ትንቢተ ኢሳይያስ 58
58
ስለ እውነተኛ ጾም
1በኀይልህ ጩኽ፤ አትቈጥብ፤ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፤ ለሕዝቤ ኀጢአታቸውን፥ ለያዕቆብ ቤትም በደላቸውን ንገር። 2ነገር ግን ጽድቅን እንደሚያደርግ የአምላኩንም ፍርድ እንደማይተው ሕዝብ ዕለት ዕለት ይሹኛል፤ መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ። አሁንም እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፤ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። 3“ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅኸንም?” ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። 4እነሆ፥ ለጠብና ለክርክር ትጾማላችሁ፤ ድሃውንም በጡጫ ትማታላችሁ፤ በምትጮኹበት ጊዜ ድምፃችሁ እንዲሰማ ለእኔ ትጾማላችሁን? ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። 5እኔ ይህን ጾም የመረጥሁ አይደለሁም፤ እንደዚችም ባለች ቀን ሰው ራሱን ቢያሳዝን፥ አንገቱንም እንደ ቀለበት ቢያቀጥን፥ ማቅ ለብሶ በአመድ ላይ ቢተኛም፥ ይህ ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠ አይደለም። 6ይህን ጾም የመረጥሁ አይደለም ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን የበደልን እስራት ፍታ፤ ጠማማውን ሁሉ አቅና፤ የተጨነቀውንም ሁሉ አድን፤ የዐመፃ ደብዳቤንም ተው። 7ለተራበውም እንጀራህን አጥግበው፤ ድሆችን ወደ ቤትህ አስገብተህ አሳድራቸው፤ የተራቈተውንም ብታይ አልብሰው፤ ከሥጋ ዘመድህ አትሸሽግ። 8ያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፤ ፈውስህም ፈጥኖ ይወጣል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይጋርድሃል። 9ያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ፤ እርሱም፦ እነሆኝ፥ ይልሃል። የዐመፅ እስራትን ከመካከልህ ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ማንጐራጐርንም ብትተው፥ 10ከምግብህም ለተራበ ብታካፍል፥ የተራበች ሰውነትንም ብታጠግብ፥ ያንጊዜ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል፤ ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል። 11እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ከአንተ ጋር ይኖራል፤ እንደ ነፍስህም ፍላጎት ያጠግብሃል፤ አጥንትህንም ያለመልማል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። 12ከድሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎችህ ይሠራሉ፤ መሠረትህም ለልጅ ልጅ ዘመን ይሆናል፤ አንተም፦ ሰባራውን ጠጋኝ፥ የመኖሪያ መንገድንም አዳሽ ትባላለህ።
13ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፥ ሰንበትንም ደስታ፥ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ብታደርገው፥ ክፉ ሥራን ለመሥራት እግርህን ባታነሣ፥ በአፍህም ክፉ ነገርን ባትናገር፥ 14በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ትታመናለህ፤ በምድርም በረከት ላይ ያወጣሃል፤ የአባትህ የያዕቆብንም ርስት ይመግብሃል፤ የእግዚአብሔር አፍ እንደዚህ ተናግሮአልና።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 58: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ