ትንቢተ ዳንኤል 7
7
ስለ 4 አራዊት ራእይ
1በባቢሎን ንጉሥ በብልጣሶር በመጀመሪያው ዓመተ መንግሥት ዳንኤል በአልጋው ላይ ሕልምንና የራሱን ራእይ አየ፤ ከዚያም በኋላ ሕልሙን ጻፈ፥ 2እንዲህም አለ፥ “እኔ ዳንኤል ራእይ አየሁ፤ እነሆም አራቱ የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ይነፍሱ ነበር። 3አራትም ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ፥ እያንዳንዲቱም ከሌላይቱ ልዩ ነበረች። 4መጀመሪያይቱ እንደ ሴት አንበሳ ነበረች፤ እንደ ንስርም ክንፍ ነበራት፤ ክንፎችዋም ከእርስዋ እስኪነቀሉ ድረስ አይ ነበር፤ ከምድርም ከፍ ከፍ አለች፤ እንደ ሰውም በእግር ቆመች፤ የሰውም ልብ ተሰጣት። 5እነሆም ሁለተኛይቱ ድብ የምትመስል ሌላ አውሬ ነበረች፤ በአንድ ወገንም ቆመች፤ ሦስትም የጎድን አጥንቶች በአፍዋ ውስጥ በጥርሶችዋ መካከል ነበሩ፤ እንደዚህም፦ ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ አሏት። 6ከዚህም በኋላ፥ እነሆ ነብር የምትመስል፥ በጀርባዋም ላይ አራት የወፍ ክንፎች የነበሩአት፤ ሌላ አውሬ አየሁ፤ ለአውሬይቱም አራት ራሶች ነበሩአት፤ ሥልጣንም ተሰጣት። 7ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም የምታስፈራና የምታስደነግጥ፥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ ዐሥር ቀንዶችም ነበሩአት። 8ቀንዶችንም ተመለከትሁ፤ እነሆም፤ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፤ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ፤ እነሆም በዚያ በትንሹ ቀንድ እንደ ሰው ዐይኖች የነበሩ ዐይኖች፥ በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት።
9“ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፤ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ነጭ ሱፍ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። 10የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፤ ሺህ ጊዜ ሺህ የሆኑ ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ለፍርድም ተቀመጠ፤ መጻሕፍትንም ገለጠ። 11የዚያን ጊዜም ይህ ቀንድ ከተናገረው ነገር የተነሣ አውሬው እስኪርቅና እስኪጠፋ ድረስ አየሁ፤ በእሳትም ያቃጥሉት ዘንድ ሰውነቱን አሳልፈው ሰጡት፤ 12ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፤ የሕይወታቸው ዘመን ግን እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ረዘመ።
13“በሌሊትም ራእይ አየሁ፤ እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል በሰማይ ደመና መጣ፤ በዘመናትም ወደ ሸመገለው ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። 14ወገኖችና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር፥ መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።
የሕልሙ ፍች
15“እኔም ዳንኤል መንፈሴ ተንቀጠቀጠብኝ፤ ከራሴም ራእይ የተነሣ ልቤ ደነገጠብኝ። 16በዚያም ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ ስለዚህ ሁሉ እውነቱን ጠየቅሁት፤ እርሱም ነገረኝ፤ የነገሩንም ፍቺ አስታወቀኝ፥ እኔም ነገሩን ተረዳሁት። 17እንዲህም አለኝ፦ እነዚህ ያየሃቸው አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ አራት ነገሥታት ናቸው፤ ዳግመኛም ይወገዳሉ። 18ነገር ግን መንግሥት ለልዑሉ ቅዱሳን ይመለሳል፤ የልዑሉ ቅዱሳንም መንግሥቱን ይወስዳሉ፤ እስከ ዘለዓለም ዓለምም መንግሥቱን ይወርሳሉ። 19ከዚህም በኋላ ከቀሩት ሁሉ ተለይታ እጅግ ስለምታስፈራው፥ ጥርሶችዋም የብረት፥ ጥፍሮችዋም የናስ ስለ ሆኑት፥ ስለምትበላውና ስለምታደቅቀው፥ የቀረውንም በእግርዋ ስለምትረግጠው ስለ አራተኛዪቱ አውሬ፥ 20በራስዋም ላይ ስለ ነበሩ ስለ ዐሥር ቀንዶች፥ በኋላም ስለ ወጣው፥ በፊቱም ስለ ወደቁ ሦስቱ ቀንዶች፥ ዐይኖችና ትዕቢት የተናገረ አፍ ስለ ነበሩት ራሱም ከሌሎች ስለ በለጠ ስለ ሌላው ቀንድ እውነቱን ለማወቅ ጠየቅሁት። 21እነሆም፥ ያ ቀንድ ከቅዱሳን ጋር ሲዋጋ አየሁ፤ አሸነፋቸውም፤ 22በዘመናት የሸመገለው እስኪመጣ ድረስ፥ ፍርድም ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪሰጥ ድረስ፥ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወስዱበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ አሸነፋቸው።
23“እንዲህም አለኝ፦ አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሣ አራተኛ መንግሥት ነው፤ እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ ይበልጣል።#ዕብ. “የተለየ ይሆናል” ይላል። ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፤ ይረግጣታል፤ ያደቅቃትማል። 24ዐሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነርሱም በኋላ ሌላ ይነሣል፤ እርሱም ከፊተኞቹ በክፋት የበለጠ#ዕብ. “የተለየ” ይላል። ይሆናል፤ ሦስቱንም ነገሥታት ያዋርዳል። 25በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፤ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፤ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኩሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ። 26ነገር ግን ፍርድ ይሆናል፤ እስከ ፍጻሜውም ድረስ ያፈርሱትና ያጠፉት ዘንድ ግዛቱን ያስወግዱታል። 27መንግሥትም፥ ግዛትም፥ ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘለዓለም መንግሥት ነው፤ መኳንንቱም ሁሉ ይገዙለታል፤ ይታዘዙለትማል።” 28የነገሩም ፍጻሜ እስከዚህ ድረስ ነው። እኔም ዳንኤል በአሳቤ እጅግ ተቸገርሁ፤ ፊቴም ተለወጠብኝ፤ ዳሩ ግን ነገሩን በልቤ ጠብቄአለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 7: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ