መጽሐፈ መሳፍንት 12
12
ዮፍታሔና የኤፍሬም ሰዎች
1የኤፍሬምም ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ወደ ጻፎንም ተሻግረው ዮፍታሔን፥ “ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ስታልፍ ከአንተ ጋር እንድንሄድ ስለምን አልጠራኸንም? ቤትህን በአንተ ላይ በእሳት እናቃጥለዋለን” አሉት። 2ዮፍታሔም፥ “እኔና ሕዝቤ የተገፋን ነን፤ የአሞን ልጆችም በጽኑዕ አሠቃዩን፤ በጠራናችሁም ጊዜ ከእጃቸው አላዳናችሁንም። 3የሚያድን እንደሌለም ባየሁ ጊዜ ሰውነቴን በእጄ አሳልፌ ለሞት በመስጠት ወደ አሞን ልጆች ተሻገርሁ፤ እግዚአብሔርም በፊቴ ጣላቸው፤ ለምንስ ዛሬ ልትወጉኝ ወደ እኔ መጣችሁ?” አላቸው። 4ዮፍታሔም የገለዓድን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፤ ከኤፍሬምም ጋር ተዋጋ፤ ኤፍሬምም፥ “ገለዓዳውያን ሆይ! እናንተ በኤፍሬምና በምናሴ መካከል የተቀመጣችሁ ከኤፍሬም ሸሽታችሁ ነው” ስላሉ የገለዓድ ሰዎች ኤፍሬምን መቱ። 5የገለዓድ ሰዎችም ኤፍሬም በሚያልፍበት በዮርዳኖስ ማዶ ደረሱባቸው። ከዚህ በኋላ ከኤፍሬም ያመለጡት እንሻገር ባሉ ጊዜ የገለዓድ ሰዎች፥ “በውኑ እናንተ ከኤፍሬም ወገን ናችሁን?” ቢሉአቸው “አይደለንም” አሉ። 6እነርሱም፥ “አሁን ሺቦሌት#በዕብ. “ሺቦሌት” በግእዝ “መምሕፃን” ይላል። በሉ” አሉአቸው፤ እነርሱም አጥርተው መናገር አልቻሉምና፥ “ሲቦሌት” አሉ፤ ይዘውም በዮርዳኖስ መሸጋገርያ አረዱአቸው፤ በዚያም ጊዜ ከኤፍሬም አርባ ሁለት ሺህ ሰዎች ወደቁ።
7ዮፍታሔም እስራኤልን ስድስት ዓመት ገዛ። ገለዓዳዊው ዮፍታሔም ሞተ፤ በሀገሩ በገለዓድም ተቀበረ።
8ከእርሱም በኋላ የቤተ ልሔሙ ሐሴቦን እስራኤልን ገዛ። 9ሠላሳ ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ሴቶች ልጆችንም ወለደ፤ ሠላሳ ሴቶች ልጆቹንም ወደ ውጭ ሀገር ዳረ፤ ለወንዶች ልጆቹም ከውጭ ሀገር ሠላሳ ሴቶች ልጆችን አመጣ። እስራኤልንም ሰባት ዓመት ገዛ። 10ሐሴቦንም ሞተ፤ በቤተ ልሔምም ተቀበረ።
11ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎን እስራኤልን ዐሥር ዓመት ገዛ። 12ዛብሎናዊው ኤሎንም ሞተ፤ በዛብሎንም ምድር በኤሎም ተቀበረ።
13ከእርሱም በኋላ የኤፍራታዊው የኤሎን ልጅ ለቦን#ዕብ. “የጲርዓቶናዊው የሄሌል ልጅ አብዶን” ይላል። እስራኤልን ገዛ። 14አርባም ልጆች፥ ሠላሳም የልጅ ልጆች ተወለዱለት፤ በሰባም የአህያ ግልገሎች ላይ ይቀመጡ ነበር። እስራኤልንም ስምንት ዓመት ገዛ። 15የኤፍራታዊው የኤሎን ልጅ ለቦንም ሞተ፤ በተራራማውም በአማሌቃውያን ምድር በኤፍሬም ባለችው በኤፍራታ ተቀበረ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 12: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ