ኦሪት ዘዳግም 1
1
እስራኤላውያን ሲናን ለቅቀው እንዲጓዙ የተሰጠ ትእዛዝ
1በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በምዕራብ በኩል በኤርትራ ባሕር አጠገብ በፋራንና በጦፌል፥ በላባንና በአውሎን፥ በካታኪሪሲያም#ካታኪሪሲያ “የወርቅ ቦታ” ማለት ነው። መካከል፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ፥ የነገራቸው ቃላት እኒህ ናቸው። 2በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የዐሥራ አንድ ቀን ጕዞ ነው። 3በአርባኛው ዓመት በዐሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ሙሴ እንዲነግራቸው እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው፤ 4በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞሬዎናውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስጣሮትና በኤድራይን ተቀምጦ የነበረውንም የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከገደሉት በኋላ፥ 5በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህን ሕግ ይገልጥ ጀመር፦
6“አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን፦ በዚህ ተራራ መቀመጣችሁ በቃ፤ 7ተመልሳችሁ ተጓዙ፤ ወደ አሞራውያን ተራራ፥ ወደ አረባም ሀገሮች ሁሉ፥ በተራራውም፥ በሜዳውም፥ በሊባም፥ በባሕርም ዳር ወዳሉ ወደ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም ፊት ለፊት እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ። 8እነሆ፥ ምድሪቱን ሰጠኋችሁ፤ ግቡ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ፥ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ምድር ውረሱ።
ሙሴ የሕዝብ አለቆችን መሾሙ
(ዘፀ. 18፥13-27)
9“በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ ተናገርኋችሁ፦ እኔ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤ 10አምላካችሁ እግዚአብሔር አብዝቶአችኋልና፥ እነሆም፥ እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዙዎች ናችሁ። 11የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በዚህ ቍጥር ላይ እልፍ አእላፋት ይጨምር፤ እንደ ተናገራችሁም ይባርካችሁ። 12እኔ ብቻዬን ድካማችሁን፥ ሸክማችሁንም፥ ክርክራችሁንም እሸከም ዘንድ እንዴት እችላለሁ? 13ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች፥ አስተዋዮችም፥ ዐዋቂዎችም የሆኑትን ሰዎች አምጡ፤ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ። 14እናንተም፦ ‘እናደርገው ዘንድ የተናገርኸው ይህ ነገር መልካም ነው’ ብላችሁ መልሳችሁ ነገራችሁኝ። 15ከእናንተም ጥበበኞችና ዐዋቂዎች፥ አስተዋዮችም የሆኑትን ሰዎች ወሰድሁ፤ በእናንተም ላይ አለቆች፥ የሻለቆችም፥ የመቶ አለቆችም፥ የአምሳ አለቆችም፥ የዐሥር አለቆችም፥ ለፈራጆቻችሁም ጻፎች#ዕብ. “ገዦችም በየነገዶቻቸው” ይላል። አድርጌ ሰየምኋቸው። 16በዚያን ጊዜ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው። አልኋቸውም፦ የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፤ በሰውና በወንድሙ፥ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ። 17በፍርድም ፊት አትዩ፤ ለትልቁም፥ ለትንሹም በእውነት ፍረዱ፤ ለሰው ፊት አታድሉ፤ ፍርድ የእግዚአብሔር ነውና። አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ አምጡት፤ እኔም እሰማዋለሁ፤ 18በዚያን ጊዜም ልታደርጉት የሚገባችሁን ነገር ሁሉ አዘዝኋችሁ።
ከቃዴስ በርኔ ወደ ከነዓን የተላኩ ጕበኞች
(ዘኍ. 13፥1-33)
19“ከኮሬብም ተጓዝን፤ አምላካችን እግዚአብሔርም እንዳዘዘን በታላቁ፥ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ባያችሁት ምድረ በዳ ሁሉ በኩል በአሞሬዎን ተራራ መንገድ ሄድን፤ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን። 20እኔም አልኋችሁ፦ አምላካችን እግዚአብሔር እስከ ሰጣችሁ እስከ አሞሬዎን ተራራ ኑ፤ 21እነሆ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ምድሪቱን በፊታችሁ እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር እንዳላችሁ ውጡ፤ ውረሷት፤ አትፍሩ፤ አትደንግጡም። 22እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ፦ ምድሪቱን እንዲሰልሉልንና እንወጣባት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንላክ አላችሁኝ። 23ያም ነገር ደስ አሰኘኝ፤ ከእናንተም ዐሥራ ሁለት ሰው ወሰድሁ፤ ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ ሰው ነበረ። 24ሄዱም፤ ወደ ተራራውም ወጡ፤ ወደ ወይን ዘለላ ሸለቆ መጥተው ሰለሉአት። 25ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፤ ወደ እኛም ይዘውት መጡ፦ ‘አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት አሉን፤’
26“ወደ እርስዋ መውጣትንም እንቢ አላችሁ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይም ዐመፃችሁ፤ 27በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጕረመረማችሁ፦ ‘እግዚአብሔር ስለ ጠላን እንዲያጠፋን በአሞሬዎናውያን እጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን። 28ወዴት እንወጣለን? ሕዝቡ ታላቅና ብዙ ነው፤ ከእኛም ይጠነክራሉ፤ ከተሞቹም ታላላቆች፥ የተመሸጉም፥ እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፤ የረዐይትንም#ዕብ. “የኤናቅንም” ይላል ፤ “ረዐይት” ኀያላን ማለት ነው። ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አስፈሩት።’ 29እኔም አልኋችሁ፦ አትደንግጡ፤ ከእነርሱም አትፍሩ፤ 30በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ በግብፅ ምድር እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ ስለ እናንተ አብሮአችሁ ይዋጋል፤ 31ወደዚህም ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ ሰው ልጁን እንዲመግብ አምላካችሁ እግዚአብሔር በምድረ በዳ እንደመገባችሁ#ዕብ. “እንደ ተሸከማችሁ” ይላል። እናንተ አይታችኋል። 32ዳሩ ግን በዚህ ነገር አምላካችሁ እግዚአብሔርን አላመናችሁትም። 33እርሱም ስፍራን እንዲመርጥላችሁ፥ ትሄዱበትም ዘንድ የሚገባውን መንገድ እንዲያሳያችሁ ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን አላመናችሁትም።
እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ቀጣ
(ዘኍ. 14፥20-45)
34“እግዚአብሔርም የቃላችሁን ድምፅ ሰምቶ ተቈጣ፤ እንዲህም ብሎ ማለ፦ 35ለአባቶቻችሁ እሰጣት ዘንድ የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር ከእነዚህ ሰዎች#ዕብ. “ከዚህ ክፉ ትውልድ” ይላል። ማንም አያይም፥ 36ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በስተቀር፥ እርሱ ግን ያያታል፤ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ተከትሎአልና የረገጣትን ምድር ለእርሱ፥ ለልጆቹም እሰጣለሁ። 37እግዚአብሔርም በእናንተ ምክንያት በእኔ ተቈጣ፤ እንዲህም አለ፦ አንተ ደግሞ ወደዚያ አትገባም፤ 38በፊትህ የሚቆም የነዌ ልጅ ኢያሱ እርሱ ወደዚያ ይገባል፤ እርሱን አበርታው፤ ለእስራኤል ምድሪቱን ያወርሳልና። 39ደግሞ፦ ይማረካሉ ያላችኋቸው ልጆቻችሁ፥ ዛሬም መልካሙን ከክፉ መለየት የማይችሉ ሕፃኖቻችሁ እነርሱ ወደዚያ ይገባሉ፤ ምድሪቱንም ለእነርሱ እሰጣለሁ፤ ይወርሱአታልም። 40እናንተ ግን ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።
41“እናንተም፦ እግዚአብሔርን በድለናል፤ አምላካችን እግዚአብሔር እንዳዘዘን ሁሉ እንወጣለን፤ እንዋጋማለን ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ከእናንተም ሰው ሁሉ የጦር መሣሪያውን ያዘ፤ ወደ ተራራም ወጣችሁ። 42እግዚአብሔርም፦ እኔ ከእናንተ ጋር አይደለሁምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ፤ አትዋጉም በላቸው አለኝ። 43እኔም ተናገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ተላለፋችሁ፤ በኀይላችሁም ወደ ተራራማው አገር ወጣችሁ። 44በዚያም ተራራማ አገር ይኖሩ የነበሩ አሞሬዎናውያን ወጥተው ተጋጠሙአችሁ፤ ንብ እንደምትነድፍም ነደፉአችሁ፤ አሳደዱአችሁም፤ ከሴይር እስከ ሔርማም ድረስ መቱአችሁ። 45ተቀምጣችሁም በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት አለቀሳችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ድምፃችሁን አልሰማም፤ ወደ እናንተም አልተመለከተም። 46ቀድሞ እንደ ተቀመጣችሁበትም ዘመን መጠን በቃዴስ ብዙ ቀን ተቀመጣችሁ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ