ኦሪት ዘፀአት 18
18
ዮቶር ሙሴን እንደ መከረው
1የምድያም ካህን የሙሴ አማት ዮቶር እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን ከግብፅ እንደ አወጣ ሰማ። 2በዚያ ጊዜ የሙሴ አማት ዮቶር ትቶአት የነበረውን የሙሴን ሚስት ሲፓራን፥ ሁለቱንም ልጆችዋን ወሰደ። 3የአንደኛው ስም ጌርሳም ነበረ፤ አባቱ “በሌላ ሀገር ስደተኛ ነበርሁ” ብሎአልና፤ 4የሁለተኛውም ስም አልዓዛር ነበረ፤ “የአባቴ አምላክ ረዳኝ፤ ከፈርዖንም እጅ አዳነኝ” ብሎአልና። 5የሙሴ አማት ዮቶርም ከልጆቹና ከሚስቱ ጋር በእግዚአብሔር ተራራ አጠገብ በምድረ በዳ ወደ ሰፈረ ወደ ሙሴ መጣ። 6ሙሴንም፥ “እነሆ፥ አማትህ ዮቶር፥ ሚስትህም ከእርስዋም ጋር ሁለቱ ልጆችህ መጥተውልሃል” አሉት። 7ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ወጣ፤ እጅ ነሣው፤ ሳመውም፤ እርስ በርሳቸውም ሰላምታ ተሰጣጡ፤ ወደ ድንኳኑም ገቡ። 8ሙሴም እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ስለ እስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ በመንገድም ያገኛቸውን ድካም ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እንደ አዳናቸው ለአማቱ ነገረው። 9ዮቶርም እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ቸርነት ሁሉ፥ ከግብፃውያን እጅና ከፈርዖን እጅ እንደ አዳናቸው ሰምቶ በሁሉ አደነቀ። 10ዮቶርም፥ “ከግብፃውያን እጅና ከፈርዖን እጅ ሕዝቡን የአዳነ እግዚአብሔር ቡሩክ ነው። 11እግዚአብሔርም ግብፃውያን ከሚመኩባቸውና ከሚገዙላቸው አማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አሁን ዐወቅሁ” አለ። 12የሙሴ አማት ዮቶርም የሚቃጠል መሥዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከሙሴ አማት ጋር እንጀራ ሊበሉ አሮንና የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ።
የዳኞች መሾም
(ዘዳ. 1፥9-18)
13እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ በሕዝቡ ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ ቆመው ነበር። 14ዮቶርም ሙሴ በሕዝቡ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቶ እንዲህ አለው፥ “ብቻህን ተቀምጠህ በሕዝቡ የምታደርገው ይህ ምንድን ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመዋል።” 15ሙሴም አማቱን፥ “ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ፍርድ ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ 16ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፤ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ሥርዐትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ” አለው። 17የሙሴም አማት አለው፥ “አንተ የምታደርገው ይህ ነገር ትክክል አይደለም። 18አንተ፥ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ ይህ ነገር ይከብድብሃል፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። 19አሁንም እመክርሃለሁና ስማኝ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፤ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤ 20የእግዚአብሔርንም ሥርዐቱንና ሕጉን መስክርላቸው፤ የሚሄዱበትንም መንገድ፥ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው። 21አንተም ከሕዝቡ ሁሉ ኀያላን ሰዎችን፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን እውነተኞች ሰዎችን፥ ትዕቢትንም የሚጠሉ ሰዎችን ፈልግ። ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የዐሥርም አለቆችን ሹምላቸው። 22በሕዝቡ ላይ ሁል ጊዜ ይፍረዱ፤ የከበዳቸውን ነገር ወደ አንተ ያምጡት፤ ቀላሉን ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤ ያቃልሉልሃል፤ ይረዱሃልም። 23ይህንም ቃሌን ብታደርግ፥ እግዚአብሔር ያበረታሃል፤ መፍረድም ትችላለህ፤ ሕዝቡም ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይመለሳል።” 24ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፤ እንደ አለውም አደረገ። 25ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መረጠ፤ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶ አለቆች፥ የአምሳም አለቆች፥ የዐሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው። 26በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበዳቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፤ ቀላሉን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ። 27ሙሴም አማቱን አሰናበተው፤ እርሱም ወደ ሀገሩ ተመለሰ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 18: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ