ኦሪት ዘፀአት 5
5
ሙሴና አሮን በፈርዖን ፊት
1ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ገብተው እንዲህ አሉት፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በምድረ በዳ በዓል ያደርግልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።’ ” 2ፈርዖንም፥ “የእስራኤልን ልጆች እለቅቅ ዘንድ ቃሉን የምሰማው እርሱ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም” አለ። 3እነርሱም፥ “ቸነፈር ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ የዕብራውያን አምላክ ጠራን” አሉት። 4የግብፅ ንጉሥም፥ “እናንተ ሙሴና አሮን፥ ሕዝቡን ለምን ሥራቸዉን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ” አላቸው። 5ፈርዖንም ለሕዝቡ አለ፥ “እነሆ፥ ሕዝቡ በምድር በጣም በዝተዋል፤ እናንተም ከሥራቸው አሳርፋችኋቸዋል። 6ፈርዖንም በዚያ ቀን የሕዝቡን አሠሪዎችና ጸሓፊዎች እንዲህ ሲል አዘዘ፦ 7“እንደ ወትሮው ለጡብ ሥራ ደግሞ ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ ነገር ግን እነርሱ ሄደው ለራሳቸው ገለባ ይሰብስቡ። 8ቀድሞ ያደርጉት የነበረውን የጡብ ቍጥር እንዲሁ በየቀኑ በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ምንም ከእርሱ አታጕድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ፦ ‘ለአምላካችን እንድንሠዋ እንሂድ’ እያሉ ይጮሃሉ። 9በእነዚህ ሰዎች ላይ ሥራው ይክበድባቸው፤ ይህን ብቻ ያስባሉ፤ ከንቱ ቃልም አያስቡም።” 10የሕዝቡም አሠሪዎችና ጸሓፊዎች ወጡ፤ ሕዝቡንም፥ “ፈርዖን እንዲህ ይላል፦ እንግዲህ ገለባ አይሰጣችሁም፤ 11እናንተ ሂዱ፤ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከምትሠሩት ጡብ ግን ምንም አይጐድልም” አሉአቸው። 12ሕዝቡም ሁሉ ስለ ገለባ እብቅ ሊሰበስቡ በግብፅ ምድር ሁሉ ተበተኑ። 13አሠሪዎቹም፥ “ገለባ ትቀበሉበት እንደነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ” እያሉ ያስቸኩሉአቸው ነበር። 14የፈርዖንም ሹሞች፥ “ቀድሞ ታደርጉት እንደ ነበራችሁ እንደ ትናንትናውና እንደ ትናንትና በስቲያው የተቈጠረውን ጡብ ዛሬስ ስለምን አትጨርሱም?” እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆች ይገርፉ ነበር።
15የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ “ለምን በአገልጋዮችህ እንዲህ ታደርጋለህ? ገለባ አይሰጡአቸውም፤ ጡቡንም ሥሩ ይሉአቸዋል፤ 16እነሆም፥ አገልጋዮችህ ይገረፋሉ፤ ይገፋሉም፤ ግፉም በአንተ ሕዝብ ላይ ነው” ብለው ጮኹ። 17እርሱ ግን፥ “እናንተ አርፋችኋል፤ ቦዝናችኋል፤ ስለዚህም፦ ‘እንሂድ ለእግዚአብሔርም እንሠዋ’ ትላላችሁ። 18አሁንም ሂዱ፤ ሥሩ፤ ገለባም አይሰጡአችሁም፤ የጡቡን ቍጥር ግን ታመጣላችሁ” አላቸው። 19የእስራኤልም ልጆች አለቆች ዕለት ዕለት ከምትሠሩት ከጡቡ ቍጥር ምንም አታጕድሉ ባሉአቸው ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ። 20ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን በፊታቸው ቆመው ተገናኙአቸው። 21እነርሱም፥ “በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት ሽታችንን አግምታችሁታልና፥ ይገድለንም ዘንድ ሰይፍን በእጁ ሰጥታችሁታልና እግዚአብሔር ይመልከታችሁ፤ ይፍረድባችሁም” አሉአቸው።
ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው አቤቱታ
22ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመለሰና፥ “ጌታ ሆይ፥ ስለምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ስለ ምንስ ላክኸኝ? 23በስምህ እናገር ዘንድ ወደ ፈርዖን ከገባሁ ወዲህ፥ ይህን ሕዝብ አስከፍቶታልና፤ አንተም ሕዝብህን ከቶ አላዳንኸውም” አለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 5: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ