ኦሪት ዘፀአት 32
32
የወርቅ ጥጃው ምስል
(ዘዳ. 9፥6-29)
1ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው፥ “ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን” አሉት። 2አሮንም፥ “በሚስቶቻችሁና በሴቶች ልጆቻችሁ ጆሮ ያሉትን የወርቅ ጌጦች አምጡልኝ” አላቸው። 3ሕዝቡም ሁሉ በጆሮዎቻቸው ያሉትን የወርቅ ጌጦች ወደ አሮን አመጡለት። 4ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፤ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም፥ “እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው” አላቸው። 5አሮንም በአየው ጊዜ መሠዊያውን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም፥ “ነገ የእግዚአብሔር በዓል ነው” ሲል አወጀ። 6አሮንም በነጋው ማልዶ ተነሣ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ሠዋ፤ የደኅንነት መሥዋዕትንም አቀረበ#ዕብ. “በበነጋው ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሰዉ ፤ የደኅንነት መሥዋዕትም አቀረቡ” ይላል። ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ።
7እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው እንዲህም አለው፥ “ከግብፅ ምድር ያወጣኻቸው ሕዝብህ በድለዋልና ሂድ፤ ፈጥነህ ውረድ። 8ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፤ ሰገዱለትም፤ ሠዉለትም፤ 9‘እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው’ አሉ።#ዕብ. “እግዚአብሔርም ሙሴን፥ እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት ፤ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው” የሚል ይጨምራል። 10አሁንም ተቈጥቼ አጠፋቸው ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” 11ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፤ አለም፥ “አቤቱ፥ በታላቅ ኀይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር በአወጣኸው በሕዝብህ ላይ ለምን ተቈጣህ? 12ግብፃውያንስ፦ ‘በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው’ ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፤ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። 13ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፤ ለዘለዓለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸው ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ዐስብ።” 14እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ይቅር አለ።
15ሙሴም ተመለሰ፤ ሁለቱንም የምስክር ጽላት በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ የድንጋይ ጽላቱም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። 16ጽላቱ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቱ ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ። 17ኢያሱም ሲጮሁ የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ሙሴን፥ “የሰልፍ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ” አለው። 18ሙሴም፥ “ይህ የድል ነሺዎች ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፤ ነገር ግን የወይን ስካር ድምፅ እሰማለሁ” አለው። 19እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፤ እነዚያንም ሁለቱን ጽላት ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበራቸው። 20የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፤ ፈጨው፤ አደቀቀውም፤ በውኃም ላይ በተነው፤ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣቸው።
21ሙሴም አሮንን፥ “ይህን ታላቅ ኀጢአት ታመጣበት ዘንድ ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ?” አለው። 22አሮንም እንዲህ አለ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በእኔ ላይ አትቈጣ፤ የዚህን ሕዝብ ጠባይ አንተ ታውቃለህ። 23እነርሱም ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉኝ። 24እኔም ከእናንተ ወርቅ ያለው ሰው ያምጣልኝ አልኋቸው፤ ሰጡኝም፤ በእሳትም ላይ ጣልሁት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።”
25ሙሴም በጠላቶቻቸው ፊት እንዲነወሩ አሮን ስድ ለቅቆአቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቀ በአየ ጊዜ፥ 26ሙሴ በሰፈሩ ደጅ ቆሞ፥ “የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ” አለ፤ የሌዊ ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። 27እርሱም፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፤ ሂዱና በሰፈሩ ውስጥ ከበር እስከ በር ተመላለሱ፤ እያንዳንዱም ወንድሙን፥ እያንዳንዱም ጎረቤቱን፥ እያንዳንዱም የቅርቡን ይግደል” አላቸው። 28የሌዊም ልጆች ሙሴ እንዳለ አደረጉ፤ በዚያም ቀን ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ሰዎች ሞቱ። 29ሙሴም፥ “ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ ከልጁና፥ ከወንድሙ የተነሣ እግዚአብሔርን በእጃችሁ ደስ አሰኛችሁት” አላቸው።
30በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ፥ “እናንተ ታላቅ በደል ሠርታችኋል፤ አሁንም አስተሰርይላችሁ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤” አላቸው። 31ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኀጢአት ሠርተዋል፤ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ 32አሁንም ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር ትላቸው እንደሆነ ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ ደምስሰኝ” አለ። 33እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “በፊቴ የበደለውን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። 34አሁንም ሂድ፤ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ቦታ ምራ፤ እነሆ፥ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኀጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ” አለው። 35አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቀሠፈ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 32: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ