ኦሪት ዘፍጥረት 30
30
1ራሔልም ለያዕቆብ ልጅ እንዳልወለደች በአየች ጊዜ በእኅቷ ላይ ቀናችባት፤ ያዕቆብንም “ልጅ ስጠኝ፤ ይህስ ከአልሆነ እሞታለሁ” አለችው። 2ያዕቆብም፥ “የማኅፀንሽን ፍሬ የምከለክልሽ እኔ እንደ እግዚአብሔር ነኝን?” ብሎ ራሔልን ተቈጣት። 3እርስዋም፥ “ባሪያዬ ባላ እነሆ አለች፤ ወደ እርስዋ ግባ፤ በእኔም ጭን ላይ ትውለድ፤ የእርስዋም ልጆች ለእኔ ደግሞ ይሁኑልኝ” አለች። 4አገልጋይዋን ባላንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ለእርሱ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ። 5የራሔል አገልጋይ ባላም ፀነስች፤ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችለት። 6ራሔልም፥ “እግዚአብሔር ፈረደልኝ፤ ቃሌንም ደግሞ ሰማ፤ ወንድ ልጅንም ሰጠኝ” አለች፤ ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ ጠራችው። 7የራሔልም አገልጋይ ባላ ደግማ ፀነስች፤ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅን ወለደች። 8ራሔልም፥ “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አደረገኝ፤ ብርቱ ትግልንም ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፤ አሸነፍሁም፤ እኅቴንም መሰልኋት” አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ ጠራችው።
9ልያም መውለድን እንዳቆመች በአየች ጊዜ አገልጋይዋን ዘለፋን ወሰደች፤ ሚስት ትሆነውም ዘንድ ለያዕቆብ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ።#“ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ” በግሪክ ሰባ. ሊ. ብቻ። 10የልያ አገልጋይ ዘለፋም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። 11ልያም፥ “እኔም ራሴን ብፅዕት አሰኘሁ” ስትል ስሙን ጋድ ብላ ጠራችው። 12የልያ አገልጋይ ዘለፋም ዳግመኛ ለያዕቆብ ወንድ ልጅን ወለደች። 13ልያም፥ “እኔ ብፅዕት ነኝ፤ ሴቶች ያመሰግኑኛልና” አለች፤ ስሙንም አሴር ብላ ጠራችው።
14ሮቤል ስንዴ በሚታጨድበት ወራት ወጣ፤ በእርሻም እንኮይ አገኘ፥ ለእናቱ ለልያም አመጣላት። ራሔልም ልያን፥ “የልጅሽን እንኮይ ስጪኝ” አለቻት። 15ልያም፥ “ባሌን መውሰድሽ አይበቃሽምን? አሁን ደግሞ የልጄን እንኮይ ልትወስጂ ትፈልጊያለሽን?” አለቻት። ራሔልም “እንኪያስ ስለ ልጅሽ እንኮይ በዚህች ሌሊት ከአንቺ ጋር ይደር” አለች፤ ሰጠቻትም። 16ያዕቆብም ሲመሽ ከዱር ገባ፤ ልያም ልትቀበለው ወጣች፤ እንዲህም አለችው፥ “እኔ ዘንድ ታድራለህ፤ በልጄ እንኮይ በእርግጥ ተስማምቼሃለሁና።” 17በዚያችም ሌሊት ከእርስዋ ጋር አደረ። እግዚአብሔርም የልያን ጸሎት ሰማ፤ ፀነሰችም፤ አምስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። 18ልያም፥ “የልጄን እንኮይ#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “ባሪያዬን ለባሌ” ይላል። ስለ ሰጠሁ እግዚአብሔር ዋጋዬን ሰጠኝ” አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ ጠራችው። 19ልያም ደግማ ፀነስች፤ ስድስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። 20ልያም፥ “እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ሰጠኝ፤ እንግዲህስ ከዛሬ ጀምሮ ባሌ ይወደድኛል#ዕብ. “ባሌ ከእኔ ጋር ይኖራል” ይላል። ስድስት ልጆችን ወልጄለታለሁና” አለች፤ ስሙንም ዛብሎን ብላ ጠራችው። 21ከዚያም በኋላ ሴት ልጅን ወለደች፤ ስምዋንም ዲና አለቻት። 22እግዚአብሔርም ራሔልን አሰባት፤ እግዚአብሔርም ተለመናት፤ ማኅፀንዋንም ከፈተላት፤ ፀነሰችም፤ 23ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችና፥ “እግዚአብሔር ሽሙጤን ከእኔ አስወገደ” አለች፤ 24ስሙንም፥ “እግዚአብሔር ሁለተኛ ወንድ ልጅን ይጨምርልኝ” ስትል ዮሴፍ ብላ ጠራችው።
ያዕቆብ ስለ ደመወዝ ከላባ ጋር መከራከሩ
25ራሔልም ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፥ “ወደ ስፍራዬ፥ ወደ ሀገሬም እመለስ ዘንድ አሰናብተኝ። 26ስለ እነርሱ የተገዛሁላቸውን ሚስቶቼንና ልጆችን ስጠኝና ልሂድ፤ የተገዛሁልህን መገዛት ታውቃለህና።” 27ላባም፥ “በዐይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚሁ ተቀመጥ፤ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና። 28ደመወዝህን ንገረኝ፤ እርሱንም እሰጥሃለሁ” አለው። 29ያዕቆብም አለው፥ “እንዴት እንዳገለገልሁህ፥ በእኔ ዘንድ ያሉ ከብቶችህ ምን ያህል እንደ ሆኑ አታውቅምን? ጥቂት ሆነው አግኝቻቸዋለሁና፤ 30አሁን ግን ፈጽመው በዝተዋል፤ እግዚአብሔርም በእኔ መምጣት ባርኮአቸዋል፤ አሁን ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው?” 31ላባም፥ “የምሰጥህ ምንድን ነው?” አለው። ያዕቆብም አለው፥ “ምንም አትስጠኝ፤ ይህንም ነገር ብታደርግልኝ እንደገና በጎችህን አሰማራለሁ፤ እጠብቃለሁም። 32ዛሬ በጎችህ ሁሉ ይለፉ፤#ዕብ. “በመንጎችህ በኩል አልፋለሁ” ይላል። በዚያም ከበጎችህ መካከል ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለበትን ጥቁሩንም በግ ሁሉ፥ ከፍየሎቹም ነቍጣና ዝንጕርጕር ያለበትን ለይልኝ፤#ዕብ. “እለያለሁ” ይላል። እነርሱም ደመወዜ ይሆናሉ። 33ስለዚህም በፊትህ ያለውን ደመወዜን ለመመልከት በመጣህ ጊዜ ወደፊት ጻድቅነቴን ይመሰክርልኛል፤ ከፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ የሌለበት፥ ከበግ ጠቦቶችም ጥቁር ያልሆኑ ሁሉ፥ እርሱ በእኔ ዘንድ ቢገኝ እንደ ተሰረቀ ይቈጠርብኝ።”#ምዕ. 30 ቍ. 33 በግእዙ “ዝንጕርጕር ያልሆነው፥ መልኩም ነጭ ያልሆነው ሁሉ እርሱ ለአንተ ይሁን” ይላል። 34ላባም፥ “እነሆ እንደ ቃልህ ይሁን” አለ። 35በዚያም ቀን ከተባቶቹ ፍየሎች ሽመልመሌ መሳይና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ከእንስቶቹ ፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ነጭ ያለበትን ማንኛውንም ሁሉ፥ ከበጎቹም መካከል ጥቁሩን በግ ሁሉ ለይቶ ለልጆቹ ሰጣቸው። 36በእርሱና በያዕቆብ መካከልም የሦስት ቀን መንገድ ያህል አራቃቸው፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር። 37ያዕቆብም ልብን፥ ለውዝ፥ ኤርሞን ከሚባሉ ዕንጨቶች ርጥብ በትርን ወስዶ በበትሮቹ ውስጥ ያለው ነጭ እንዲታይ ነጭ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው። 38በጎቹም ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ በትሮቹ በፊታቸው ይሆኑ ዘንድ የላጣቸውን በትሮች በውኃ ማጠጫ ገንዳው ውስጥ አኖራቸው፤ 39በጎቹም መጥተው በጠጡ ጊዜ ሽመልመሌ መሳይና ዝንጕርጕር፥ ነቍጣም ያለበትን በበትሮቹ አምሳል ፀነሱ። 40ያዕቆብም ተባት በጎችንና እንስት በጎችን ለይቶ ነጭና ሐመደ ክቦ በሆኑ አውራዎች ፊት አቆማቸው፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ አውራዎቹን በእንስቶቹ በጎች ፊት አቆመ” ይላል። መንጎቹንም ለብቻቸው አቆማቸው። ከላባ በጎች ጋርም አልጨመራቸውም። 41እንዲህም ሆነ፦ በጎቹ በሚፀንሱበት ወራት በበትሮቹ አምሳል ይፀንሱ ዘንድ ያዕቆብ በትሮቹን በበጎቹ ፊት በውኃ ማጠጫ ገንዳው ውስጥ ያኖራቸው ነበር። 42በጎችም ከወለዱ በኋላ በፊታቸው በትሩን አያደርገውም ነበር፤ ምልክት ያላቸው ለያዕቆብ፥ ምልክት የሌላቸውም ለላባ ሆኑ። 43ያዕቆብም እጅግ ባለጠጋ ሆነ፤ ሴቶችም ወንዶችም አገልጋዮች፥ ብዙ ከብትም፤ ላሞችም፥ በጎችም፥ ግመሎችና አህዮችም ሆኑለት።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 30: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ