ኦሪት ዘፀአት 34
34
እንደ ገና የተሠሩት ጽላቶች
(ዘዳ. 10፥1-5)
1እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ሁለት የድንጋይ ጽላት እንደ ፊተኞቹ አድርገህ ቅረጽ፤ ወደ እኔም ወደ ተራራ ውጣ፤ በሰበርሃቸው በፊተኞቹ ጽላት የነበሩትን ቃላት እጽፍባቸዋለሁ። 2ለጥዋትም የተዘጋጀህ ሁን፤ ወደ ሲና ተራራ ወጥተህ በዚያ በተራራው ራስ ላይ በፊቴ ቁም። 3ከአንተም ጋር ማንም ሰው አይውጣ፤ በተራራውም ሁሉ ማንም አይታይ፤ መንጎችና ከብቶችም በዚያ ተራራ አጠገብ አይሰማሩ። 4ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጎ ሁለት የድንጋይ ጽላት ቀረጸ፤ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላት በእጁ ወሰደ፤ በነጋውም ማልዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ 5እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፤ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ። 6ጌታም በፊቱ አለፈ፥ “ስሜም ጌታ እግዚአብሔር፥ መሓሪ፥ ይቅር ባይ፥ ከመዓት የራቀ ምሕረቱ የበዛ ጻድቅ፥ 7ለብዙ ሺህ ጽድቅን የሚጠብቅ፥ ቸርነትን የሚያደርግ፥ አበሳንና መተላለፍን፥ ኀጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኀጢአት በልጆች፥ እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው” ሲል አወጀ። 8ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጎነበሰና ለእግዚአብሔር ሰገደ፦ 9“አቤቱ በፊትህስ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ይህ ሕዝብ አንገተ ደንዳና ነውና ጌታዬ ከእኛ ጋር ይሂድ፤ ጠማማነታችንን፥ ኀጢአታችንንና በደላችንን ይቅር በለን፤ ለአንተም እንሆናለን” አለ።
እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን እንደ ገና ማደሱ
(ዘፀ. 23፥14-19፤ ዘዳ. 7፥1-5፤ 16፥1-17)
10እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እነሆ፥ እኔ በሕዝብህ ፊት ሁሉ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በምድር ሁሉ፥ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እንደ እርሱ ያለ ከቶ ያልተደረገውን ታላቅ ተአምራትን አደርግልሃለሁ፤ እኔም የማደርግልህ ነገር ድንቅ ነውና አንተ በመካከሉ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል። 11በዚህ ቀን የማዝዝህን ነገር ጠብቅ፤ እነሆ፥ እኔ አሞሬዎናዊውን፥ ከነዓናዊውንም፥ ኬጤዎናዊውንም፥ ፌርዜዎናዊውንም፥ ጌርጌሴዎናዊውንም፥ ኤዌዎናዊውንም፥ ኢያቡሴዎናዊውንም ከፊትህ አወጣለሁ። 12በመካከልህ ወጥመድ እንዳይሆኑብህ አንተ በምትገባበት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ 13ነገር ግን መሠውያዎቻቸውን ታፈርሳላችሁ፤ ሐውልቶቻቸውንም ትሰብራላችሁ፤ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውን ትቈርጣላችሁ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት ታቃጥላላችሁ፤#“ጣዖቶቻቸውን በእሳት ታቃጥላላችሁ” የሚለው በዕብ. የለም። 14ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር ቅንዐት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ። 15በዚያች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፥ እነርሱ አምላኮቻቸውን ተከትለው በአመነዘሩና በሠዉላቸው ጊዜ እንዳይጠሩህ፥ ከመሥዋዕታቸውም እንዳትበላ፥ 16ሴቶች ልጆቻቸውምንም ከወንድ ልጆችህ፥ ሴቶች ልጆችህንም ከወንድ ልጆቻቸው ጋር እንዳታጋባ፥ ልጆቻቸውም አምላኮቻቸውን ተከትለው ሲያመነዝሩ ከአምላኮቻቸው በኋላ ሄደው አመንዝረውም ልጆችህን እንዳያስቱ ተጠንቀቅ። 17ቀልጠው የተሠሩትን አማልክት ለአንተ አታድርግ።
18“የቂጣውን በዓል ትጠብቀዋለህ። በሚያዝያ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና በታዘዘው ዘመን በሚያዝያ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ ብላ። 19መጀመሪያ የሚወለድ ተባት ሁሉ የእኔ ነው፤ የላምህም በኵር፥ የበግህም በኵር፥ የበሬህም በኵር ሁሉ የእኔ ነው። 20የአህያውንም በኵር በበግ ትዋጀዋለህ፤ ባትዋጀው#ዕብ. “አንገቱን ትሰብረዋለህ” ይላል። ግን ዋጋውን ትሰጣለህ። የልጆችህንም በኵር ሁሉ ትዋጃለህ። በፊቴም ባዶ እጅህን አትታይ።
21“ስድስት ቀን ሥራህን ትሠራለህ፤ በሰባተኛውም ቀን ታርፋለህ። በምትዘራበትና በምታጭድበት ዘመን ታርፋለህ። 22የሰባቱንም ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ፤ እርሱም የስንዴ መከር መጀመሪያ ነው፤ በዓመቱም መካከል የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ። 23ወንድ ልጅህ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ፊት በዓመት ሦስት ጊዜ ይታይ። 24አሕዛብን ከፊትህ በአወጣሁ ጊዜ ሀገርህን አሰፋለሁ፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊትም ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም።
25“የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የፋሲካውም በዓል መሥዋዕት እስከ ነገ አይደር። 26የመጀመሪያውን የምድርህን ፍሬ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ትወስዳለህ። ጠቦቱን በእናቱ ወተት አትቀቅል።”
27እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “በእነዚህ ቃሎች ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ” አለው። 28በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም። በጽላቱም ዐሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ።
የሙሴ ፊት እንደ አበራ
29እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ#ዕብ. “የምስክር ጽላት” ይላል። ጽላት በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ፊቱ እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። 30አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እነሆ፥ ፊቱ እንዳንጸባረቀ ሙሴን በአዩ ጊዜ፥ ወደ እርሱ ለመቅረብ ፈሩ። 31ሙሴም ጠራቸው፤ አሮንም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም ተናገራቸው። 32ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። 33ሙሴም ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ። 34ሙሴም ከእርሱ ጋር ይነጋገር ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በገባ ጊዜ እስኪወጣ ድረስ መሸፈኛውን ከፊቱ ያነሣ ነበር፤ በወጣም ጊዜ ለእስራኤል ልጆች የታዘዘውን ነገር ይነግራቸው ነበር። 35የእስራኤልም ልጆች የሙሴን ፊት እንዳንጸባረቀ ያዩ ነበር፤ እርሱም ከእርሱ ጋር ሊነጋገር እስኪገባ ድረስ እንደ ገና በፊቱ መሸፈኛ ያደርግ ነበር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 34: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ