ትንቢተ ሕዝቅኤል 39
39
የጎግ መሸነፍ
1“አንተም የሰው ልጅ ሆይ! በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሮስ የሞሣሕና የቶቤል አለቃ ጎግ ሆይ! እነሆ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤ 2እሰበስብሃለሁ፤ እመራሃለሁ፤ ከሰሜንም ዳርቻ አወጣሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች እወስድሃለሁ። 3ከግራ እጅህም ቀስትህን አስጥልሃለሁ፤ ከቀኝ እጅህም ፍላጾችህን አስረግፍሃለሁ፤#“አስረግፍሃለሁ” የሚለው በዕብ. ብቻ። በእስራኤልም ተራሮች ላይ እጥልሃለሁ። 4አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ፥ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ በምድረ በዳ ፊት ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ#“ለሚናጠቁ” የሚለው በዕብ. ብቻ። ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። 5አንተ በሜዳ ፊት ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 6በማጎግም ላይ፥ በሰላምም በደሴቶች በሚቀመጡ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቃል፤ ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላረክስም፤ አሕዛብም የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር፥ እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 8እነሆ ይመጣል፤ እንደሚሆንም ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያልሁት ቀን ይህ ነው። 9በእስራኤልም ከተሞች የሚኖሩ ይወጣሉ፤ የጦር መሣሪያዎችንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ አላባሽ አግሬ ጋሻንና ጋሻን፥ ቀስትንና ፍላጻዎችን፥ የእጅ በትሮችንና ጦርንም ያቃጥላሉ፤ ሰባት ዓመት በእሳት ያቃጥሉአቸዋል። 10እንጨትን ከሜዳ አይወስዱም፤ ከዱርም አይቈርጡም፤ ነገር ግን የጦር መሣሪያን በእሳት ያነድዳሉ፤ የገፈፉአቸውንም ይገፍፋሉ፤ የበዘበዙአቸውንም ይበዘብዛሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የጎግ መቃብር
11“በዚያም ቀን በእስራኤል ዘንድ በባሕር ምሥራቅ የሚያልፉበትን ሸለቆ፥ የመቃብርን ስፍራ ለጎግ እሰጣለሁ፤ የሚያልፉትንም ይከለክላል፤ በዚያም ጎግንና ሠራዊቱን ሁሉ ይቀብራሉ፤ የሸለቆውንም ስም የጎግ መቃብር ብለው ይጠሩታል። 12ምድርንም ያነደዱ የእስራኤል ወገኖች ሰባት ወር መቃብር እየቈፈሩ ይቀብሯቸዋል፤ 13የምድሩም ሕዝብ ሁሉ ይቀብሯቸዋል፤ እኔም በምመሰገንበት ቀን ለክብር ይሆንላቸዋል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 14ምድርንም ለማጽዳት በምድሩ ላይ ወድቀው የቀሩትን የሚቀብሩ፥ ዘወትር በምድሩ ላይ የሚዞሩትን ሰዎች ይቀጥራሉ፤ ከሰባት ወርም በኋላ ይመረምራሉ። 15በምድርም የሚዞሩት ያልፋሉ፤ የሰውንም አጥንት ቢያዩ፥ ቀባሪዎች በጎግ መቃብር ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ ምልክት ያኖሩበታል። 16ደግሞም የከተማዪቱ ስም የመቃብር ቦታ ይባላል። እንዲሁ ምድሪቱን ያጸዳሉ።
17“አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሚበርሩ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ ኑ፤ ተከማቹ፤ ሥጋንም ትበሉ ዘንድ፥ ደምንም ትጠጡ ዘንድ በእስራኤል ተራሮች ላይ ወደማርድላችሁ መሥዋዕት፥ እርሱም ታላቅ መሥዋዕት፥ ከየሰፍራው ሁሉ ተሰብሰቡ። 18የኀያላኑን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድርንም አለቆች፥ የአውራ ፍየሎችንና የአውራ በጎችን፥ የወይፈኖችንና፥ የባሳንን#“የባሳንን” የሚለው በዕብ. ብቻ። ፍሪዳዎች ሁሉ፥ ደም ትጠጣላችሁ። 19እኔም ከማርድላችሁ መሥዋዕት እስክትጠግቡ ድረስ ጮማን ትበላላችሁ፤ እስክትሰክሩም ድረስ ደምን ትጠጣላችሁ። 20ከማዕዴም ከፈረሶችና ከፈረሰኞች፥ ከኀያላንና ከሰልፈኞች ሁሉ ሥጋን ትጠግባላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የእስራኤል እንደ ገና መቋቋም
21“ክብሬንም እሰጣችኋለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ ያደረግሁትን ፍርዴን፥ በላያቸውም ያኖርኋትን እጄን ያያሉ። 22ከዚች ቀን ጀምሮ ለዘለዓለም የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 23አሕዛብም የእስራኤል ቤት በኀጢአታቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ ያውቃሉ፤ ስለ ከዱኝ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ስለ መለስሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ እነርሱም ሁሉ በሰይፍ ወደቁ። 24እንደ ርኵሰታቸውም እንደ መተላለፋቸውም መጠን አደረግሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ መለስሁ።
25“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። 26በምድራቸው ተዘልለው በተቀመጡ ጊዜ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ሁሉ ይሸከማሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም። 27ከአሕዛብም ዘንድ በመለስኋቸው ጊዜ፥ ከአሕዛብም ሀገሮች በሰበሰብኋቸው ጊዜ፥ በብዙ አሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ 28እኔም ወደ አሕዛብ አስማርኬአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አላስቀርም፤ 29ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልመልስም፤ መዓቴን#ዕብ. “መንፈሴን” ይላል። በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 39: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ