ትንቢተ ኢሳይያስ 53
53
1ጌታ ሆይ፥ ነገራችንን ማን ያምነናል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? 2ነገራችን በፊቱ እንደ ሕፃን፥ በደረቅ መሬትም እንዳለ ሥር ሆነ፤ መልክና ውበት የለውም፤ እነሆ፥ አየነው፤ ደም ግባት የለውም፤ ውበትም የለውም። 3መልኩም የተናቀ፥ ከሰውም ልጆች ሁሉ የተዋረደ፥ የተገረፈ ሰው፥ መከራንም የተቀበለ ነው፤ ፊቱንም መልሶአልና አቃለሉት፥ አላከበሩትምም።
4እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኀጢአታችንን ተቀበለ” ይላል። ሕመማችንንም ተሸከመ፤ ስለ እኛም ታመመ፤ እኛም እንደ ታመመ፥ እንደ ተገረፈም ቈጠርነው። 5እርሱ ግን ስለ ኀጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፤ የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። 6እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም ስለ ኀጢአታችን ለሞት አሳልፎ ሰጠው።#ዕብ. “የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ” ይላል።
7እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። 8በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዷልና ልደቱን ማን ይናገራል? ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ለሞት ደረሰ።#ዕብ. “ከፍርድ ተወሰደ ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?” ይላል። 9ክፉዎችንም ስለ መቃብሩ፥ ባለጸጎችንም ስለ ሞቱ እሰጣለሁ፤ ኀጢአትን አላደረገምና፥ ከአፉም ሐሰት አልተገኘበትምና።#ዕብ. “ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ ፤ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ፤ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር ፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም ነበር” ይላል።
10እግዚአብሔር ከግርፋቱ ያነጻው ዘንድ ፈቀደ፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕትን ብታቀርቡ ሰውነታችሁ ረዥም ዕድሜ ያለውን ዘር ታያለች።#ዕብ. “ስለ ኀጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል” ይላል። 11እግዚአብሔርም ከሰውነቱ ሕማምን ያርቅ ዘንድ ይወዳል፤ ብርሃንንም ያሳየዋል፤ በጥበቡም ይለየዋል፤ ለጽድቅና ለበጎ ነገር የሚገዛውን ጻድቁን ያጸድቀዋል። የብዙዎችንም ኀጢአታቸውን እርሱ ይደመስሳል። 12ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፤ ከኀያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ኀጢአታቸውም ተሰጠ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 53: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ