ኦሪት ዘፍጥረት 48
48
ያዕቆብ ኤፍሬምንና ምናሴን መባረኩ
1ከዚህም ነገር በኋላ እንዲህ ሆነ፤ “እነሆ፥ አባታችን ደከመ” ብለው ለዮሴፍ ነገሩት፤ እርሱም ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። 2ለያዕቆብም፥ “እነሆ፥ ልጅህ ዮሴፍ መጥቶልሃል” ብለው ነገሩት፤ እስራኤልም ተጠነካከረ፤ በአልጋውም ላይ ተቀመጠ። 3ያዕቆብ ዮሴፍን አለው፥ “አምላኬ በከነዓን ምድር በሎዛ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም። 4እንዲህም አለኝ፦ እነሆ፥ አበዛሃለሁ፤ አባዛሃለሁም፤ ለብዙም ሕዝብ ጉባኤ አደርግሃለሁ፤ ይህችንም ምድር ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለዘለዓለም ርስት ለዘርህ እሰጣታለሁ። 5አሁንም እኔ ወደ አንተ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የተወለዱልህ ሁለቱ ልጆችህ ለእኔ ይሁኑ፤ ኤፍሬምና ምናሴ ለእኔ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ናቸው። 6ከእነርሱም በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ለአንተ ይሁኑ፤ በርስታቸው በወንድሞቻቸው ስም ይጠሩ። 7እኔም ከሶርያ መስጴጦምያ በመጣሁ ጊዜ፥ ወደ ኤፍራታ ለመግባት ጥቂት ቀርቶኝ በፈረስ መጋለቢያው መንገድ ሳለሁ፥ ራሔል በከነዓን ምድር ሞተችብኝ፤ በዚያም በኤፍራታ ወደ ፈረስ መጋለቢያ በሚወስደው መንገድ ላይ ቀበርኋት፤ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት።”
8እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ለይቶ፥ “እነዚህ ምኖችህ ናቸው?” አለው። 9ዮሴፍም ለአባቱ ፥ “እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው። ያዕቆብም፥ “እባርካቸው ዘንድ ወደ እኔ አቅርብልኝ” አለው። 10የእስራኤልም ዐይኖች ከሽምግልና የተነሣ ከብደው ነበር፤ ማየትም አይችልም ነበር፤ ወደ እርሱም አቀረባቸው፤ ሳማቸውም፤ አቀፋቸውም። 11እስራኤልም ዮሴፍን፥ “ከፊትህ አልተለየሁም፤#ዕብ. “ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር” ይላል። እነሆም፥ እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ” አለው። 12ዮሴፍም ከጕልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፤ ወደ ምድርም በግንባሩ ሰገደ። 13ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፤ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አቆማቸው፤ ወደ አባቱም አቀረባቸው። 14እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፤ እርሱም ታናሽ ነበረ፤ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፤ እጆቹንም አስተላለፈ።#ዕብ. “ምናሴ በኵር ነበርና” የሚል ይጨምራል። 15ያዕቆብም ባረካቸው፤#ዕብ. “ያዕቆብ ዮሴፍን ባረከ” ይላል። እንዲህም አለ፥ “አባቶች አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ ደስ ያሰኙት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ 16ከከፉ ነገር ሁሉ የአዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም፥ የአባቶች የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድር ላይ ይብዙ፤ የብዙ ብዙም ይሁኑ፤” 17ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ በአየ ጊዜ ከባድ ነገር ሆነበት፤ ዮሴፍም የአባቱን እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው። 18ዮሴፍም አባቱን፥ “አባቴ ሆይ፥ እንዲህ አይደለም፤ በኵሩ ይህ ነውና ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ” አለው። 19አባቱም እንቢ አለ፤ እንዲህ ሲል፥ “አውቃለሁ ልጄ ሆይ፥ አውቃለሁ፤ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፤ ዘሩም ብዙ ሕዝብ ይሆናል።” 20በዚያም ቀን እንዲህ ብሎ ባረካቸው፥ “በእናንተ እስራኤል#አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “በእናንተ የእስራኤል አምላክ ይመሰገናል” ይላል። እንዲህ ተብሎ ይባረካል፦ እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ይባርክህ።” ኤፍሬምንም ከምናሴ ፊት አደረገው። 21እስራኤልም ዮሴፍን፥ “እነሆ፥ እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ወደ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፤ 22እኔም ከአሞራውያን እጅ በሰይፌና በቀስቴ የወሰድሁትን ምርኮ ለአንተ ከወንድሞችህ የተሻለውን እሰጥሃለሁ” አለው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 48: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ