ትንቢተ ሆሴዕ 1
1
1በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስም ዘመን በእስራኤልም ንጉሥ በኢዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
የሆሴዕ ሚስትና ልጆቹ
2ወደ ሆሴዕ የመጣ የእግዚአብሔር የቃሉ መጀመሪያ ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሆሴዕን፥ “ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታመነዝራለችና ሂድ፤ ዘማዊቱን ሴትና የዘማዊቱን ልጆች ለአንተ ውሰድ” አለው። 3እርሱም ሄዶ የዴብላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደችለት። 4እግዚአብሔርም፥ “ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በይሁዳ ቤት ላይ #ዕብ. “በኢዩ ቤት ላይ” ይላል። እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፤ 5በዚያም ጊዜ እንዲህ ይሆናል፤ በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ” አለው። 6ደግሞ ፀነሰች፤ ሴት ልጅንም ወለደች። እግዚአብሔርም፥ “መለየትን እለያቸዋለሁ እንጂ ይቅር እላቸው ዘንድ የእስራኤልን ቤት ከእንግዲህ ወዲህ አልምራቸውምና ስምዋን ኢሥህልት ብለህ ጥራት፤ 7ነገር ግን የይሁዳን ልጆች ይቅር እላቸዋለሁ፤ እኔ አምላካቸውም እግዚአብሔር አድናቸዋለሁ እንጂ በቀስት ወይም በሰይፍ፥ ወይም በጦር፥ ወይም በሠረገላ፥ ወይም በፈረሶች፥ ወይም በፈረሰኞች የማድናቸው አይደለም” አለው።
8ኢሥህልትንም ጡት ባስጣሏት ጊዜ፥ ደግሞ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅንም ወለደች። 9እግዚአብሔርም፥ “ሕዝቤ አይደላችሁምና፥ እኔም አምላክ አልሆናችሁምና ስሙን ኢሕዝብየ ብለህ ጥራው” አለው።#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. ምዕ. 1 ቍ. 9 ላይ ይጨርሳል ቍ. 10 ላይ ምዕ. 2ን ይጀምራል።
የእስራኤል መመለስ
10የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲህም ይሆናል፤ “እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም” ተብሎ በተነገረበት በዚያ ስፍራ የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ። 11የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፤ ለእነርሱም አንድ አለቃ ይሾማሉ፤ ከምድሪቱም ይወጣሉ፤ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ