ኦሪት ዘፍጥረት 27
27
ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ ባረከ
1እንዲህም ሆነ፦ ይስሐቅ ፈጽሞ ከአረጀ በኋላ ዐይኖቹ ፈዝዘው አያይም ነበር። ታላቁን ልጁን ዔሳውንም ጠርቶ፥ “ልጄ ሆይ፥” አለው፤ እርሱም፥ “እነሆ አለሁ” አለው። 2እርሱም አለው፥ “እነሆ እኔ አረጀሁ፤ የምሞትበትን ቀን አላውቅም። 3አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፤ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፤ አደንም አድንልኝ፤ 4ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ እኔ እንደምወደው መብል አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ።”
5ርብቃም ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው እንደዚህ ሲነግር ትሰማ ነበር። ዔሳውም ለአባቱ አደን ሊያድን ወደ ምድረ በዳ ሄደ። 6ርብቃም ታናሹ ልጅዋን ያዕቆብን እንዲህ አለችው፦ 7“እነሆ፥ አባትህ ለወንድምህ ለዔሳው፦ እንዲህ ሲለው ሰማሁ፤ ‘ሂድና ከአደንኸው መብል አዘጋጅተህ አምጣልኝ፤ ሳልሞትም በልች በእግዚአብሔር ፊት ልባርክህ።’ 8አሁንም ልጄ ሆይ፥ እኔ እንደማዝዝህ ስማኝ፤ 9ወደ በጎቻችን ሄደህ ሁለት መልካም ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እነርሱንም ለአባትህ እንደሚወደው መብል አደርጋቸዋለሁ፤ 10ለአባትህም ሳይሞት እንዲባርክህ፥ ይበላ ዘንድ ትወስድለታለህ።” 11ያዕቆብም እናቱን ርብቃን፥ “እነሆ ዔሳው ወንድሜ ጠጕራም ሰው ነው፥ እኔ ግን ለስላሳ ነኝ፤ 12ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደምንቀው እሆናለሁ፤ መርገምን በላዬ አመጣለሁ፤ በረከትንም አይደለም።” 13እናቱም አለችው፥ “ልጄ ሆይ፥ መርገምህ በእኔ ላይ ይሁን፥ ቃሌን ብቻ ስማኝ፤ ሂድና ያልሁህን አምጣልኝ።” 14ሄዶም አመጣ፤ ለእናቱም ሰጣት፤ እናቱም መብልን አባቱ እንደሚወድደው አደረገች። 15ርብቃም ከእርስዋ ዘንድ በቤት የነበረውን የታላቁን ልጅዋን የዔሳውን መልካሙን ልብስ አመጣች፤ ለታናሹ ልጅዋ ለያዕቆብም አለበሰችው፤ 16የጠቦቶችንም ለምድ በእጆቹና በለስላሳው አንገቱ ላይ አደረገች፤ 17ያን የሠራችውን መብልና እንጀራውን ለልጅዋ ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው።
18ወደ አባቱም አግብቶ፥ “አባቴ ሆይ፥” አለው፦ እርሱም፥ “እነሆኝ፤ ልጄ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ?” አለ። 19ያዕቆብም አባቱን አለው፥ “የበኵር ልጅህ እኔ ዔሳው ነኝ፤ እንዳዘዝኸኝ አደረግሁ፤ ነፍስህ ትባርከኝ ዘንድ ቀና ብለህ ተቀመጥ፤ ካደንሁትም ብላ።” 20ይስሐቅም ልጁን፥ “ልጄ ሆይ፥ ፈጥነህ ያገኘኸው ይህ ምንድን ነው?” አለው። እርሱም፥ “አምላክህ እግዚአብሔር በፊቴ የሰጠኝ ነው” አለ። 21ይስሐቅም ያዕቆብን፥ “ልጄ ሆይ፥ አንተ ልጄ ዔሳው እንደ ሆንህ ወይም እንዳልሆንህ ቅረበኝና ልዳስስህ” አለው። 22ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቀረበ፤ ዳሰሰውም፤ እንዲህም አለው፥ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፥ እጆች ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለው። 23እርሱም አላወቀውም ነበር፤ እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ነበሩና፤ ይስሐቅም ባረከው ። 24አለውም፥ “አንተ ልጄ ዔሳው ነህን?” እርሱም፥ “እኔ ነኝ” አለ። 25እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ ከአደንኸው እንድበላና ነፍሴ እንድትባርክህ አምጣልኝ” አለው። አቀረበለትም፤ በላም፤ ወይንም አመጣለት፤ እርሱም ጠጣ። 26አባቱ ይስሐቅም፥ “ልጄ ሆይ፥ ወደ እኔ ቅረብ፤ ሳመኝም” አለው። 27ወደ እርሱም ቀረበ፤ ሳመውም፤ የልብሱንም ሽታ አሸተተ፤ ባረከውም፤ እንዲህም አለ፥ “የልጄ ሽታ እግዚአብሔር እንደ ባረከው የእርሻ ሽታ ነው፤ 28እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል፥ ከምድርም ስብ፥ የእህልንም፥ የወይንንም፥ የዘይትንም ብዛት ይስጥህ፤ 29አሕዛብ ይገዙልህ፤ አለቆችም ይስገዱልህ፤ ለወንድምህ ጌታ ሁን፤ የአባትህም#ዕብ. “የእናትህ” ይላል። ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን፤ የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን።”
ዔሳው ከይስሐቅ በረከትን መለመኑ
30ይስሐቅም ያዕቆብን ባርኮ ከፈጸመ በኋላ፥ ያዕቆብ ከአባቱ ከይስሐቅ ፊት ወጣ፥ ወንድሙ ዔሳውም ከአደኑ መጣ፤ 31እርሱም ደግሞ መብል አዘጋጀ፥ ለአባቱም አመጣ፤ አባቱንም፥ “አባቴ ተነሥ፤ ነፍስህም ትባርከኝ ዘንድ ልጅህ ከአደነው ብላ” አለው። 32አባቱ ይስሐቅም፥ “አንተ ማን ነህ?” አለው። እርሱም፥ “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው። 33ይስሐቅም እጅግ ደነገጠ፤ እንዲህም አለ፥ “ያደነውን አደን ወደ እኔ ያመጣው ማን ነው? አንተ ሳትመጣም ከሁሉ በላሁ፤ ባረክሁትም፤ እርሱም የተባረከ ነው።” 34ዔሳውም የአባቱን ቃል በሰማ ጊዜ ታላቅ፥ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ፤ አባቱንም፥ “አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ” አለው። 35ይስሐቅም ዔሳውን አለው፥ “ወንድምህ በተንኰል መጥቶ በረከትህን ወሰደብህ።” 36ዔሳውም አለ፥ “በእውነት ስሙ ያዕቆብ ተባለ፤ ሁለት ጊዜ አሰናክሎኛልና፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደ፤ አሁንም እነሆ በረከቴን ወሰደ።” ዔሳውም አባቱን አለው፥ “ደግሞም አባቴ ሆይ፥ ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን?” 37ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው፥ “እነሆ ጌታህ አደረግሁት፤ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች አደረግኋቸው፤ እህሉን፥ ወይኑንና ዘይቱንም አበዛሁለት፤ ለአንተ ግን፥ ልጄ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ?” 38ዔሳውም አባቱን ይስሐቅን አለው፥ “አባቴ ሆይ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን? አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ።” ዔሳውም ጮሆ አለቀሰ። 39አባቱ ይስሐቅም መለሰ፤ አለውም፥ “እነሆ መኖሪያህ ከላይ ከሰማይ ጠል፥ ከምድርም ስብ ይሁን፤ 40በሰይፍህም ትኖራለህ፤ ለወንድምህም ትገዛለህ፤ ነገር ግን ቀንበሩን ከአንገትህ ልትጥል ብትወድድ ከእርሱ ጋር ተስማማ።”#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “በተቃወምኸው ጊዜ ቀንበሩን ከአንገትህ ትጥላለህ” ይላል።
41ዔሳውም አባቱ ስለ ባረከው በያዕቆብ ቂም ያዘበት፤ ዔሳውም በልቡ አለ፥ “ለአባቴ የልቅሶ ቀን ትቅረብ፤ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ።” 42ለርብቃም ታላቁ ልጅዋ ዔሳው ያለው ተነገራት፤ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም ልካ ጠራችው፤ አለችውም፥ “እነሆ ወንድምህ ዔሳው ያድድንሃል፤ ሊገድልህም ይፈልጋል። 43አሁንም ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ስማ፤ ተነሣና በሶርያ ወንዞች መካከል ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ፤ 44በእርሱም ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ። የወንድምህ ቍጣ ከአንተ እስኪበርድ ድረስ፥ 45ያደረግህበትንም እስኪረሳው ድረስ፤ በአንድ ቀን ሁለታችሁን እንዳላጣ፥ ከዚያም ልኬ አመጣሃለሁ።”
ይስሐቅ ያዕቆብን ወደ ላባ መላኩ
46ርብቃም ይስሐቅን አለችው፥ “ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሣ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ከዚህ ሀገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለእኔ ምኔ ነው?”
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 27: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ