ትንቢተ ሕዝቅኤል 10
10
የእግዚአብሔር ክብር ከቤተ መቅደስ እንደ ተነሣ
1እኔም አየሁ፤ እነሆም በኪሩቤል ራስ ላይ ባለው ጠፈር በላያቸው እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ ዙፋን የሚመስል መልክ ተገለጠ። 2በፍታም የለበሰውን ሰው፥ “በመንኰራኵሮች መካከል በኪሩብ በታች ግባ፤ ከኪሩቤልም መካከል ከአለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ፤ በከተማዪቱም ላይ በትነው” ብሎ ተናገረው። እኔም እያየሁ ገባ። 3ሰውየውም ሲገባ ኪሩቤል በቤቱ ቀኝ በኩል ቆመው ነበር፤ ደመናውም ውስጠኛውን አደባባይ ሞላ። 4የእግዚአብሔር ክብርም ከኪሩቤል ወጥቶ በቤቱ መድረክ ላይ ቆመ፤ ቤቱም በደመናው ተሞላ፤ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ፀዳል ተሞላ። 5የኪሩቤልም የክንፎቻቸው ድምፅ ሁሉን የሚችል አምላክ እንደሚናገረው ያለ ድምፅ እስከ ውጭው አደባባይ ድረስ በሩቅ ይሰማ ነበር። 6የተቀደሰ በፍታም የለበሰውን ሰው፥ “ከመንኰራኵሮቹ ከኪሩቤል መካከል እሳት ውሰድ” ብሎ በአዘዘው ጊዜ እርሱ ገብቶ በመንኰራኵር አጠገብ ቆመ። 7ከኪሩቤል መካከልም አንዱ ኪሩብ እጁን በኪሩቤል መካከል ወደ አለው እሳት ዘርግቶ ከዚያ እሳት ወሰደ፤ የተቀደሰ በፍታም በለበሰው ሰው እጅ አኖረው፤ እርሱም ይዞ ወጣ። 8ኪሩቤልንም አየሁ፤ ከክንፎቻቸውም በታች የሰው እጅ መሳይ አለ።
9እኔም አየሁ፤ እነሆም በኪሩቤል አጠገብ አራት መንኰራኵሮች ነበሩ፤ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ፥ አንዱ መንኰራኵር በአንዱ ኪሩብ አጠገብ ነበረ። የመንኰራኵሮቹም መልክ እንደ ቢረሌ ድንጋይ ነበረ። 10የአራቱም መልክ አንድ ይመስል ነበር፤ መልካቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንደ አለ መንኰራኵር ነበረ። 11ሲሔዱም በአራቱ ጎድናቸው ይሄዱ ነበር። ሲሄዱም ወዲያና ወዲህ አይሉም ነበር፤ መጀመሪያው ወደሚያመለክትበት ስፍራ ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም ወዲያና ወዲህ አይሉም ነበር። 12ገላቸውም ሁሉ፥ ጀርባቸውም፥ እጆቻቸውም፤ ክንፎቻቸውም፥ መንኰራኵሮቹም፤ ለአራቱ የነበሩ መንኰራኵሮች በዙሪያቸው ዐይኖች ተሞልተው ነበር። 13አራቱም መንኰራኵሮች እኔ እየሰማሁ ጌልጌል ተብለው ተጠሩ። 14ለእያንዳንዱም አራት አራት ፊት ነበሩት፤ አንደኛው ፊት የኪሩብ#“ገጸ ኪሩብ” የተባለ ገጸ ላሕም ነው። ፊት፥ ሁለተኛውም የሰው ፊት፥ ሦስተኛው የአንበሳ ፊት፥ አራተኛውም የንስር ፊት ነበረ።#ምዕ. 10 ቍ. 14 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
15እነዚህም በኮቦር ወንዝ በእንስሶች አምሳል ያየኋቸው ኪሩቤል በረሩ። 16ኪሩቤልም ሲሄዱ መንኰራኵሮቹ ከእነርሱ ጋር ተያይዘው ይሄዱ ነበር፤ ኪሩቤልም ይበሩ ዘንድ ክንፋቸውን ከምድር በሚያነሡ ጊዜ ከእነርሱ ጋር የተያያዘ መንኰራኵራቸው አይመለስም ነበር። 17የሕይወት መንፈስ በውስጣቸው ነበርና እነዚህ ሲቆሙ እነዚያም ይቆሙ ነበር፤ እነዚህም ሲበርሩ፥ እነዚያ ከእነርሱ ጋር ይበርሩ ነበር።
18የእግዚአብሔርም ክብር ከቤቱ መድረክ ላይ ወጥቶ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ። 19ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ዘረጉ፤ እኔም እያየሁ ከምድር በረሩ፤ በወጡም ጊዜ መንኰራኵሮቹ በአጠገባቸው ነበሩ፤ፊት ለፊት በአለው በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ በር ዳርቻ ቆሙ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር ከእነርሱ ጋራ በላያቸው ነበረ።
20ይህ በኮቦር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ በታች ያየሁት እንስሳ ነው፤ ኪሩቤልም እንደ ነበሩ ዐወቅሁ። 21ለእያንዳንዱ አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት፤ የሰውም እጅ አምሳያ ከክንፎቻቸው በታች ነበረ። 22ፊቶቻቸውም በኮቦር ወንዝ ከእስራኤል አምላክ ክብር በታች ያየኋቸውን ፊቶች ይመስሉ ነበር፤ እነርሱና መልካቸውም እንዲሁ ነበረ፤ እያንዳንዱም አቅንቶ ወደ ፊት ይሄድ ነበር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 10: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ