ኦሪት ዘፍጥረት 26
26
ይስሐቅ ወደ ጌራራ መሄዱ
1በምድርም ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከሆነው ራብ ሌላ ራብ ሆነ፤ ይስሐቅም ወደ ፍልስጥኤም ንጉሥ ወደ አቤሜሌክ ወደ ጌራራ ሄደ። 2እግዚአብሔርም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥ “ወደ ግብፅ አትውረድ፤ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ። 3በዚህች ምድር ተቀመጥ፤ ከአንተ ጋርም እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህችን ምድር ሁሉ ለአንተም፥ ለዘርህም እሰጣለሁና፥ ለአባትህም ለአብርሃም የማልሁለትን መሐላ ከአንተ ጋር አጸናለሁ። 4ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ይህችንም ምድር ሁሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፤ 5አባትህ አብርሃም ቃሌን ሰምቶአልና፤ ትእዛዜንና ፍርዴን፥ ሥርዐቴንና ሕጌንም ጠብቆአልና።” 6ይስሐቅም በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም ስፍራ ሰዎች ስለ ሚስቱ ስለ ርብቃ ጠየቁት፤ እርሱም፥ “እኅቴ ናት” አላቸው፤ 7የዚህ ስፍራ ሰዎች ለርብቃ ሲሉ እንዳይገድሉኝ ብሎ ሚስቴ ናት ማለትን ፈርቶአልና፤ እርስዋም ውብ ነበረችና። 8በዚያም ብዙ ቀን ተቀመጠ። የፍልስጥኤም ንጉሥ አቤሜሌክም በመስኮት ሆኖ በተመለከተ ጊዜ ይስሐቅን ከሚስቱ ከርብቃ ጋር ሲጫወት አየው። 9አቤሜሌክም ይስሐቅን ጠራ፤ እንዲህም አለው፥ “እነሆ፥ ሚስትህ ናት፤ እንዴትስ እርስዋን፦ ‘እኅቴ ናት’ አልህ?” ይስሐቅም፥ “በእርስዋ ምክንያት እንዳልሞት ብዬ ነው” አለው። 10አቤሜሌክም አለ፥ “ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው? ከሕዝቡ አንዱ ባለማወቅ ከሚስትህ ጋር ሊተኛ ጥቂት በቀረው ነበር፤ ኀጢአትንም ልታመጣብን ነበር።” 11አቤሜሌክም ሕዝቡን ሁሉ፥ “ይህን ሰው፥ ሚስቱንም የሚነካ ፍርዱ ክፉ ሞት ነው” ብሎ አዘዘ።
12ይስሐቅም በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፤ በዚያች ዓመትም መቶ እጥፍ ገብስ አገኘ፤ እግዚአብሔርም ባረከው። 13ከፍ ከፍም አለ፤ እጅግም ታላቅ እስኪሆን ድረስ እየጨመረ ይበዛ ነበር፤ 14ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን፥ ብዙ በጎችንና ላሞችን፥ የእርሻ መሬትንም ገዛ፤ የፍልስጥኤም ሰዎችም ቀኑበት። 15በአባቱ በአብርሃም ዘመን የአባቱ ሎሌዎች የማሱአቸውን ጕድጓዶች ሁሉ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፈኑአቸው፤ አፈርንም ሞሉባቸው። 16አቤሜሌክም ይስሐቅን፥ “ከእኛ ተለይተህ ሂድ፤ ከእኛ ይልቅ እጅግ በርትተሃልና” አለው። 17ይስሐቅም ከዚያ ሄደ፤ በጌራራም ሸለቆ ሰፈረ፤ በዚያም ተቀመጠ።
18ይስሐቅም የአባቱ የአብርሃም አገልጋዮች ቈፍረዋቸው የነበሩትን የውኃ ጕድጓዶች ደግሞ አስቈፈረ፤ አባቱ አብርሃም ከሞተ በኋላ የፍልስጥኤም ሰዎች ደፍነዋቸው ነበርና፤ አባቱም አብርሃም ይጠራቸው በነበረው ስም ጠራቸው። 19የይስሐቅ ሎሌዎችም በጌራራ ሸለቆ ውስጥ ጕድጓድ ቈፈሩ፤ በዚያም ጣፋጭ የውኃ ምንጭ አገኙ። 20የጌራራ እረኞች ከይስሐቅ እረኞች ጋር፥ “ውኃው የእኛ ነው” ሲሉ ተጣሉ፤ የዚያችንም ጕድጓድ ስም “ዐዘቅተ ዐመፃ” ብሎ ጠራት፤ እነርሱ በድለውታልና። 21ይስሐቅም ከዚያ ሄደ በዚያም ሌላ ጕድጓድ ማሰ፥ ስለ እርስዋም ደግሞ ተጣሉት፤ ስምዋንም “ጽልእ” ብሎ ጠራት። 22ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ስለ እርስዋም አልተጣሉትም፤ ስምዋንም “መርኅብ” ብሎ ጠራት፤ እንዲህ ሲል፥ “አሁን እግዚአብሔር አሰፋልን፤ በምድርም አበዛን።”
23ከዚያም ወደ ዐዘቅተ መሐላ ሄደ። 24በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፥ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ አትፍራ፤ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አባትህ ስለ አብርሃም ዘርህን አበዛዋለሁ።” 25በዚያም ለአምላኩ ለእግዚአብሔር መሠውያን ሠራ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ጠራ፤ በዚያም ድንኳን ተከለ፤ የይስሐቅም ሎሌዎች በዚያ ጕድጓድ ማሱ።
በይስሐቅና በአቤሜሌክ መካከል የተደረገ ስምምነት
26አቤሜሌክና ሚዜው አኮዘት፥ የሠራዊቱም አለቃ ፋኮል ከጌራራ ወደ እርሱ ሄዱ። 27ይስሐቅም፥ “ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? እናንተ ጠልታችሁኛል፤ ከእናንተም ለይታችሁ አሳድዳችሁኛልና” አላቸው። 28እነርሱም አሉት፥ “እኛ የጠላንህ አይደለም፤ በመልካም አኑረን፥ በመልካም አሰናበትንህ እንጂ፥ አሁንም አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቡሩክ ነህ። 29አምላክህ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር እንደ አለ በአየን ጊዜ በአንተና በእኛ መካከል መሐላ ይሁን፤ አንተ በእኛ ላይ ክፉ እንዳታደርግ፤ እኛም በአንተ ላይ ክፉ እንዳናደርግ እንማማላለን።” 30ይስሐቅም ማዕድ አቀረበላቸው፤ በሉም፤ ጠጡም። 31ማልደውም ተነሡ፤ እርስ በርሳቸውም ተማማሉ፤ ይስሐቅም አሰናበታቸው፤ ከእርሱም በደኅና ሄዱ። 32በዚያም ቀን የይስሐቅ ሎሌዎች መጡ፤ ስለ ቈፈሩአትም ጕድጓድ፥ ውኃ አገኘን ብለው ነገሩት። 33ስምዋንም “መሐላ” ብሎ ጠራት፤ ስለዚህም የከተማዪቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ “ዐዘቅተ መሐላ” ይባላል።
ዔሳው ከከነዓን ሚስቶችን እንደ አገባ
34ዔሳውም አርባ ዓመት ሲሆነው የኬጢያዊው የብኤልን ልጅ ዮዲትን፥ የኬጢያዊው የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትንም ሚስቶች አድርጎ አገባ፤ 35እነርሱም ይስሐቅንና ርብቃን ያሳዝኑ ነበር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 26: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ