ትንቢተ ኢሳይያስ 59
59
የሕዝቡ ኀጢአት እንደ ተወገዘ
1በውኑ፥ የእግዚአብሔር እጅ ማዳን አትችልምን? ጆሮውስ አይሰማምን? 2ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በእግዚአብሔር መካከል ለይታለች፤ ይቅርም እንዳይላችሁ ኀጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። 3እጃችሁ በደም ጣታችሁም በኀጢአት ተሞልትዋል፤ ከንፈራችሁም ዐመፅን ተናግሮአል፤ ምላሳችሁም ኀጢአትን አሰምቶአል።
4ጽድቅን የሚናገር በእውነትም የሚፈርድ የለም፤ በከንቱ ነገር ታምነዋል፤ የማይጠቅማቸውንም ተናግረዋል፤ ኀጢአትን ፀንሰዋል፤ በደልንም ወልደዋል። 5የእባብን ዕንቍላል ቀፈቀፉ፤ የሸረሪትንም ድር አደሩ፤ እንቁላላቸውንም የሚበላ ሰው ፈጥኖ ይሞታል፤ እንቍላሉም ሲሰበር እባብ ይወጣል። 6የሸረሪቶች ድር ልብስ አይሆንም፤ በሥራቸውም ራሳቸውን አያለብሱም፤ ሥራቸው የግፍ ሥራ ነውና።#ዕብ. “የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው” ይላል። 7እግሮቻቸውም ለተንኮል ይሮጣሉ፤ ደምን ለማፍሰስም ይፈጥናሉ፤ ሰውን ለመግደል ይመክራሉ፤ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ በመንገዳቸው አለ። 8የሰላምን መንገድ አያውቁም፤ በመንገዳቸውም ፍርድ የለም፤ የሚሄዱበትም መንገድ ጠማማ ነው፤ ሰላምንም አያውቁም።
9ስለዚህ ፍርድ ከእነርሱ ዘንድ ርቆአል፤ ጽድቅም አላገኛቸውም፤ ብርሃንን ሲጠባበቁ ብርሃናቸው ጨለማ ሆነባቸው፤ ብርሃንንም ሲጠባበቁ በጨለማ ሄዱ፤ 10እንደ ዕውሮች ወደ ቅጥሩ ተርመሰመሱ፤ ዐይንም እንደሌላቸው ተርመሰመሱ፤ በቀትርም ጊዜ በመንፈቀ ሌሊት እንዳለ ሰው ተሰናከሉ፤ እንደ ሙታንም ይጨነቃሉ። 11እንደ ድብና እንደ ርግብ በአንድነት ይሄዳሉ፤ ፍርድን እንጠባበቅ ነበር፤ መዳንም የለም፤ ከእኛም ርቆአል።
12ዐመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኀጢአታችንም መስክሮብናልና፥ ዐመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ ጽድቅንም አላወቅንምና። 13በድለናል፤ ዋሽተናልም፤ አምላካችንንም መከተል ትተናል፤ ዐመፃን ተናግረናል፤ ከድተንሃልም፤ የኀጢአትንም ቃል ፀንሰን፤ ከልብ አውጥተናል። 14ፍርድን ከመከተል ወደ ኋላ ርቀናል፤ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም ከመንገዳቸው ታጥቶአል፤ በቀና መንገድም መሄድ አልቻሉም። 15ከእውነት ተወግደዋል፤ እንዳያስተውሉም ልባቸውን መልሰዋል። እግዚአብሔርም አየ፤ ፍርድም ስለሌለ ደስ አላለውም። 16ሰውም እንደሌለ አየ፤ የሚረዳም ሰው እንደሌለ ተረዳ፤ ሰለዚህ በክንዱ ደገፋቸው፤ በይቅርታውም አጸናቸው። 17ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፤ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ። 18ጠላቶቹንም ያዋርዳቸው ዘንድ የበቀልና የፍዳን መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ።#ዕብ. “እንደ ሥራቸው መጠን እንዲሁ ቍጣን ለባላጋራዎቹ ፍዳንም ለጠላቶቹ ይከፍላል ለደሴቶችም ፍዳቸውን ይከፍላል” ይላል። 19በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም፥ በፀሐይ መውጫም ያሉት ክብሩን ይፈራሉ። መቅሠፍትም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ኀይለኛ ፈሳሽ በቍጣ ይመጣል።
20ከጽዮን ታዳጊ ይመጣል፤ ከያዕቆብም ኀጢአትን ያርቃል።#ዕብ. “ይላል እግዚአብሔር” ብሎ ይጨምራል። 21“ከእነርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከአፍህ፥ ከዘርህም አፍ፥ ከዘር ዘርህም አፍ አይጠፋም፥” ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 59: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ