ኦሪት ዘዳግም 9
9
በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ የሚያስከትለው መቅሠፍት
1“እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ከአንተ የበለጡትንና የበረቱትን አሕዛብ፥ የቅጽራቸው ግንብ እስከ ሰማይ የሚደርስ ታላላቆች ከተሞችን ለመውረስ ትገቡ ዘንድ ዛሬ ዮርዳኖስን ትሻገረዋለህ። 2አንተም የምታውቃቸው፥ ስለ እነርሱም፦ በዔናቅ ልጆች ፊት መቆም ማን ይችላል? ሲባል የሰማኸው ታላቅ፥ ብዙና ረዥም ሕዝብ የዔናቅ ልጆች ናቸው። 3አምላክህም እግዚአብሔር በፊትህ እንዲያልፍ ዛሬ ዕወቅ፤ እርሱ የሚበላ እሳት ነው፤ እርሱ ያጠፋቸዋል፤ በፊትህም ያዋርዳቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ነገረህ ከፊትህ ያርቃቸዋል፥ ፈጥኖም ያጠፋቸዋል። 4አምላክህ እግዚአብሔር እነዚያን አሕዛብ ከፊትህ ባወጣቸው ጊዜ፦ ስለ ጽድቄ እወርሳት ዘንድ ወደዚች መልካም ምድር እግዚአብሔር አገባኝ ብለህ በልብህ አትናገር፤#ዕብ. “ነገር ግን እነዚህን አሕዛብ ስለ ኀጢአታቸው እግዚአብሔር ከፊትህ ያጠፋቸዋል” የሚል ይጨምራል። 5ምድራቸውን ትወርሳት ዘንድ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንነት አይደለም፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ በሚያጠፋቸው በእነዚያ አሕዛብ ኀጢአት ምክንያትና ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው። 6እንግዲህ አንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነህና አምላክህ እግዚአብሔር ይህችን መልካም ምድር ርስት አድርጎ የሰጠህ ስለ ጽድቅህ እንዳይደለ ዛሬ ዕወቅ።
7“አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ ምን ያህል እንዳሳዘንኸው፥ ከግብፅ ሀገር ከወጣህበት ቀን ጀምሮ ወደዚህ ስፍራ እስከ መጣችሁ ድረስ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ አስብ፤ አትርሳም። 8በኮሬብ ደግሞ እግዚአብሔርን አሳዘናችሁት፤ እግዚአብሔርም ሊያጠፋችሁ በእናንተ ላይ ተቈጣ። 9ሁለቱን የድንጋይ ጽላት፥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የተማማለባቸውን የቃል ኪዳን ጽላት እቀበል ዘንድ ወደ ተራራ በወጣሁ ጊዜ፥ በተራራው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ተቀምጬ ነበር፤ እንጀራ አልበላሁም፤ ውኃም አልጠጣሁም። 10እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ጣት የተጻፉትን ሁለት የድንጋይ ጽላት ሰጠኝ፤ በተሰበሰባችሁ ጊዜ እግዚአብሔር#ዕብ. “በእሳት ውስጥ ሆኖ” የሚል ይጨምራል። በተራራው ላይ የነገረኝ ቃል ሁሉ ተጽፎባቸው ነበር። 11ከአርባ ቀንና ከአርባ ሌሊትም በኋላ እግዚአብሔር ሁለቱን የድንጋይ ጽላት፥ የቃል ኪዳኑን ጽላት ሰጠኝ። 12እግዚአብሔርም አለኝ፦ ተነሥተህ ከዚህ ፈጥነህ ውረድ፤ ከግብፅ ያወጣሃቸው ሕዝብህ በድለዋልና፤ ፈጥነው ካዘዝኋቸው መንገድ ፈቀቅ ብለዋልና፥ ቀልጦ የተሠራ ምስልም ለራሳቸው አድርገዋልና። 13እግዚአብሔርም አለኝ፦ ‘አንድ ጊዜም ሁለት ጊዜም እንዲህ ብዬ ነገርሁህ፤#“አንድ ጊዜም ሁለት ጊዜም እንዲህ ብዬ ነገርሁህ” የሚለው በዕብ. የለም። ይህ ሕዝብ አንገተ ደንዳና ሕዝብ እንደ ሆነ አይችአለሁ፤ 14አጠፋቸው ዘንድ፥ ስማቸውንም ከሰማይ በታች እደመስስ ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ከእነርሱ ለሚበረታና እጅግ ለሚበዛ ሕዝብ አደርግሃለሁ።’ 15እኔም ተመልሼ ከተራራው ወረድሁ፤ ተራራውም በእሳት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እስከ ሰማይ” ብሎ ይጨምራል። ይነድድ ነበር፤ ሁለቱም የቃል ኪዳን ጽላት በሁለቱ እጆች ነበሩ። 16እነሆ፥ በአምላካችሁ እግዚአብሔር ፊት እንደ በደላችሁ፥ ለእናንተም ቀልጦ የተሠራ ምስል ሠርታችሁ ልትጠብቁት እግዚአብሔር ካዘዛችሁ መንገድ ፈጥናችሁ ፈቀቅ እንዳላችሁ ባየሁ ጊዜ፥ 17ሁለቱንም ጽላት ያዝሁ፤ ከሁለቱም እጆች ጣልኋቸው፤ በእናንተም ፊት ሰበርኋቸው። 18ስለ ሠራችሁት ኀጢአት ሁሉ፥ እርሱንም ለማስቈጣት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጋችሁ፥ እንደ ፊተኛው በእግዚአብሔር ፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ዳግመኛ ለመንሁ፤ እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም። 19እግዚአብሔርም ሊያጠፋችሁ ከተቈጣባችሁ ከቍጣውና ከመዓቱ የተነሣ ፈራሁ፤ እግዚአብሔርም በዚያን ጊዜ ደግሞ ሰማኝ። 20እግዚአብሔርም አሮንን ሊያጠፋው እጅግ ተቈጣው፤ ስለ አሮንም ደግሞ በዚያን ጊዜ ጸለይሁ። 21ስለ አደረጋችሁትም ኀጢአት የጥጃውን ምስል ወሰድሁ፤ በእሳትም አቃጠልሁት፤ አደቀቅሁትም፤ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨሁት፤ እንደ ትቢያም ሆነ፤ ትቢያውንም ከተራራው በሚወርድ ወንዝ ጨመርሁት።
22“በውዕየት፥ በፈተናም#ዕብ. “በተቤራም በማሳህም” ይላል። በምኞት መቃብርም እግዚአብሔርን አስቈጣችሁት። 23እግዚአብሔርም፦ ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ውረሱ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁ ጊዜ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ዐመፃችሁ፤ በእርሱም አላመናችሁም፤ ቃሉንም አልሰማችሁም። 24ለእናንተ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ በእግዚአብሔር ዐመፀኞች ነበራችሁ።
25“እግዚአብሔርም፦ ያጠፋችሁ ዘንድ ስለ ተናገረ ቀድሞ እንደ ለመንሁ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ለመንሁ። 26በእግዚአብሔርም ፊት እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፦ የአማልክት ንጉሥ እግዚአብሔር ሆይ፥ በታላቅ ኀይልህ የተቤዠሃቸውን፥ በጠነከረችውም እጅህና በተዘረጋች ክንድህ ከግብፅ ያወጣሃቸውን ሕዝብህንና ርስትህን አታጥፋ። 27በራስህ የማልህላቸውን አገልጋዮችህን አብርሃምንና ይስሐቅን፥ ያዕቆብንም አስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፥ ክፋቱንም፥ ኀጢአቱንም አትመልከት፤ 28ከእርስዋ እኛን ያወጣህባት ምድር ሰዎች፦ እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና፥ ጠልቶአቸውማልና ስለዚህ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው እንዳይሉ። 29እነርሱም በታላቅ ኀይልህ፥ በጸናውና በተዘረጋውም ክንድህ ከግብፅ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 9: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ