ኦሪት ዘፍጥረት 28
28
1ይስሐቅም ያዕቆብን ጠራው፤ ባረከውም፥ እንዲህም ብሎ አዘዘው፥ “ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ፤ 2ተነሣና ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሂድ፤ ከዚያም ከእናትህ ከርብቃ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስትን አግባ። 3አምላኬ#ዕብ. “ሁሉን የሚችል አምላክ” ይላል። ከአንተ ጋር ይሂድ፤ ከፍ ከፍም ያድርግህ፤ ይባርክህ፤ ያብዛህ፤ ብዙ ሕዝብም ሁን ፤ 4ስደተኛ ሆነህ የተቀመጥህባትን፥ እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጣትን ምድር ትወርስ ዘንድ የአባቴን የአብርሃምን በረከት ለአንተ ይስጥህ፤ ከአንተም በኋላ ለዘርህ።” 5ይስሐቅም ልጁ ያዕቆብን ላከው፤ እርሱም የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም የሚሆን የሶርያዊው ባቱኤል ልጅ ላባ ወዳለበት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሄደ።
ዔሳው ሌላ ሚስት ማግባቱ
6ዔሳውም ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ ባረከው በአየ ጊዜ ከዚያም ሚስትን ያገባ ዘንድ ወደ ሁለቱ የሶርያ ወንዞች መካከል እንደ ላከው፥ በባረከውም ጊዜ፥ “ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ” ብሎ እንዳዘዘው፥ 7ያዕቆብም የአባቱንና የእናቱን ቃል ሰምቶ ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል እንደ ሄደ፥ 8የከነዓናውያንም ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ፊት የተጠሉ እንደ ሆኑ ዔሳው በአየ ጊዜ፥ 9ዔሳው ወደ ይስማኤል ሄደ፤ ቤሴሞትንም በፊት ካሉ ሚስቶቹ ጋር ሚስት ትሆነው ዘንድ ወሰዳት፤ እርስዋም የናኮር ወንድም የአብርሃም ልጅ የሆነው የይስማኤል ልጅና የናቡዓት እኅት ናት።
ያዕቆብ በቤቴል ያየው ሕልም
10ያዕቆብም ከአዘቅተ መሐላ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። 11ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፤ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና በዚያ አደረ፤ ከዚያም ስፍራ ድንጋዮች አንድ ድንጋይ አነሣ፤ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ። 12ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል#ግእዙ “ሰዋስወ ወርቅ” ይላል። በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበትና ይወርዱበት ነበር። 13እነሆም፥ እግዚአብሔር በላዩ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ፥ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ አትፍራ፥ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤ 14ዘርህም እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ባሕርና እስከ አዜብ እስከ መስዕና እስከ ምሥራቅ ይበዛል፤ ይሞላልም፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተ፥ በዘርህም ይባረካሉ። 15እነሆም፥ እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚያችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።” 16ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ፥ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ አላወቅሁም ነበር” አለ። 17ፈራ፤ እንዲህም አለ፥ “ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህችም የሰማይ ደጅ ናት።”
18ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፤ ተንተርሷት የነበረችውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆማት፥ በላይዋም ዘይትን አፈሰሰባት። 19ያዕቆብም ያን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፤ አስቀድሞ ግን የዚያ ከተማ ስም ሎዛ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኡላምሉዝ” ግእዙ “ወለምሕሳ” ይላል። ነበረ። 20ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ፥ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ፥ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥ 21ወደ አባቴም ቤት በጤና ቢመልሰኝ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፤ 22ለሐውልት ያቆምኋት ይህችም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ትሆንልኛለች፤ ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከዐሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 28: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ