የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀ​አት 22

22
ስለ ዕዳ አከ​ፋ​ፈል
1“ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰ​ርቅ፥ ቢያ​ር​ደው ወይም ቢሸ​ጠው፥ በአ​ንድ በሬ ፋንታ አም​ስት በሬ​ዎች፥ በአ​ንድ በግም ፋንታ አራት በጎች ይክ​ፈል። 2ሌባ ቤት ሲምስ ቢገኝ፥ እር​ሱም ቢመታ፥ ቢሞ​ትም በመ​ታው ሰው ላይ የደም ዕዳ አይ​ሆ​ን​በ​ትም። 3ፀሐይ ግን ከወ​ጣ​ች​በት የደም ዕዳ አለ​በት፤ የገ​ደ​ለው ይገ​ደል፤#ዕብ. “ሌባው የሰ​ረ​ቀ​ውን ይመ​ልስ” ይላል። ሌባው ቢያዝ የሚ​ከ​ፍ​ለ​ውም ቢያጣ ስለ ሰረ​ቀው ይሸጥ። 4የሰ​ረ​ቀው ደኅና ሆኖ በእጁ ቢገኝ፥ በሬ ወይም በግ ቢሆን፥ የሰ​ረ​ቀ​ውን ያህል ሁለት እጥፍ ይክ​ፈል።
5“የሰ​ውን አዝ​መራ ከብ​ቱን ያስ​በላ፥ የሌላ ሰው ወይ​ን​ንም ያስ​በላ ሰው ቢኖር ግም​ቱን ይክ​ፈል። የሰ​ውን አዝ​መራ ፈጽሞ ቢያ​ስ​በላ ግን በአ​ጠ​ገቡ ባለ አዝ​መራ ልክ ይክ​ፈል፤ ወይ​ንም ቢሆን በአ​ጠ​ገቡ ባለ ወይን ልክ ይክ​ፈል።
6“እሳት ቢነሣ ጫካ​ው​ንም ቢይዝ፥ ዐው​ድ​ማ​ው​ንም፥ ክም​ሩ​ንም ወይም ያል​ታ​ጨ​ደ​ውን እህል ወይም እር​ሻ​ውን ቢያ​ቃ​ጥል እሳ​ቱን ያነ​ደ​ደው ይክ​ፈል።
7“ሰው በባ​ል​ን​ጀ​ራው ዘንድ ብር ወይም ሌላ ዕቃ እን​ዲ​ጠ​ብ​ቅ​ለት አደራ ቢያ​ኖር ከቤ​ቱም ቢሰ​ረቅ፥ ሌባው ቢገኝ እጥፍ ይክ​ፈል። 8ሌባው ባይ​ገኝ ባለ​ቤቱ ወደ ፈጣሪ ፊት ይቅ​ረብ፤ ባል​ን​ጀ​ራው አደራ በአ​ስ​ቀ​መ​ጠ​በት ገን​ዘ​ብም ላይ እን​ዳ​ል​ተ​ተ​ነ​ኰ​ለና ክፉ እን​ዳ​ላ​ሰበ ይማል።#ዕብ. “በባ​ል​ን​ጀ​ራው ከብት ላይ እጁን እን​ዳ​ል​ዘ​ረጋ ይማል” ይላል። 9ሰዎች ስለ በሬ ወይም ስለ አህያ ወይም ስለ በግ ወይም ስለ ልብስ ወይም ስለ​ሌላ ስለ ጠፋ ነገር ቢካ​ሰሱ፥ አን​ዱም፦ ‘ይህ የእኔ ነው’ ቢል፥ ክር​ክ​ራ​ቸው በፈ​ጣሪ ፊት#ዕብ. “በዳ​ኞች ፊት” ይላል። ይቅ​ረብ፤ በፈ​ጣሪ ፊት የተ​ፈ​ረ​ደ​በት እርሱ ለባ​ል​ን​ጀ​ራው እጥፍ ይክ​ፈል።
10“ሰው በባ​ል​ን​ጀ​ራው ዘንድ አህያ ወይም በሬ ወይም በግ ወይም ሌላ እን​ስሳ እን​ዲ​ጠ​ብ​ቅ​ለት አደራ ቢያ​ኖር፥ ማንም ሳያይ ቢሞት ወይም ቢጐዳ ወይም ቢማ​ረክ፥ 11በባ​ል​ን​ጀ​ራው ከብት ላይ እጁን እን​ዳ​ል​ዘ​ረጋ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሐላ በሁ​ለ​ታ​ቸው መካ​ከል ይሁን፤ የከ​ብ​ቱም ባለ​ቤት ይህን ከተ​ቀ​በለ፥ እርሱ ምንም አይ​ክ​ፈል። 12ከእ​ር​ሱም ዘንድ ቢሰ​ረቅ ለባ​ለ​ቤቱ ይክ​ፈል። 13በም​ድረ በዳም አውሬ ቢበ​ላው ውዳ​ቂ​ውን ያሳይ፤ አይ​ክ​ፈ​ልም። 14ሰው ከባ​ል​ን​ጀ​ራው አን​ዳች ቢዋስ ባለ​ቤቱ ከእ​ርሱ ጋር ሳይ​ኖር ቢጎዳ፥ ወይም ቢሞት፥ ወይም ቢነ​ጠቅ ፈጽሞ ይክ​ፈ​ለው። 15ባለ​ቤቱ ግን ከእ​ርሱ ጋር ቢኖር አይ​ክ​ፈል፤ ቢከ​ራ​የ​ውም ኪራ​ዩን ይክ​ፈል።
ማኅ​በ​ራ​ዊና ሃይ​ማ​ኖ​ታዊ ሕጎች
16“ሰው ያል​ታ​ጨ​ች​ውን ድን​ግል ቢያ​ስ​ታት፥ ከእ​ር​ስ​ዋም ጋር ቢተኛ ሚስት አድ​ርጎ ይው​ሰ​ዳት።#ዕብ. “ማጫ​ዋን ሰጥቶ ሚስት ያድ​ር​ጋት” ይላል። 17አባ​ቷም እር​ስ​ዋን እን​ዳ​ይ​ሰ​ጠው ፈጽሞ እንቢ ቢል እንደ ደና​ግል ማጫ ያህል ማጫ​ዋን ይስ​ጠው።
18“ከመ​ተ​ተኛ ጋር አንድ አት​ሁኑ።
19“ከእ​ን​ስሳ የሚ​ደ​ርስ ሁሉ ሞትን ይሙት።
20“ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ብቻ በቀር ለአ​ማ​ል​ክት የሚ​ሠዋ ፈጽሞ ይጥፋ። 21እና​ንተ በግ​ብፅ ምድር ስደ​ተ​ኞች ነበ​ራ​ች​ሁና ስደ​ተ​ኛ​ውን አት​በ​ድ​ሉት፤ ግፍም አታ​ድ​ር​ጉ​በት። 22መበ​ለ​ቲ​ቱ​ንና ድሀ-አደ​ጎ​ቹን አታ​ስ​ጨ​ን​ቁ​አ​ቸው። 23ብታ​ስ​ጨ​ን​ቁ​አ​ቸ​ውና ወደ እኔ ቢጮኹ እኔ ጩኸ​ታ​ቸ​ውን ፈጽሞ እሰ​ማ​ለሁ፤ 24ቍጣ​ዬም ይጸ​ና​ባ​ች​ኋል፤ በሰ​ይ​ፍም አስ​ገ​ድ​ላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ሚስ​ቶ​ቻ​ች​ሁም መበ​ለ​ቶች፥ ልጆ​ቻ​ች​ሁም ድሀ-አደ​ጎች ይሆ​ናሉ።
25“ከአ​ንተ ጋር ለተ​ቀ​መ​ጠው ለድ​ሃው ወገ​ንህ ብር ብታ​በ​ድ​ረው፥ አታ​ስ​ጨ​ን​ቀው፤ አራ​ጣም አታ​ስ​ከ​ፍ​ለው። 26የባ​ል​ን​ጀ​ራ​ህን ልብስ ለመ​ያዣ ብት​ወ​ስድ ፀሐይ ሳት​ገባ መል​ስ​ለት፤ 27ልብሱ ነውና፥ ዕር​ቃ​ኑ​ንም የሚ​ሸ​ፍ​ን​በት ይህ ብቻ ነውና፤ የሚ​ተ​ኛ​በ​ትም ሌላ የለ​ው​ምና፤ ወደ እኔም ቢጮኽ ፈጥኜ እሰ​ማ​ዋ​ለሁ፤ መሓሪ ነኝና።
28“ፈራ​ጆ​ችን አት​ስ​ደብ፥ የሕ​ዝ​ብ​ህ​ንም አለቃ ክፉ አት​ና​ገ​ረው። 29የአ​ው​ድ​ማ​ህ​ንና የወ​ይ​ን​ህ​ንም መጀ​መ​ሪያ ለማ​ቅ​ረብ አት​ዘ​ግይ፤ የል​ጆ​ች​ህ​ንም በኵር ትሰ​ጠ​ኛ​ለህ። 30እን​ዲ​ሁም በበ​ሬ​ዎ​ች​ህና በበ​ጎ​ችህ፥ በአ​ህ​ያ​ህም ታደ​ር​ገ​ዋ​ለህ፤ ሰባት ቀን ከእ​ናቱ ጋር ይቀ​መጥ፤ በስ​ም​ን​ተ​ኛ​ውም ቀን ለእኔ ትሰ​ጠ​ዋ​ለህ። 31ቅዱስ ወገን ትሆ​ኑ​ል​ኛ​ላ​ችሁ፤ ስለ​ዚህ አውሬ የገ​ደ​ለ​ውን ሥጋ ለውሻ ጣሉት እንጂ አት​ብ​ሉት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ