ትንቢተ ሕዝቅኤል 23
23
ሁለት አመንዝራ እኅትማማቾች
1የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ፥ የአንዲት እናት ልጆች የሆኑ ሁለት ሴቶች ነበሩ። 3በግብፅ ሀገር አመነዘሩ፤ በኮረዳነታቸው ሳሉ አመነዘሩ፤ በዚያም ጡቶቻቸው ወደቁ፤ በዚያም ድንግልናቸውን አጡ። 4ስማቸውም የታላቂቱ ሐላ የታናሽ እኅቷም ሐሊባ ነበረ፤ እኔም አገባኋቸው፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለዱ። ስማቸውም ሐላ ሰማርያ ናት፤ ሐሊባ ደግሞ ኢየሩሳሌም ናት።
5“ሐላም አመነዘረችብኝ፤ ወዳጆችዋንም የሚቀርቡአትን አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው። 6እነርሱም ሰማያዊ ሐር የለበሱ መሳፍንትና መኳንንት፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ በፈረስ ላይ የሚቀመጡ የተመረጡ ፈረሰኞች ነበሩ። 7ዝሙቷንም ከተመረጡ ከአሦር ሰዎች ሁሉ ጋር አደረገች፤ በፍቅር በተከተለቻቸውም ጣዖቶቻቸው ሁሉ ረከሰች። 8በግብፅም የነበረውን ዝሙቷን አልተወችም፤ በዚያም በኮረዳነቷ ጊዜ ከእርስዋ ጋር ተኝተው ነበር፤ የድንግልናዋንም ጡቶች ዳብሰው ነበር፤ ዝንየታቸውንም አፍስሰውባት ነበር። 9ስለዚህ በፍቅር በተከተለቻቸው በወዳጆችዋ በአሦራውያን እጆች አሳልፌ ሰጠኋት። 10እነርሱም ኀፍረተ ሥጋዋን ገለጡ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋንም ማርከው ወሰዱ፤ እርስዋንም በሰይፍ ገደሉ፤ በእርስዋና በሴቶች ልጆችዋ ላይ በቀልን ስላደረጉባቸው በሴቶች መካከል መተረቻ ሆነች።
11“እኅቷም ሐሊባ ይህን አየች፤ ሆኖም ከእርስዋ ይልቅ በፍቅር በመከተልዋ ረከሰች፤ ዝሙቷንም ከእኅቷ ዝሙት ይልቅ አበዛች። 12የሚቀርቡአትን መሳፍንቱንና መኳንንቱን ጌጠኛ ልብስ የለበሱትን፥ በፈረሶች ላይ የሚቀመጡትን ፈረሰኞች፥ ሁሉንም መልከ መልካሞችን ጐበዛዝት አሦራውያንን በፍቅር ተከተለቻቸው። 13እንደ ረከሱም አየሁ፤ ሁለቱም አንድ መንገድ ሄደዋል። 14ዳግመኛም ዝሙቷን አበዛች፤ በግንብ ላይ የተሣሉ የከለዳውያን ሰዎች ሥዕልንም አየሁ። 15#ዕብ. “ግልሙትናዋንም አበዛች ፤ በቀይ ቀለምም የተሳለችውን የከለዳውያንን ሥዕል ፤ በናስ ላይ የተሳሉትን ሰዎች አየች” ይላል።በጥቍር ቀለም የተሣሉ የከለዳውያንን መልክ አየሁ፤ በወገባቸው ዝናር የታጠቁ ናቸው፤ በራሳቸውም ላይ ጥልፍ ሰበን የጠመጠሙ ናቸው፤ ፊታቸውም ሦስት ወገን ነው፤ ሁሉም በትውልድ ሀገራቸው የሚኖሩ የባቢሎን ሰዎችን ከለዳውያንን ይመስላሉ። 16ዐይንዋንም ወደ እነርሱ አቅንታ አየቻቸው፤#ዕብ. “በአየቻቸውም ጊዜ በፍቅር ተከተለቻቸው” ይላል። ወደ ከላውዴዎንም ምድር ወደ እነርሱ መልእክተኞችን ላከች። 17የባቢሎንም ልጆች ወደ እርስዋ መጥተው በመኝታዋ ከእርስዋ ጋር ተኙ፤ በዝሙታቸውም አረከሱአት፤ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ረከሰች፤ ነፍስዋም ከእነርሱ ተለየች። 18ዝሙቷንም ገለጠች፤ ኀፍረተ ሥጋዋንም ገለጠች፤ ነፍሴም ከእኅቷ እንደ ተለየች እንዲሁ ነፍሴ ከእርስዋ ተለየች። 19ነገር ግን በግብፅ ምድር ያመነዘረሽበትን የወጣትነትሽን ዘመን አስበሽ ዝሙትሽን አበዛሽ። 20አካላቸውም እንደ አህዮች አካል፤ ዘራቸውም እንደ ፈረሶች ዘር የሆነውን እነዚያን የከለዳውያን ልጆች በፍቅር ተከተልሻቸው። 21ጡትሽ በአጐጠጐጠ ጊዜ በማደሪያሽ በግብፅ ሀገር የሠራሽውን የወጣትነትሽን ኀጢአት አሰብሽ።”
22ስለዚህ ሐሊባ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ነፍስሽ ከእነርሱ የተለየች ወዳጆችሽን አስነሣብሻለሁ፤ በዙሪያሽም በአንቺ ላይ አመጣቸዋለሁ። 23እነርሱም የባቢሎን ልጆች፥ ከለዳውያንም ሁሉ፥ ፋቁድ፥ ሱሔ፥ ቆዓ፥ ከእነርሱም ጋር አሦራውያን ሁሉ፥ መልከ መልካሞች ጐበዛዝት፥ መሳፍንትና መኳንንት ሁሉ፥ መሳፍንትና አማካሪዎች ሁሉ፥ በሦስት ወገን በፈረስ ላይ የተቀመጡ ናቸው። 24ስማቸውን ያስጠሩ ሰዎች ሁሉ በመንኰራኵርና በሠረገላ፥ በአሕዛብም ጉባኤ ይመጡብሻል፤ ጋሻና አላባሽ ጋሻ፥ ራስ ቍርም ይዘው በዙሪያሽ ጥበቃ ያደርጋሉ፤ ፍርድንም እሰጣቸዋለሁ፤ እንደ ፍርዳቸውም ይፈርዱብሻል። 25ቅንአቴንም በአንቺ ላይ አደርጋለሁ፤ በመዓትም ያደርጉብሻል፤ አፍንጫሽንና ጆሮሽንም ከአንቺ ይቈርጣሉ፤ ከአንቺም የቀረ በሰይፍ ይወድቃል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽንም ማርከው ይወስዳሉ፤ ከአንቺም የቀሩትን እሳት ትበላቸዋለች። 26ልብስሽንም ይገፍፉሻል፤ የክብርሽንም ጌጥ ይወስዳሉ። 27ሴሰኝነትሽንም፥ ከግብፅ ምድር ያወጣሽውን ዝሙትሽንም ከአንቺ አስቀራለሁ፤ ዐይንሽንም ከእንግዲህ ወዲህ ወደ እነርሱ አታነሺም፤ ግብፅንም ከዚያ ወዲያ አታስቢም። 28ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በጠላሻቸው እጅ፥ ነፍስሽም በተለየቻቸው እጅ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ 29እነርሱም በጥል ያደርጉብሻል፤ የደከምሽበትንም ሁሉ ይወስዳሉ፤ ዕራቁትሽንና ዕርቃንሽን አድርገውም ይተዉሻል፤ የግልሙትናሽንም ነውር፥ ሴሰኝነትሽንና ግልሙትናሽንም ሁሉ ይገልጣሉ። 30ከአሕዝብ ጋር ስላመነዘርሽ፤ በበደላቸውም#ዕብ. “በጣዖታቸው” ይላል። ስለ ረከስሽ ይህን ያደርጉብሻል። 31በእኅትሽ መንገድ ሄደሻል፤ ስለዚህ ጽዋዋን በእጅሽ እሰጥሻለሁ። 32ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የጠለቀውንና የሰፋውን፥ ብዙም የሚይዘውን የእኅትሽን ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ ብዙ መጠጥን በሚጠጡ ሰዎችም ዘንድ#“ብዙ መጠጥን በሚጠጡ ሰዎች ዘንድ” የሚለው በዕብ. የለም። መሳቂያና መሳለቂያ ትሆኛለሽ። 33በእኅትሽ በሰማርያ ጽዋ፥ በድንጋጤና በጥፋት ጽዋ፥ በስካርና በውርደት ትሞሊያለሽ። 34ትጠጪዋለሽ፥ ትጨልጪውማለሽ፤ በዓላትሽንና መባቻዎችሽን እሽራለሁ፤#ዕብ. “ገሉንም ታኝኪዋለሽ ፤ ጡትሽንም ትሸነትሪዋለሽ” ይላል። እኔ ተናግሬአለሁና ይላል እግዚአብሔር። 35ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዘንግተሽኛልና፥ ወደ ኋላሽም ጥለሽኛልና አንቺ ደግሞ ሴሰኝነትሽንና ኀጢአትሽን ተሸከሚ።”
36እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ሐላንና ሐሊባን ተፋረዳቸው፤ ኀጢአታቸውንም አስታውቃቸው፤ 37አመንዝረዋልና፥ ደምም በእጃቸው አለና፥ ዝሙታቸውንም ወድደዋልና፥#ዕብ. “ከጣዖቶቻቸው ጋር አመንዝረዋል” ይላል። ለእኔም የወለዱአቸውን ልጆቻቸውን መብል እንዲሆኑላቸው በእሳት አሳልፈዋቸዋልና። 38ይህን ደግሞ አድርገውብኛል፤ በዚያ ቀን መቅደሴን አርክሰዋል፤ ሰንበታቴንም ሽረዋል። 39ልጆቻቸውንም ለጣዖቶቻቸው በሠዉ ጊዜ ፥ በዚያው ቀን ያረክሱት ዘንድ ወደ መቅደሴ ገቡ፤ እነሆም በቤቴ ውስጥ እንደዚህ አደረጉ። 40ከሩቅ ሀገርም ወደመጡ ሰዎች መልእክተኞችን ላኩ፤ እነርሱም በደረሱ ጊዜ ይታጠባሉ፤ ዐይኖቻቸውንም ይኳላሉ፤ ያጌጣሉም። 41በክብር አልጋ ላይ ይቀመጣሉ፤ በፊት ለፊታቸውም ማዕድ ተዘጋጅታ ነበር፤ በዕጣኔና በዘይቴም ደስ ይላቸዋል። 42የበገናውን አውታር ድምፅ ይቃኛሉ፤ ከብዙ ሰዎችም ጉባኤ ጋር ሰካራሞቹ ከምድረ በዳ መጡ፤ በእጃቸው አንባር፥ በራሳቸውም የተዋበ አክሊል አደረጉ። 43እኔም፦#ዕብ. “በምንዝር ላረጀችው” የሚል ይጨምራል። ‘አሁን ከእርስዋ ጋር ያመነዝራሉ፤ እርስዋም ከእነርሱ ጋር ታመነዝራለች፤’ አልሁ። 44ወደ ጋለሞታ እንደሚገቡም ወደ እርስዋ ገቡ፤ እንዲሁ ይሰስኑ ዘንድ ወደ ሐላና ወደ ሐሊባ ገቡ። 45ሴቶቹ አመንዝሮች ናቸውና፥ በእጃቸውም ደም አለና ጻድቃን ሰዎች በአመንዝሮቹና በደም አፍሳሾቹ ሴቶች ላይ በሚፈረደው ፍርድ ይፈርዱባቸዋል።”
46ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ጉባኤን አመጣባቸዋለሁ፤ ለመበተንና ለመበዝበዝም አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። 47ጉባኤውም በድንጋይ ይወግሩአቸዋል፤ በሰይፋቸውም ይቈርጡአቸዋል፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም ይገድላሉ፤ ቤቶቻቸውንም በእሳት ያቃጥላሉ። 48ሴቶችም ሁሉ እንደ ኀጢአታችሁ እንዳይሠሩ ይማሩ ዘንድ ሴሰኝነትን ከምድር ላይ አጠፋለሁ። 49እንግዲህ በደላችሁ በላያችሁ ላይ ይመለሳል፤ እናንተም የጣዖቶቻችሁን ኀጢአት ትሸከማላችሁ፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 23: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ