ኦሪት ዘዳግም 12
12
አምልኮት ሊፈጸምበት የሚገባ ትክክለኛ ቦታ
1“በምድር ላይ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ትወርሷት ዘንድ በሚሰጣችሁ ሀገር ታደርጉት ዘንድ የምትጠብቁት ሥርዐት፥ ፍርድም ይህ ነው። 2እናንተ የምትወርሱአቸው አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩባቸውን፥ በረዥም ተራሮች፥ በኮረብቶችም ላይ ከለምለምም ዛፍ በታች ያለውን ስፍራ ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉት፤ 3መሠዊያቸውንም አፍርሱ፤ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐጸዶቻቸውንም ቁረጡ፤ የአማልክቶቻቸውንም ምስሎች በእሳት አቃጥሉ፤ ከዚያም ስፍራ ስማቸውን አጥፉ። 4ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር እንዲህ ያለ ሥራ በዚያ አትሥሩ። 5ነገር ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር ከከተሞቻችሁ ሁሉ በአንዱ ስሙ ይጠራ ዘንድ የመረጠውን ስፍራ ትሻላችሁ፤ ወደዚያም ትመጣላችሁ። 6ወደዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ቍርባናችሁንም፥ ዐሥራታችሁንም፥ ቀዳምያታችሁን፥ ስዕለታችሁንም፥ በፈቃዳችሁ የምታቀርቡትን፥ የላማችሁንና የበጋችሁንም በኵራት ውሰዱ። 7በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ብሉ፤ እጃችሁንም በምትዘረጉበት፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር በባረካችሁ ነገር ሁሉ፥ እናንተና ቤተሰባችሁ ደስ ይበላችሁ። 8ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን፥ እኛ በዚህ ዛሬ የምናደርገውን ሁሉ አታድርጉ፤ 9አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ማረፊያና ርስት እስከ ዛሬ ድረስ አልደረሳችሁምና። 10ዮርዳኖስን ግን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁም እግዚአብሔር በሚያወርሳችሁ ምድር በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ ያለ ፍርሀትም እንድትኖሩ ከከበቡአችሁ ጠላቶች ሁሉ ዕረፍት በሰጣችሁ ጊዜ፥ 11በዚያን ጊዜ አምላካችሁ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ ወደዚያ ወደ መረጠው ስፍራ፥ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ ቍርባናችሁንም፥ ዐሥራታችሁንም፥ ከእጃችሁ ሥራ ቀዳምያቱን የተመረጠውንም መባችሁን ሁሉ፥ ለአምላካችሁም የተሳላችሁትን ሁሉ ውሰዱ። 12እናንተም፥ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁም፥ ከእናንተ ጋር ክፍልና ርስት ስለሌለው በደጆቻችሁ ውስጥ የተቀመጠው ሌዋዊም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ። 13የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በሚታይህ ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። 14ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከነገዶችህ ከአንዱ ዘንድ በመረጠው ስፍራ በዚያ የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብ፤ በዚያም ዛሬ እኔ የማዝዝህን ሁሉ አድርግ።
15“ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ሰጠህ በረከት፥ እንደ ፈቀድህ፥ በሀገርህ ሁሉ ውስጥ አርደህ ሥጋን ብላ፤ ከአንተ ንጹሕ ሰው፥ ንጹሕም ያልሆነ ሰው እንደ ሚዳቋና እንደ ዋላ ያለውን ይብላው። 16ደሙን ግን እንደ ውኃ በምድር ላይ አፍስሱት እንጂ አትብሉት። 17የእህልህን፥ የወይን ጠጅህን፥ የዘይትህንም ዐሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኵራት፥ የተሳልኸውንም ስእለት ሁሉ፥ በፈቃድህ ያቀረብኸውን፥ የእጅህንም ቀዳምያት በከተሞችህ ሁሉ ውስጥ መብላት አትችልም። 18ነገር ግን አንተ፥ ወንድና ሴት ልጅህም፥ ወንድና ሴት አገልጋይህም፥ በሀገርህም ውስጥ ያለው መጻተኛ#ዕብ. “ሌዋዊ” ይላል። አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ብሉት፤ እጅህንም በምትዘረጋበት ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። 19በምድርህ ላይ በምትኖርበት ዘመን ሁሉ ሌዋዊዉን ቸል እንዳትል ተጠንቀቅ።
20“አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ነገረህ ድንበርህን ባሰፋልህ ጊዜ፥ ሰውነትህም ሥጋ መብላት ስለ ወደደች፦ ሥጋ ልብላ ስትል፥ ሰውነትህ ከወደደችው ሁሉ ብላ። 21አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራ ዘንድ የመረጠው ስፍራ ከአንተ ሩቅ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከላምና ከበግ መንጋህ እንዳዘዝሁህ እረድ፤ ሰውነትህም የወደደችውን በሀገርህ ውስጥ ብላው። 22ሚዳቋና ዋላ እንደሚበሉ እንዲሁ ብላው፤ ከአንተ ንጹሕ ሰው፥ ንጹሕም ያልሆነ ይብላው። 23ደምን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደሙ ነፍሱ ነውና፥ ነፍስም ከሥጋ ጋር አይበላምና። 24በምድር ላይ እንደ ውኃ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 25በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ጥሩ የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁ፥ አትብላው። 26ነገር ግን የተቀደሰውን ነገርህን፥ ስእለትህንም ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ በዚያ እንዲጠራ ወደ መረጠው ስፍራ ሂድ። 27ሥጋውን#ዕብ. “ሥጋውንና ደሙን” ይላል። የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የመሥዋዕትህም ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፥ ሥጋውንም ብላው። 28በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ጥሩ የሆነውን ነገር ስታደርግ ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ ለዘለዓለም መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ እኔ የማዝዝህን እነዚህን ቃሎች ሁሉ ሰምተህ ጠብቅ።
ለጣዖት መስገድ እንደማይገባ
29“አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳቸው ዘንድ የምትሄድባቸውን አሕዛብ በፊትህ ባጠፋ ጊዜ፥ አንተም በወረስሃቸው ጊዜ፥ በምድራቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፥ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ እነርሱን ለመከተል እንዳትሻ፥ 30አምላኮቻቸውንም እንዳትሻ፥ አሕዛብም ለአምላኮቻቸው እንደሚያደርጉ እኔም አደርጋለሁ እንዳትል ራስህን ጠብቅ። 31ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲሁ አታድርግ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአምላኮቻቸው በእሳት ስለሚያቃጥሉ አሕዛብ ለአምላኮቻቸው የሚያደርጉትን ርኩስ ነገር እግዚአብሔር ይጠላልና።
32“እኔ ዛሬ የማዝዝህን ነገር ሁሉ ታደርገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእርሱ ላይ አትጨምር፤ ከእርሱም ምንም አታጕድል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 12: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ