ትንቢተ ኢሳይያስ 57
57
የእስራኤል ጣዖት ማምለካቸው እንደ ተወገዘ
1ጻድቅ ሰው እንደጠፋ አያችሁ፤ ይህንም በልባችሁ አላሰባችሁም፤ ጻድቃን ሰዎች ይወገዳሉ፤ ጻድቅም ከክፋት ፊት እንደ ተወገደ ማንም አያስተውልም። 2መቃብሩ በሰላም ይሆናል፤ ከመካከልም ይወሰዳል።#ዕብ. “ወደ ሰላም ይገባል፥ በቅንነት የሄደ በአልጋው ላይ ያርፋል” ይላል።
3እናንተ የኃጥኣን#ዕብ. “የአስማተኛዪቱ ልጆች” ይላል። ልጆች፥ የዘማውያንና የጋለሞታዪቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ። 4በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ? 5እናንተ በለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች በጣዖት ደስ የምትሰኙ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ልጆቻችሁን የምትሠዉ፥ እናንተ የጥፋት ልጆችና የዐመፀኞች ዘሮች አይደላችሁምን? 6በሸለቆ ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች#“በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች” የሚለው በዕብ. ብቻ። ዕድል ፋንታሽ ናቸው፤ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፤ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣምን?
7ከፍ ባለውና በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፤ በዚያም መሥዋዕትሽን ሠዋሽ። 8ከመዝጊያው በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ብትተዪ የሚጠቅምሽ መሰለሽን? ከእኔም ይልቅ ከአንቺ ጋራ የሚተኙትን መረጥሽ። 9ዝሙትሽን ከእነርሱ ጋር አበዛሽ፤ ከአንቺ የራቁ ብዙዎችንም ተጐዳኘሽ።#ዕብ. “ዘይትም ይዘሽ ወደ ንጉሡ ሄድሽ፥ ሽቱንም አበዛሽ” ይላል። መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፤ ከእነርሱም ጋር ተወገድሽ፤ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ። 10በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፤ ዳግመኛም ጕልበት እያለኝ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን መንገድ አልተውም አላልሽም፤ ይህንም ስላደረግሽ አላፈርሽም።
11ሐሰት የተናገርሽው፥ እኔንም ያላሰብሽው፥ በልብሽም ነገሩን ያላኖርሽው ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔም ዝም አልሁሽ፤ አንቺም አልፈራሽኝም። 12እንግዲህ እኔ ጽድቄንና የማይረባሽን የአንቺን በደል እናገራለሁ። 13በችግርሽ ቀን በጮኽሽ ጊዜ እስኪ ይታደጉሽ፤ እነሆ፥ ዐውሎ ይወስዳቸዋል፤ ነፋስም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። ወደ እኔ የሚጠጉ ግን ምድሪቱን ይገዛሉ፤ የተቀደሰውን ተራራዬንም ይወርሳሉ።
14እርሱም፥ “በፊቱ፥ መንገድን ጥረጉ፤ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አስወግዱ” ይላል። 15ለዘለዓለም በአርያም የሚኖር ስሙም ቅዱሰ ቅዱሳን የሆነ፥ በቅዱሳን አድሮ የሚኖር፥ ለተዋረዱት ትዕግሥትን የሚሰጥ፥ ልባቸውም ለተቀጠቀጠ ሕይወትን የሚሰጥ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 16“መንፈስ ከእኔ ይወጣልና፥ የሁሉንም ነፍስ ፈጥሬአለሁና ለዘለዓለም አልቀስፋችሁም፤ ሁልጊዜም አልቈጣችሁም። 17ስለ ኀጢአቱ ጥቂት ጊዜ መከራ አመጣሁበት፤ ቀሠፍሁትም፤ ፊቴንም ከእርሱ መለስሁ፤ እርሱም አዘነ። እያዘነም ሄደ። 18ከዚህም በኋላ መንገዱን አይቻለሁ፤ ፈወስሁትም፤ አጽናናሁት፤ እውነተኛ ደስታንም ሰጠሁት። 19በሩቅም በቅርብም ላሉ በሰላም ላይ ሰላም ይሁን፤ እፈውሳቸውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
20“ኃጥኣን ግን እንዲህ ይገለበጣሉ፤ ዕረፍትንም አያገኙም።#ዕብ. “እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው ፤ ጸጥ ይል ዘንድ አይችልምና ውሆቹም ጭቃና ጕድፍ ያወጣሉና” ይላል። 21ለኃጥአን ደስታ የላቸውም” ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 57: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ