ወደ ዕብራውያን 2
2
ስለሚመጣው ዓለም
1ስለዚህም ከሰማነው ነገር ምንአልባት እንዳንወሰድ ለእርሱ አብዝተን ልንጠነቀቅ ይገባናል። 2በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ 3እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበረና የሰሙትም ለእኛ አጸኑት። 4እግዚአብሔርም እንደ ራሱ ፈቃድ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በመስጠት፥ በምልክትና በድንቅ ነገር፥ በልዩ ልዩ ተአምራትም መሰከረላቸው፤ ነገራቸውንም አስረዳላቸው።
5ስለ እርሱ የምንናገርለትን የሚመጣውን ዓለም ለመላእክት ያስገዛ አይደለም። 6ነገር ግን መጽሐፍ እንዲህ ብሎ የመሰከረበት ስፍራ አለ፤ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጐበኘውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? 7ከመላእክትህ ጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድንም ጫንህለት፤ በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው። 8#መዝ. 8፥4-6። ሁሉንም ከእግሩ በታች አድርገህ አስገዛህለት።” ሁሉን ለእርሱ ባስገዛለት ጊዜም የተወውና ያላስገዛለት የለም፤ አሁን ግን ሁሉን እንዳስገዛለት አናይም። 9ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ጭኖ እናየዋለን።
10ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእጁ ለተያዘ፥ በእርሱም ሁሉ ለሆነ ለእርሱ ተገብቶታልና። 11እነርሱን የቀደሳቸው እርሱ፥ የተቀደሱት እነርሱም ሁሉም በአንድነት ከአንዱ ናቸውና። ስለዚህም እነርሱን፥ “ወንድሞች” ማለትን አያፍርም። 12#መዝ. 21፥22። “ስምህን ለወንድሞች እነግራቸዋለሁ፤ በማኅበር መካከልም አመሰግንሃለሁ” አለ። 13#ኢሳ. 8፥17-18። ዳግመኛም፥ “እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች እነሆ፥” አለ፤ ዳግመኛም፥ “እኔ እታመንበታለሁ” አለ። 14ልጆች በሥጋና በደም አንድ ናቸውና፤ እርሱ ደግሞ በዚህ ከእነርሱ ጋር አንድ ሆነ፤ ለእነርሱም እንደ ወንድም ሆነላቸው፤#“ለእነርሱም እንደ ወንድም ሆነላቸው” የሚለው በግሪኩ የለም። መልአከ ሞትን በሞቱ ይሽረው ዘንድ፥ ይኸውም ሰይጣን ነው። 15በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ሞትን በመፍራት የተቀጡትን፥ ለባርነት የተገዙትንም ሁሉ ያሳርፋቸው ዘንድ። 16የነሣውን ከአብርሃም ዘር እንጂ ከመላእክት የነሣው አይደለምና። 17ስለዚህም የሕዝብን ኀጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው። 18እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።
Currently Selected:
ወደ ዕብራውያን 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ