ትንቢተ ሕዝቅኤል 8
8
አምልኮ ባዕድ በኢየሩሳሌም
1እንዲህም ሆነ፤ በስድስተኛው ዓመት በስድስተኛው ወር#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በአምስተኛው ወር” ይላል። ከወሩም በአምስተኛው ቀን በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ፥ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፥ በዚያ የጌታ የእግዚአብሔር እጅ በላዬ መጣ። 2እኔም አየሁ፤ እነሆም ከወገቡ በታች እንደ እሳት የሚመስል የሰው አምሳያ ነበረ፤ ከወገቡም ወደ ላይ እንደ ፀዳል ምሳሌ፥ እንደሚያንጸባርቅ አይነት ነበረ። 3እጅ መሳይንም ዘረጋ፤ በራስ ጠጕሬም ያዘኝ፤ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፤ በእግዚአብሔርም ራእይ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ወደ ውስጠኛው አደባባይ በር መግቢያ ቅንአት የተባለው ምስል ወደ አለበት አመጣኝ፤ 4እነሆም ቀድሞ በሜዳ እንደ አየሁት ራእይ የእስራኤል አምላክ ክብር በዚያ ነበረ።
5እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ዐይንህን ወደ ሰሜን መንገድ አንሣ” አለኝ። ዐይኔንም ወደ ሰሜን መንገድ አነሣሁ፤ እነሆም በመሠዊያው በር በሰሜን በኩል በመግቢያው ይህ የቅንዓት ምስል ነበረ። ከዚያም ወደ ምሥራቅ ያስገባል።#“ወደ ምሥራቅ ያስገባል” የሚለው በዕብ. የለም። 6እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! የሚያደርጉትን ከመቅደሴ ያርቁኝ ዘንድ የእስራኤል ቤት በዚህ የሚያደርጉትን፥ ታላቁን ርኵሰት ታያለህን? ደግሞም ተመልሰህ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ርኵሰት ታያለህ” አለኝ።
7ወደ አደባባዩም መግቢያ አስገባኝ፤ በአየሁም ጊዜ፥ እነሆ በግንቡ ውስጥ ፉካ ነበረ።#“አስገባኝ ፤ ባየሁህም ጊዜ እነሆ በግንቡ ውስጥ ፉካ ነበረ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 8እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ግንቡን ንደለው” አለኝ፤ ግንቡንም በነደልሁት ጊዜ ደጃፍ አገኘሁ። 9እርሱም፥ “ግባ፤ በዚህ የሚያደርጉትን ክፉውን ርኵሰት እይ” አለኝ። 10እኔም ገባሁና፥ እነሆ በግንቡ ዙሪያ ላይ የተንቀሳቃሾች አዕዋፍና እንስሳትን ምሳሌ ከንቱና ርኩስ የእስራኤልንም ቤት ጣዖታት ሁሉ ተሥለው አየሁ። 11በፊታቸውም ከእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች ሰባ ሰዎችና የሳፋን ልጅ ያእዛንያ ቆመው ነበር፤ ሰውም ሁሉ እያንዳንዱ በእጁ ጥናውን ይዞ ነበር፥ የዕጣኑም ጢስ ሽታ ይወጣ ነበር። 12እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች በስውር#ዕብ. “በጨለማ” ይላል። እያንዳንዱ በሥዕሉ ቤት የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱ እግዚአብሔር አያየንም፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል ይላሉና” አለኝ። 13እርሱም፥ “ከዚያ የበለጠውን የሚያደርጉትን ታላቅ ኀጢአት ታይ ዘንድ ና” አለኝ።
14ወደ ሰሜንም ወደሚመለከተው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር አመጣኝ፤ እነሆም፥ ሴቶች ለተሙዝ#“ተሙዝ” የጣዖት ስም ነው። እያለቀሱ በዚያ ተቀምጠው ነበር። 15እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን አይተሃልን? ደግሞ ከዚህ የበለጠ ርኵሰት ታያለህ” አለኝ።
16ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ እነሆም በእግዚአብሔር መቅደስ መግቢያ ፊት በወለሉና በመሠዊያው መካከል ሃያ አምስት የሚያህሉ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሃያ” ይላል። ሰዎች ነበሩ፤ ጀርባቸውም ወደ እግዚአብሔር መቅደስ፥ ፊታቸውም ወደ ምሥራቅ ነበረ፤ እነርሱም ወደ ምሥራቅ ለፀሐይ ይሰግዱ ነበር። 17እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን አይተሃልን? በዚህ የሚያደርጉትን ይህን ኀጢአት ያደርጉ ዘንድ ለይሁዳ ቤት ጥቂት ነገር ነውን? ምድሪቱን በኀጢአት ሞልተዋታል፤ ያስቈጡኝም ዘንድ ተመልሰዋል፤ እነሆም ቅርንጫፉን አስረዝመዋል። ይዘባበታሉም። 18ስለዚህ እኔ ደግሞ በመዓት እሠራለሁ፤ ዐይኔ አይራራም፤ እኔም ይቅርታ አላደርግም፤ ወደ ጆሮዬም በታላቅ ድምፅ ቢጮኹ አልሰማቸውም” አለኝ።#ወደ ጆሮዬም በታላቅ ድምፅ ቢጮኹ አልሰማቸውም አለኝ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 8: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ