ትንቢተ ሆሴዕ 12
12
1ኤፍሬም በሐሰት፥ የእስራኤል ቤትና ይሁዳም በተንኰል ከበቡኝ፤ አሁንም እግዚአብሔር ዐወቃቸው፤ ለእግዚአብሔርም ቅዱስ ሕዝብ ተባሉ። 2ኤፍሬም ግን ክብርንና ከንቱ ነገርን የሚያሳድድ ክፉ ጋኔን ነው።#ዕብ. “ነፋስን ይበላል ፥ የምሥራቅንም ነፋስ ይከተላል” ይላል። ሁልጊዜም ሐሰትንና ተንኰልን ያበዛል፤ ከአሦርም ጋር ቃል ኪዳን ያደርጋል፤ ምሕረትም ያደርጉለት ዘንድ ወደ ግብፅ ዘይትን ይልካል። 3እግዚአብሔርም ደግሞ ከይሁዳ ጋር ይዋቀሳል፤ ያዕቆብንም እንደ መንገዱ ይበቀለዋል፤ እንደ ሥራውም ይከፍለዋል። 4በማኅፀን ውስጥ ወንድሙን በተረከዙ ያዘው፤ በደካማነቱም ጊዜ ከአምላክ ጋር ታገለ። 5ከመልአኩም ጋር ታግሎ አሸነፈ፤ አልቅሶም ለመነኝ። በቤትአዎንም#ዕብ. “በቤቴልም” ይላል። አገኘኝ፤ በዚያም ከእኔ ጋር ተነጋገረ። 6ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር መታሰቢያው ነው።#ዕብ. “የመታሰቢያው ስም እግዚአብሔር ነው” ይላል። 7ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ምሕረትንና ፍርድን ጠብቅ፤ ዘወትርም ወደ አምላክህ ቅረብ።
8በከነዓን እጅ የዐመፅ ሚዛን አለ፤ ቅሚያንም ይወድዳል። 9ኤፍሬምም፥ “ባለጸጋ ሆኜአለሁ፤ ሀብትንም አግኝቻለሁ፤ በድካሜም ሁሉ ኀጢአት የሚሆን በደል አይገኝብኝም” አለ። 10እኔም ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንደ ዓመት በዓል ቀንም እንደ ገና በድንኳን አስቀምጥሃለሁ። 11ለነቢያትም ተናግሬአለሁ፤ ራእይንም አብዝቻለሁ፤ በነቢያትም እጅ ተመስያለሁ። 12በገለዓድ ባይሆንም እንኳ በጌልጌላ መሥዋዕታቸውን የሚሠዉ አለቆች ስተዋል፤ መሠዊያዎቻቸውም በእርሻ ትልም ላይ እንደ አለ የድንጋይ ክምር ነው።#ዕብ. “ኀጢአት በገለዓድ አለ ፤ ፈጽመው ከንቱ ናቸው ፤ ወይፈኖች በጌልጌላ ይሠዋሉ ፤” ይላል። 13ያዕቆብ ወደ ሶርያ ሀገር ሸሸ፤ እስራኤልም ስለ ሚስት አገለገለ፤ ስለ ሚስትም ጠበቀ። 14እግዚአብሔርም በነቢይ እስራኤልን ከግብፅ ምድር አወጣው፤ በነቢይም ጠበቀው። 15ኤፍሬም ተመረረ፤ ተቈጣም፤ ደሙም በላዩ ላይ ይፈስሳል፤ እግዚአብሔርም ስድቡን በራሱ ላይ ይመልሳል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 12: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ