ትንቢተ ኢሳይያስ 9
9
ስለሚመጣው ንጉሥ
1የዚህም ጊዜው እስከሚደርስ የተቸገረው ሁሉ አያመልጥም፤ በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፤ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል። 2በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው። 3ብዙ ሕዝብን በደስታ አወረድህ፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ምርኮንም እንደሚካፈሉ በፊትህ ደስ ይላቸዋል። 4በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ በላያቸው የነበረው ቀንበር ተነሥቶአልና፥ በጫንቃቸው የነበረውንም፥ የአስጨናቂዎችንም በትር መልሶአልና። 5በደም የተለወሰ ልብስ በእሳት ከሚቃጠል በቀር ለምንም አይጠቅምም።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በማታለል የተሰበሰበውን ልብስ ሁሉ ይመልሳሉ ፤ በለውጡም ልብስን ይቀበላሉ በእሳትም ሊያቃጥሉት ይወድዳሉ” ይላል። 6ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፤ 7ለአለቆች ሰላምን ለእርሱም ሕይወትን አመጣለሁና፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ ግዛቱ ታላቅ ይሆናል፤ በዳዊት ዙፋን መንግሥቱ ትጸናለች፤ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም። የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅንዐት ይህን ያደርጋል።
8ጌታ በያዕቆብ ላይ ሞትን#ዕብ. “ቃልን” ይላል። ላከ፤ በእስራኤልም ላይ ወደቀ። 9የኤፍሬም ሕዝብ ሁሉና በሰማርያ የሚኖሩ ያውቃሉ፤ በትዕቢትና በልብ ኵራትም እንዲህ ይላሉ፦ 10“ጡቡ ወደቀ፤ ነገር ግን ኑ፥ ድንጋይ እንውቀር፤ ሾላው ነቀዘ፤ ነገር ግን ፅድን እንቍረጥ፤ ለራሳችንም ግንብን እንሥራ።” 11ስለዚህ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይ እርሱን በመቃወም የሚነሡትን ይበትናቸዋል። 12ጠላቶቹን ሶርያውያንንም ከምሥራቅ፥ አረማውያንንም ከምዕራብ ያንቀሳቅስበታል፤ እስራኤልንም በተከፈተ አፍ ይበሉታል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
13ሕዝቡ ግን እስከተቀሠፉ ድረስ አልተመለሱም፤ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን አልፈለጉም። 14ስለዚህ እግዚአብሔር ራስንና ጅራትን፥ ታላቁንና ታናሹን በአንድ ቀን ከእስራኤል ይቈርጣል። 15ሽማግሌውና ለፊት የሚያደላው እርሱ ራስ ነው፤ ዐመፅንም የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው። 16ይህን ሕዝብ የሚያመሰግኑ ያስቱአቸዋል፤ ይበሉአቸውም ዘንድ ያስቱአቸዋል፤ 17ሰው ሁሉ ክፉና በደለኛ ነውና፥ አፍም ሁሉ ዐመፅን ይናገራልና፥ ስለዚህ ጌታ በጐልማሶቻቸው ደስ አይለውም፤ ለሙት ልጆቻቸውና ለመበለቶቻቸውም አይራራም። በዚህ ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
18ኀጢአት እንደ እሳት ይነድዳል፤ እሳት እንደ በላችው ደረቅ ሣር ይቃጠላል፤ እንደ ዱር ሣርም ይቃጠላል፤ በተራራዎች ዙሪያ ያለው ሁሉ አብሮ ይቃጠላል። 19በእግዚአብሔር ቍጣ ምድር ሁሉ ትቃጠላለች፤ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም። 20ነገር ግን ሰው ወደ ቀኙ ይመለሳል፤ ይራባልና፤ በግራም በኩል ይበላል፤ አይጠግብምም፤ 21እያንዳንዱም የክንዱን ሥጋ ይበላል፤ ምናሴ ኤፍሬምን፥ ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ እነርሱ በአንድነት የይሁዳ ጠላቶች ይሆናሉና። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 9: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ