መጽሐፈ መሳፍንት 7
7
ጌዴዎን ምድያማውያንን ድል እንደ አደረገ
1ጌዴዎን የተባለውም ይሩበኣል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ማልደው ተነሡ፤ በአሮኤድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤ የምድያምም ሰፈር ከእነርሱ ወደ ሰሜን በኩል በሞሬ ኮረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበረ።
2እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፥ “ከአንተ ጋር ያለው ሕዝብ በዝቶአል፤ ስለዚህ እስራኤል፦ እጄ አዳነኝ ብሎ እንዳይታበይብኝ እኔ ምድያምን በእጃቸው አሳልፌ አልሰጣቸውም።” 3እግዚአብሔርም አሁን እንግዲህ፥ “የፈራ፥ የደነገጠም ከገለዓድ ተራራ ተነሥቶ ይመለስ ብለህ በሕዝቡ ጆሮ አውጅ” አለው። ከሕዝቡም ሃያ ሁለት ሺህ ተመለሱ፤ ዐሥርም ሺህ ቀሩ።
4እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፥ “ሕዝቡ ገና ብዙ ነው፤ ወደ ውኃ አውርዳቸው፤ በዚያም እፈትናቸዋለሁ፤ እኔም፦ ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ የምለው እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ እኔም፦ ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ የምለው እርሱ አይሄድም” አለው። 5ሕዝቡንም ወደ ውኃ አወረደ። እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፥ “ውሻ እንደሚጠጣ ውኃ በምላሱ የሚጠጣውን ሁሉ፥ እርሱን ለብቻው አድርገው፤ እንዲሁም ሊጠጣ በጕልበቱ የሚንበረከከውን ሁሉ ለብቻው አድርገው” አለው። 6በእጃቸውም ውኃ ወደ አፋቸው አድርገው የጠጡት ቍጥር ሦስት መቶ ሆነ፤ የቀሩት ሕዝብ ግን ውኃ ሊጠጡ በጕልበታቸው ተንበረከኩ። 7እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፥ “በእጃቸው ውኃ በጠጡት በሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያምንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ የቀሩት ሕዝብ ሁሉ ግን ወደ ስፍራቸው ይመለሱ” አለው። 8የሕዝቡንም ስንቅና ቀንደ መለከት በእጃቸው ወሰዱ፤ የቀሩትንም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ድንኳናቸው ሰደዳቸው፤ ሦስቱን መቶ ሰዎች ግን በእርሱ ዘንድ ጠበቃቸው፤ የምድያምም ሰፈር ከእርሱ በታች በሸለቆው ውስጥ ነበረ።
9በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር፥ “በእጅህ አሳልፌ ሰጥቻቸዋለሁና ተነሥተህ ወደ ሰፈር ውረድ። 10ብቻህንም ለመውረድ ብትፈራ አንተ ከሎሌህ ፋራን ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤ 11የሚናገሩትንም አድምጣቸው፤ ከዚያም በኋላ እጆችህ ይበረታሉ፤ ወደ ሰፈርም ትወርዳለህ” አለው። እርሱም ከሎሌው ፋራን ጋር ከሰፈሩ በአንድ ወገን የአምሳ አለቃ ጦር ወደ ሰፈረበት ወረደ። 12ብዛታቸውም እንደ አንበጣ የሆነ ምድያማውያንና አማሌቃውያን የምሥራቅም ልጆች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት ቍጥር እንደሌለው በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበረ። 13ጌዴዎንም በደረሰ ጊዜ አንድ ሰው ሕልምን ለባልንጀራው ሲያጫውት፥ “እነሆ፥ ሕልም አለምሁ፤ እነሆም፥ አንዲት የገብስ እንጎቻ ወደ ምድያም ሰፈር ተንከባልላ ወረደች፤ ወደ ድንኳኑም ደርሳ እስኪወድቅ ድረስ መታችው፤ ገለበጠችውም፤ ድንኳኑም ወደቀ” ይል ነበር። 14ባልንጀራውም መልሶ፥ “ይህ ነገር ከእስራኤል ሰው ከኢዮአስ ልጅ ከጌዴዎን ሰይፍ በቀር ሌላ አይደለም፤ እግዚአብሔር ምድያምንና ሠራዊቱን ሁሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶአል” አለው።
15ጌዴዎንም ሕልሙንና ትርጓሜዉን በሰማ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ወደ እስራኤልም ሰፈር ተመልሶ፥ “እግዚአብሔር የምድያምን ሠራዊት በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተነሡ” አለ። 16ሦስቱንም መቶ ሰዎች በሦስት ወገን ከፈላቸው፤ በሁሉም እጅ ቀንደ መለከትና ባዶ ማሰሮ፥ በማሰሮዉም ውስጥ ችቦ ሰጣቸው። 17እርሱም፥ “እኔን ተመልከቱ፤ እንዲሁም አድርጉ፤ እነሆም፥ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ በደረስሁ ጊዜ እኔ እንደማደርግ እንዲሁ እናንተ አድርጉ፤ 18እኔ ከእኔም ጋር ያሉት ሁሉ ቀንደ መለከት ስንነፋ፥ እናንተ ደግሞ በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ ቀንደ መለከታችሁን ንፉ፦ ኀይል የእግዚአብሔር፥ ሰይፍ የጌዴዎን በሉ”#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለእግዚአብሔርና ለጌዴዎን በሉ” ይላል። አላቸው።
19ጌዴዎንም፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት መቶ ሰዎች በመካከለኛው ትጋት መጀመሪያ ዘብ ጠባቂዎች ሳይነቁ ወደ ሰፈሩ ዳርቻ መጡ፤ ቀንደ መለከቶችንም ነፉ፤ በእጃቸውም የነበሩትን ማሰሮዎች ሰባበሩ፤ 20ሦስቱም ወገኖች ቀንደ መለከቶችን ነፉ፤ ማሰሮዎችንም ሰበሩ፤ በግራ እጃቸውም ችቦዎችን፥ በቀኝ እጃቸውም ቀንደ መለከቶችን ይዘው እየነፉ፥ “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ” ብለው ጮኹ። 21ሁሉም በየቦታው፥ በሰፈሩ ዙሪያ ቆመ፤ ሠራዊቱም ሁሉ ደንግጠው ሸሹ። 22ሦስቱንም መቶ ቀንደ መለከቶችን ነፉ፤ እግዚአብሔርም የሰውን ሁሉ ሰይፍ በባልንጀራዉና በሠራዊቱ ሁሉ ላይ አደረገ፤ ሠራዊቱም በጽሬራ በኩል እስከ ቤትሲጣ ጋራጋታ ድረስ በጣባት አጠገብ እስካለው እስከ አቤልሜሁላ ዳርቻ ድረስ ሸሸ። 23የእስራኤልም ሰዎች ከንፍታሌምና ከአሴር፥ ከምናሴም ሁሉ ተሰብስበው ምድያምን አሳደዱ።
24ጌዴዎንም፥ “ምድያማውያንን ለመግጠም ውረዱ፥ እስከ ቤትባራም ድረስ ያለውን ውኃ፥ ዮርዳኖስንም፥ ያዙባቸው” ብሎ መልእክተኞችን በኤፍሬም ወዳለው ተራራማ ሀገር ሁሉ ላከ። የኤፍሬምም ሰዎች ሁሉ ተሰብስበው እስከ ቤትባራ ድረስ ውኃውን፥ ዮርዳኖስንም ቀድመው ያዙ። 25የምድያምን ሁለቱን አለቆች ሔሬብንና ዜብን ያዙ፤ ሔሬብንም በሱርኤራብ#ዕብ. “በሔሬብ ዐለት አጠገብ” ይላል። ገደሉት፥ ዜብንም በኢያፌቅ ገደሉት፤ የምድያምንም ሰዎች አሳደዱ፤ የሔሬብንና የዜብንም ራስ ይዘው ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ወደ ጌዴዎን አመጡ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 7: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ