መጽሐፈ መሳፍንት 17
17
ሚካ ያስቀረፃቸው ጣዖቶች
1በተራራማውም በኤፍሬም ሀገር ሚካ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። 2እናቱንም፥ “ከአንቺ ዘንድ የተሰረቀው፥ የረገምሽበትም፥ በጆሮዬም የተናገርሽበት አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር እነሆ፥ በእኔ ዘንድ አለ፤ እኔም ወስጄው ነበር” አላት። እናቱም፥ “ልጄ ሆይ፥ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለችው። 3አንዱን ሺህ አንድ መቶ ብርም ለእናቱ መለሰላት፤ እናቱም፥ “ይህን ብር የተቀረፀ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አድርጌ ከእጄ ስለ ልጄ ለእግዚአብሔር እቀድሰዋለሁ፤ አሁንም ለአንተ እመልሰዋለሁ” አለች። 4ለእናቱም ገንዘቡን መለሰላት እናቱም ብሩን ወስዳ ከእርሱ ሁለቱን መቶ ብር ለአንጥረኛ ሰጠችው፤ እርሱም የተቀረፀ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ምስል አደረገው። በሚካም ቤት አስቀመጡት። 5ሰውዬውም ሚካ የአማልክት ቤት ነበረው፤ ኤፉድና ተራፊም አደረገ፤ ከልጆቹም አንዱን ቀደሰው፤ ካህንም ሆነለት። 6በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።
7በይሁዳ ቤተ ልሔምም ከይሁዳ ወገን የሆነ አንድ ጐልማሳ ነበረ፤ እርሱም ሌዋዊ ነበረ፤ በዚያም ይቀመጥ ነበር። 8ይህም ሰው በአገኘው ስፍራ ይኖር ዘንድ ከይሁዳ ከተማ ከቤተ ልሔም ሄደ፤ በዚያም ያድር ዘንድ ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም ሀገር ወደ ሚካ ቤት ደረሰ። 9ሚካም፥ “ከወዴት መጣህ?” አለው። እርሱም፥ “ከይሁዳ ቤተ ልሔም የሆንሁ ሌዋዊ ነኝ፤ የምቀመጥበትንም ስፍራ ለመሻት እሄዳለሁ” አለው። 10ሚካም፥ “በእኔ ዘንድ ተቀመጥ፤ አባትና ካህንም ሁነኝ፤ እኔም ልብሶችንና ምግብህን፥ በየዓመቱም ዐሥር ብር እሰጥሃለሁ” አለው። 11ሌዋዊዉም ሄደ። ከዚያም ሰው ጋር ይኖር ዘንድ ጀመረ፤ ጐልማሳውም ከልጆቹ እንደ አንዱ ሆነለት። 12ሚካም ሌዋዊዉን እጁን ቀባው፤ ጐልማሳውም ካህን ሆነለት፤ በሚካም ቤት ኖረ። 13ሚካም፥ “ሌዋዊ ካህን ስለ ሆነልኝ እግዚአብሔር መልካም እንዲሠራልኝ አሁን አውቃለሁ” አለ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 17: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ