእይ አየሁ፤ እነ​ሆም አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰ​ማይ ወረደ። 14በታ​ላቅ ድም​ፅም እየ​ጮኸ እን​ዲህ አለ፦ ዛፉን ቍረጡ፤ ቅር​ን​ጫ​ፎ​ቹ​ንም ጨፍ​ጭፉ፤ ቅጠ​ሎ​ቹ​ንም አራ​ግፉ፤ ፍሬ​ው​ንም በትኑ፤ አራ​ዊ​ቱም ከበ​ታቹ፥ ወፎ​ቹም ከቅ​ር​ን​ጫፉ ይታ​ወኩ። 15ነገር ግን ሥሩ​ንና ጉቶ​ውን በም​ድር ውስጥ ተዉት፤ በመ​ስ​ክም ውስጥ በብ​ረ​ትና በናስ ማሰ​ሪያ ታስሮ ይቈይ፤ በሰ​ማ​ይም ጠል ይረ​ስ​ርስ፤ እድል ፋን​ታ​ውም በም​ድር ሣር ውስጥ ከአ​ራ​ዊት ጋር ይሁን። 16ልቡም ከሰው ልብ ይለ​ወጥ፤ የአ​ው​ሬም ልብ ይሰ​ጠው፤ ሰባት ዘመ​ና​ትም ይለ​ፉ​በት። 17ልዑል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የሰ​ዎ​ችን መን​ግ​ሥት እን​ዲ​ገዛ፥ ለወ​ደ​ደ​ውም እን​ዲ​ሰ​ጠው፥ ሕያ​ዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠ​ባ​ቂ​ዎች ትእ​ዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅ​ዱ​ሳን ቃል ነው፤ ሰው​ንም ትዕ​ቢቱ ያዋ​ር​ደ​ዋል። 18እኔ ንጉሡ ናቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር ያለ​ም​ሁት ሕልም ይህ ነው፤ አን​ተም ብል​ጣ​ሶር! ፍቺ​ውን ንገ​ረኝ፤ የመ​ን​ግ​ሥቴ ጠቢ​ባን ሁሉ ፍቺ​ውን ይነ​ግ​ሩኝ ዘንድ አል​ቻ​ሉ​ምና፤ ነገር ግን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቅዱስ መን​ፈስ በአ​ንተ ውስጥ አለና አንተ ትች​ላ​ለህ።”
ዳን​ኤል የን​ጉ​ሡን ሕልም እንደ ተረ​ጐመ
19ያን ጊዜም ብል​ጣ​ሶር የተ​ባ​ለው ዳን​ኤል አንድ ሰዓት ያህል ዐሰበ፤ ልቡም ታወከ። ንጉ​ሡም መልሶ፥ “ብል​ጣ​ሶር ሆይ! ሕል​ሙና ፍቺው አያ​ስ​ቸ​ግ​ርህ” አለው።#“ንጉ​ሡም መልሶ ብል​ጣ​ሶር ሆይ ሕል​ሙና ፍቺው አያ​ስ​ቸ​ግ​ርህ አለው” የሚ​ለው በዕብ. ብቻ። ብል​ጣ​ሶ​ርም መልሶ አለ፥ “ጌታዬ ሆይ! ሕልሙ ለሚ​ጠ​ሉህ፥ ፍቺ​ውም ለጠ​ላ​ቶ​ችህ ይሁን። 20ትልቅ የነ​በ​ረው፥ የበ​ረ​ታ​ውም፥ ቁመ​ቱም እስከ ሰማይ የደ​ረ​ሰው፥ ቅር​ን​ጫ​ፉም እስከ ምድር ሁሉ ድረስ የታ​የው፥ 21ቅጠ​ሉም አምሮ የነ​በ​ረው፤ ፍሬ​ውም የበ​ዛው፥ ለሁ​ሉም መብል የነ​በ​ረ​በት፥ በበ​ታ​ቹም የም​ድር አራ​ዊት የተ​ቀ​መጡ፥ በቅ​ር​ን​ጫ​ፎ​ቹም የሰ​ማይ ወፎች ያደ​ሩ​በት፥ ያየ​ኸው ዛፍ፥ 22ንጉሥ ሆይ! እርሱ ታላ​ቅና ብርቱ የሆ​ንህ አንተ ነህ፤ ታላ​ቅ​ነ​ትህ በዝ​ቶ​አል፤ እስከ ሰማ​ይም ደር​ሶ​አል፤ ግዛ​ት​ህም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው። 23ንጉ​ሡም ከሰ​ማይ የወ​ረ​ደ​ው​ንና፦ ዛፉን ቍረጡ፥ አጥ​ፉ​ትም፤ ነገር ግን ጉቶ​ውን በም​ድር ውስጥ ተዉት፤ በብ​ረ​ትና በናስ ማሰ​ሪያ ታስሮ በመ​ስክ ውስጥ ይቈይ፤ በሰ​ማ​ይም ጠል ይረ​ስ​ርስ፥ ሰባት ዘመ​ና​ትም እስ​ኪ​ያ​ል​ፉ​በት ድረስ እድል ፋን​ታው ከም​ድር አራ​ዊት ጋር ይሁን ያለ​ውን ቅዱስ ጠባቂ ማየቱ፥ 24ንጉሥ ሆይ! ፍቺው ይህ ነው፤ በጌ​ታዬ በን​ጉሥ ላይ የወ​ረ​ደው የል​ዑሉ ትእ​ዛዝ ነው፤ 25ልዑ​ሉም የሰ​ዎ​ችን መን​ግ​ሥት እን​ዲ​ገዛ፥ ለሚ​ወ​ድ​ደ​ውም እን​ዲ​ሰ​ጠው እስ​ክ​ታ​ውቅ ድረስ ከሰ​ዎች ተለ​ይ​ተህ ትሰ​ደ​ዳ​ለህ፤ መኖ​ሪ​ያ​ህም ከም​ድር አራ​ዊት ጋር ይሆ​ናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበ​ላ​ለህ፤ በሰ​ማ​ይም ጠል ትረ​ሰ​ር​ሳ​ለህ፤ ሰባት ዘመ​ና​ትም ያል​ፉ​ብ​ሃል። 26የዛ​ፉ​ንም ጉቶ ተዉት ማለቱ፥ ሥል​ጣን ከሰ​ማ​ያት እንደ ሆነ እስ​ክ​ታ​ውቅ ድረስ መን​ግ​ሥ​ትህ ይቈ​ይ​ል​ሃል። 27ንጉሥ ሆይ! ስለ​ዚህ ምና​ል​ባት የደ​ኅ​ን​ነ​ትህ ዘመን ይረ​ዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰ​ኝህ፤ በጽ​ድ​ቅና በም​ጽ​ዋት ትድ​ና​ለህ፤ በደ​ል​ህ​ንና ኀጢ​አ​ት​ህ​ንም ለድ​ሆች በመ​ራ​ራት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይቅር ይል​ሃል።”
ሕልሙ እንደ ደረሰ
28ይህ ሁሉ በን​ጉሡ በና​ቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር ላይ ደረሰ። 29ከዐ​ሥራ ሁለት ወር በኋ​ላም በባ​ቢ​ሎን ቤተ መን​ግ​ሥት ሰገ​ነት ላይ ሲመ​ላ​ለስ፤ 30ንጉሡ፥ “ይህች እኔ በጕ​ል​በቴ ብር​ታት ለግ​ር​ማዬ ክብር የመ​ን​ግ​ሥት መኖ​ሪያ እን​ድ​ት​ሆን ያሠ​ራ​ኋት ታላ​ቂቱ ባቢ​ሎን አይ​ደ​ለ​ች​ምን?” ብሎ ተና​ገረ። 31ቃሉም ገና በን​ጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰ​ማይ መጣና፥ “ንጉሥ ናቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር ሆይ! መን​ግ​ሥት ከአ​ንተ ዘንድ ዐለ​ፈች ተብሎ ለአ​ንተ ተነ​ግ​ሮ​አል፤ 32ልዑ​ሉም የሰ​ዎ​ችን መን​ግ​ሥት እን​ዲ​ገዛ፥ ለሚ​ወ​ድ​ደ​ውም እን​ዲ​ሰ​ጠው እስ​ክ​ታ​ውቅ ድረስ ከሰ​ዎች ተለ​ይ​ተህ ትሰ​ደ​ዳ​ለህ፤ መኖ​ሪ​ያ​ህም ከም​ድር አራ​ዊት ጋር ይሆ​ናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበ​ላ​ለህ፤#ዕብ. “ትበላ ዘንድ ትገ​ደ​ዳ​ለህ” ይላል። ሰባት ዘመ​ና​ትም ያል​ፉ​ብ​ሃል” አለው። 33በዚ​ያም ሰዓት ነገሩ በና​ቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕ​ሩም እንደ አን​በሳ፥ ጥፍ​ሩም እንደ ንስር እስ​ኪ​ረ​ዝም ድረስ ከሰ​ዎች ተለ​ይቶ ተሰ​ደደ፤ እንደ በሬም ሣር በላ፤ አካ​ሉም በሰ​ማይ ጠል ረሰ​ረሰ።
34ከእ​ነ​ዚ​ያም ዘመ​ናት በኋላ እኔ ናቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር ዐይ​ኔን ወደ ሰማይ አነ​ሣሁ፤ አእ​ም​ሮ​ዬም ተመ​ለ​ሰ​ልኝ፤ ልዑ​ሉ​ንም ባረ​ክሁ፤ ለዘ​ለ​ዓ​ለም የሚ​ኖ​ረ​ው​ንም አመ​ሰ​ገ​ንሁ፤ አከ​በ​ር​ሁ​ትም፤ ግዛቱ የዘ​ለ​ዓ​ለም ግዛት ነውና፥ መን​ግ​ሥ​ቱም ለልጅ ልጅ ነውና። 35በም​ድ​ርም የሚ​ኖሩ ሁሉ እንደ ኢም​ንት ይቈ​ጠ​ራሉ፤ በሰ​ማ​ይም ሠራ​ዊት በም​ድ​ርም ላይ በሚ​ኖሩ መካ​ከል እንደ ፈቃዱ ያደ​ር​ጋል፤ እጁ​ንም የሚ​ቃ​ወ​ማት ወይም፥ “ምን ታደ​ር​ጋ​ለህ?” የሚ​ለው የለም። 36በዚ​ያን ጊዜም አእ​ም​ሮዬ ተመ​ለ​ሰ​ልኝ፤ ወደ መን​ግ​ሥ​ቴም ክብር መጣሁ፤ ግር​ማ​ዬና ውበ​ቴም ወደ እኔ ተመ​ለሰ፤ አማ​ካ​ሪ​ዎ​ችና መኳ​ን​ን​ቶ​ችም ፈለ​ጉኝ፤ በመ​ን​ግ​ሥ​ቴም ውስጥ ጸናሁ፤ ብዙም ክብር ተጨ​መ​ረ​ልኝ። 37አሁ​ንም እኔ ናቡ​ከ​ደ​ነ​ፆር የሰ​ማ​ይን ንጉሥ አመ​ሰ​ግ​ነ​ዋ​ለሁ፤ ከፍ ከፍም አደ​ር​ገ​ዋ​ለሁ፥ አከ​ብ​ረ​ው​ማ​ለሁ። ሥራው ሁሉ እው​ነት፥ መን​ገ​ዱም ቀና ነውና፤ በት​ዕ​ቢ​ትም የሚ​ሄ​ዱ​ትን ያዋ​ርድ ዘንድ ይች​ላ​ልና።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ