ትንቢተ ኢሳይያስ 3
3
በኢየሩሳሌም ስለሚደርስ ሁከት
1እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ኀይለኛውን ወንድና ኀይለኛዋን ሴት፥ የእንጃራን ኀይል ሁሉ፥ የውኃውንም ኀይል ሁሉ ያስወግዳል፤ 2ኀያሉንም፥ ተዋጊውንም፥ ፈራጁንም፥ ነቢዩንም፥ ዐዋቂውንም፥ ሽማግሌውንም፥ 3የአምሳ አለቃውንም፥ የተከበረ አማካሪውንም፥ ጠቢቡንም፥ የአናጢዎቹንም አለቃ፥ አስተዋይ አድማጩንም ያስወግዳል። 4በእነርሱ ላይ አለቆቻቸው እንዲሆኑ ጐልማሶችን እሾምባቸዋለሁ፤ ዘባቾችም ይገዙአቸዋል። 5ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ ሰው በሰው ላይ፥ ሰውም በባልንጀራው ላይ ይገፋፋል፤ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ፥ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይታበያል። 6ሰውም በአባቱ ቤተ ሰብእ ውስጥ ወንድሙን ይዞ፥ “አንተ ልብስ አለህ፥ አለቃም ሁንልን፥ ምግባችንም ከእጅህ በታች ትሁን” ቢለው፥ 7በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፥ “እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ለሕዝቡ አለቃ አልሆንም”#ዕብ. “ባለ መድኀኒት አልሆንም” ይላል። ብሎ መለሰለት። 8ኢየሩሳሌም ተፈትታለችና፥ ይሁዳም ወድቃለችና፥ አንደበታቸውም ዐመፅን ስለሚናገር ለእግዚአብሔር አልታዘዙም። 9ዛሬም ክብራቸው ተዋርዷልና፥ ፊታቸውም አፍሯልና ኀጢአታቸው እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ኀጢአት ተቃወመቻቸው፤ በላያቸውም ተገልጣ ታወቀች።#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “ኀጢአታቸውንም እንደ ሰዶም ያወራሉ ይገልጡአትማል” ይላል። 10ክፉ ምክርን መክረዋልና ለነፍሳቸው ወዮላት! እንዲህም አሉ፥ “ጻድቁን እንሻረው፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እንሰረው” ይላል። ሸክም ሆኖብናልና፤” ስለዚህ የእጃቸውን ሥራ ፍሬ ይበላሉ። 11እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ይደርስበታል። 12ሕዝቤ ሆይ፥ ገዥዎቻችሁ ያስጨንቁአችኋል፤ አስጨናቂዎች ሴቶችም በላያችሁ ይሠለጥኑባችኋል። ሕዝቤ ሆይ፥ የሚያመሰግኑአችሁ ያስቱአችኋል፤ የምትሄዱበትንም መንገድ ያጠፋሉ።
እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ እንደሚፈርድ
13ነገር ግን እግዚአብሔር ዛሬ ለፍርድ ይነሣል፤ በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ይነሣል። 14እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ለፍርድ ይመጣል፤ እንዲህም ይላል፥ “ወይኔን አቃጥላችኋል፤ ከድሃው የበዘበዛችሁትም በቤታችሁ አለ፤ 15ሕዝቤንስ ለምን ትገፋላችሁ? የድሃውን ፊትስ ለምን ታሳፍሩታላችሁ?”
ለኢየሩሳሌም ሴቶች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
16እግዚአብሔር እንዲህ አለ፥ “የጽዮን ቆነጃጅት ኰርተዋልና፥ አንገታቸውን እያሰገጉ በዐይናቸውም እያጣቀሱ፥ በእግራቸውም እያረገዱ፥ ልብሳቸውንም እየጐተቱ፥ በእግራቸውም እያማቱ ይሄዳሉና፤ 17ስለዚህ ጌታ የጽዮን ታላላቅ ሴቶች ልጆችን ያዋርዳቸዋል። እግዚአብሔርም በዚያ ቀን ልብሳቸውን ይገልጣል። 18በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእግር አልቦውን ክብር፥ መርበቡንም፥ ጨረቃ የሚመስለውንም ጌጥ፥ 19የጆሮ እንጥልጥሉንም፥ አንባሩንም፥ መሸፈኛውንም፥ ቀጸላውንም፥ 20ሰንሰለቱንም፥ መቀነቱንም፥ የሽቱውንም ዕቃ፥ አሸንክታቡንም፥ 21የእጅና የአፍንጫ ቀለበቱንም፥ 22የዓመት በዓልንም ልብስ፥ መጐናጸፊያውንም፥ ልግምበገላውንም፥ ከረጢቱንም፥ 23መስተዋቱንም ከጥሩ በፍታ የተሠራውንም ልብስ፥ ራስ ማሰሪያውንም፥ ዐይነ ርግቡንም ያስወግዳል። 24እንዲህም ይሆናል፤ ስለ ሥራሽ ክፋት በሽቱ ፋንታ ትቢያ ይሁንብሽ፤ በወርቅ መታጠቂያሽም ፋንታ ገመድ ታጠቂ፤ በራስ ወርቅ ቀጸላሽም ፋንታ ቡሃነት ይውጣብሽ፤ በሐር መጐናጸፊያሽ ፋንታ ማቅ ልበሽ። 25የምትወጂው ትልቁ ልጅሽ በሰይፍ ይወድቃል፤ ኀያላንሽም በውጊያ ይወድቃሉ። 26የጌጦችሽም ሣጥኖች ያለቅሳሉ፤ ይዋረዳሉም፤ ብቻሽንም ትቀሪያለሽ፤ ከምድርም ጋር ትቀላቀያለሽ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 3: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ