ትንቢተ ኢሳይያስ 2
2
ስለ እግዚአብሔር ቤት
1ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ወደ አሞፅ ልጅ ወደ ኢሳይያስ የመጣ ቃል።
2በኋላ ዘመን እንዲህ ይሆናል፤ የእግዚአብሔር ቤት በተራሮች ራስ ላይ ይታያል፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የእግዚአብሔር ተራራ የተከበረ ይሆናል ፤ የእግዚአብሔርም ቤት በተራሮች ራስ ላይ ይሆናል ፤” ይላል። ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛቡም ሁሉ ወደ እርሱ ይመጣሉ። 3ሕግ ከጽዮን፥ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ መጥተው፥ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፤ በጎዳናውም እንሄዳለን” ይላሉ። 4በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፤ ብዙ አሕዛብንም ይዘልፋቸዋል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፥ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍን አያነሣም፤ ሰልፍንም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።
5አሁንም የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ኑ፤ በእግዚአብሔር ብርሃን እንመላለስ። 6ሕዝቡን የያዕቆብን ቤት ትቶአልና፤ ምድራቸው እንደ ቀድሞው እንደ ፍልስጥኤማውያን ምድር በሟርት ተሞልቶአልና፤ እንደ ባዕድ ልጆችም ሆነዋልና፤ ብዙ እንግዶች ልጆችም ተወልደውላቸዋልና። 7ምድራቸውም በብርና በወርቅ ተሞልታለች፤ ለመዛግብቶቻቸውም ቍጥር የለውም፤ ምድራቸውም ደግሞ በፈረሶች ተሞልታለች፤ ለሰረገሎቻቸውም ቍጥር የለውም። 8ምድራቸውም በእጆቻቸው በሠሩአቸው ጣዖታት ተሞልታለች፤ በጣቶቻቸውም ለሠሩአቸው ይሰግዳሉ። 9ታናሹም ሰው ዝቅ ብሎአል፤ ታላቁም ሰው ተዋርዶአል፤ ኀጢአታቸውንም ይቅር አልላቸውም።
10አሁንም ምድርን ያነዋውጣት ዘንድ በተነሣ ጊዜ እግዚአብሔርን ከመፍራትና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻ ግቡ፤ በመሬት ውስጥም ተሸሸጉ። 11የትዕቢተኞች ሰዎች ዐይኖች ይዋረዳሉ፤#ግሪኩ “የእግዚአብሔር ዐይኖች ከፍ ከፍ ይላሉ” ይላል። የሰዎችም ኵራት ትወድቃለች፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል።
12የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን በትዕቢተኛውና በኵራተኛው ሁሉ ላይ ከፍ ባለውም ላይ ይሆናል፤ እነርሱም ይዋረዳሉ፤ 13ደግሞም በረጅሙ ከፍ ባለውም በሊባኖስ ዝግባ ሁሉ ላይ፥ በባሳንም ዛፍ ሁሉ ላይ፥ 14በረጅሙም ተራራ ሁሉ ላይ፥ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ 15በረጅሙም ግንብ ሁሉ ላይ፥ በተመሸገውም ቅጥር ሁሉ ላይ፥ 16በባሕሩም መርከብ ሁሉ ላይ፥ በተጌጡ ጣዖታትም ምስል#ጊርክ ሰባ. ሊ. “በተደረደሩ መርከቦችም” ይላል። ሁሉ ላይ ይሆናል። 17ሰውም ሁሉ ይዋረዳል፤ የሰውም ኵራት ይወድቃል፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል። 18በእጅ የተሠሩ ጣዖታትን ሁሉ ይሰውራሉ፤ 19እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ እግዚአብሔርን ከመፍራትና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ምድር ንቃቃት ውስጥ ያገቡአቸዋል። 20በዚያም ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጁአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቹን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይጥላል። 21እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ እግዚአብሔርን ከመፍራትና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ተሰነጠቁ ዓለቶች ውስጥ ያገባሉ። 22እስትንፋሱ በአፍንጫው ያለበትን ሰው ተዉት፤ እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል?#ምዕ . 2 ቍ. 22 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 2: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ