መጽሐፈ መሳፍንት 9
9
አቤሜሌክ
1የይሩበኣል ልጅ አቤሜሌክም ወደ ሰቂማ ወደ እናቱ ወንድሞች ሄደ፤ ለእነርሱም፥ ለእናቱ አባት ቤተ ሰቦችም ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ 2“ለሰቂማ ሰዎች ሁሉ፦ ሰባ የሆኑት የይሩበኣል ልጆች ሁሉ ቢገዙአችሁ ወይስ አንድ ሰው ቢገዛችሁ ምን ይሻላችኋል? ብላችሁ ንገሩአቸው፤ ደግሞም እኔ የአጥንታችሁ ፍላጭ፥ የሥጋችሁ ቍራጭ እንደ ሆንሁ አስቡ።” 3የእናቱም ወንድሞች ይህን ቃል ሁሉ ስለ እርሱ በሰቂማ ሰዎች ሁሉ ጆሮ ተናገሩ፤ እነርሱም፥ “እርሱ ወንድማችን ነው” ብለው ልባቸውን ወደ አቤሜሌክ መለሱት። 4ከበዓልም#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከበዓልብሪት ቤት” ይላል። ቤት ሰባ ብር ሰጡት፤ በዚያም አቤሜሌክ ወንበዴዎችንና አስደንጋጮችን ቀጠረበት፤ እነርሱም ተከትለውት ሄዱ። 5ወደ አባቱም ቤት ወደ ኤፍራታ ገባ፤ ሰባ የሆኑትን የይሩበኣልን ልጆች ወንድሞቹን በአንድ ድንጋይ ላይ ገደላቸው፤ ትንሹ የይሩበኣል ልጅ ኢዮአታም ግን ተሸሽጎ ነበርና ተረፈ። 6የሰቂማም ሰዎች ሁሉ፥ የመሐሎንም ቤት ሁሉ ተሰበሰቡ፤ ሄደውም በሰቂማ በዐምዱ አጠገብ ባለው የወይራ ዛፍ በታች አቤሜሌክን አነገሡ።
7ይህንም ነገር ለኢዮአታም በነገሩት ጊዜ፥ ሄዶ በገሪዛን ተራራ ራስ ላይ ቆመ፤ ድምፁንም አንሥቶ አለቀሰ፤ እንዲህም አላቸው፥ “የሰቂማ ሰዎች ሆይ! ስሙኝ እግዚአብሔርም ይስማችሁ። 8አንድ ጊዜ ዛፎች በላያቸው ንጉሥ ሊያነግሡ ሄዱ፤ ወይራንም፦ በእኛ ላይ ንገሺልን አሉአት። 9ወይራዋ ግን፦ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያከብርበትን ቅባቴን ትቼ በዛፎች ላይ ለመንገሥ ልሂድን? አለቻቸው። 10ዛፎችም በለሲቱን፦ መጥተሽ በላያችን ንገሺልን አሉአት። 11በለሷ ግን፦ ጣፋጭነቴንና መልካሙን ፍሬዬን ትቼ በዛፎች ላይ እነግሥ ዘንድ ልሂድን? አለቻቸው። 12ዛፎችም ሁሉ ወይኑን፦ መጥተህ በላያችን ንገሥ አሉት። 13ወይኑም፦ እግዚአብሔርንና ሰውን ደስ የሚያሰኘውን የወይን ጠጅነቴን ትቼ በዛፎች ላይ እነግሥ ዘንድ ልሂድን? አላቸው። 14ዛፎችም ዶግን፦ መጥተሽ በላያችን ንገሺ አሉአት፤ 15ዶግም ዛፎቹን፦ በእውነት እኔን በእናንተ ላይ ካነገሣችሁኝ እሳት ከዶግ ወጥቶ የሊባኖስን ዝግባ ካልበላው ከጥላዬ በታች ታርፉ ዘንድ ኑ አለቻቸው። 16አሁን እንግዲህ አቤሜሌክን በማንገሣችሁ እውነትንና ቅንነትን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ ለይሩበኣልም፥ ለቤቱም በጎ አድርጋችሁ እንደሆነና እንደ እጁም ዋጋ መጠን ለእርሱ የተገባውን አድርጋችሁ እንደ ሆነ፥ 17አባቴስ ለእናንተ እንደ ተጋደለ፥ በፊታችሁም ሰውነቱን ለሞት አሳልፎ እንደ ሰጠ፥ ከምድያምም እጅ እንደ አዳናችሁ፥ 18እናንተም ዛሬ በአባቴ ቤት ተነሥታችኋል፤ ሰባ የሆኑትን ልጆቹንም በአንድ ድንጋይ ላይ ገድላችኋል፤ ወንድማችሁም ስለሆነ የዕቅብቱን ልጅ አቤሜሌክን በሰቂማ ሰዎች ላይ አንግሣችኋል፥ 19ለይሩበኣልና ለቤቱ እውነትንና ቅንነትን ዛሬ አድርጋችሁ እንደ ሆነ የተባረካችሁ ሁኑ፤ በአቤሜሌክም ደስ ይበላችሁ፤ እርሱም ደግሞ በእናንተ ደስ ይበለው፤ 20እንዲህ ባይሆን ግን ከአቤሜሌክ እሳት ትውጣ፤ የሰቂማንም ሰዎች፥ የመሐሎንንም ቤት ትብላ፤ ያም ባይሆን ከሰቂማ ሰዎች ከመሐሎንም ቤት እሳት ትውጣ፤ አቤሜሌክንም ትብላው።” 21ኢዮአታምም ሸሽቶ አመለጠ፤ ወንድሙን አቤሜሌክንም ፈርቶ ወደ ብኤር ሄደ፤ በዚያም ተቀመጠ።
የአቤሜሌክ መውደቅ
22አቤሜሌክም በእስራኤል ላይ ሦስት ዓመት ገዥ ሆነ። 23እግዚአብሔርም በአቤሜሌክና በሰቂማ ሰዎች መካከል ክፉን መንፈስ ሰደደ፤ የሰቂማም ሰዎች የአቤሜሌክን ቤት ከዱት። 24ይህም የሆነው፥ በሰባው የይሩበኣል ልጆች ላይ የተደረገው ዐመፅ እንዲመጣ፥ ደማቸውም በገደላቸው በወንድማቸው በአቤሜሌክ ላይ፥ ወንድሞቹንም እንዲገድል እጆቹን ባጸኑአቸው በሰቂማ ሰዎች ላይ እንዲሆን ነው። 25የሰቂማም ሰዎች በተራሮች ራስ ላይ ድብቅ ጦር አደረጉ፤ መንገድ ተላላፊዎችንም ሁሉ ይዘርፉ ነበር፤ ለአቤሜሌክም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለንጉሥ አቤሜሌክ” ይላል። ይህን አወሩለት።
26የአቤድም ልጅ ገዓል ከወንድሞቹ ጋር መጣ፤ የሰቂማ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ። 27ወደ እርሻውም ወጡ፤ ወይናቸውንም ለቀሙ፤ ጠመቁትም፤ የደስታም በዓል አደረጉ፤ ወደ አምላካቸውም ቤት ገቡ፤ በሉም፤ ጠጡም፤ አቤሜሌክንም ረገሙት። 28የአቤድም ልጅ ገዓል፥ “አቤሜሌክ ማን ነው? እንገዛለትስ ዘንድ የሴኬም ልጅ ማን ነው? እርሱ የይሩበኣል ልጅ አይደለምን? ዜቡልስ የእርሱ ጠባቂ አይደለምን? ከሴኬም አባት ከኤሞር ሰዎች ጋርስ አገልጋዩ አይደለምን? ስለምንስ ለዚህ እንገዛለን? 29ይህ ሕዝብ ከእጄ በታች ቢሆን ኖሮ አቤሜሌክን አሳድደው ነበር” አለ። አቤሜሌክንም፥ “ሠራዊትህን አብዝተህ ና፤ ውጣ” አለው።
30የከተማዪቱ ገዥ ዜቡልም የአቤድን ልጅ የገዓልን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ። 31እንዲህም ብሎ ወደ አቤሜሌክ ከእጅ መንሻ ጋር መልእክተኞችን ላከ፥ “እነሆ፥ የአቤድ ልጅ ገዓልና ወንድሞቹ ወደ ሰቂማ መጥተዋል፤ እነሆም፥ በአንተ ምክንያት ከተማዪቱን ይወጓታል። 32አሁንም አንተና ከአንተ ጋር ያሉት ሕዝብ በሌሊት ተነሡ፤ በሜዳም ሸምቁ፤ 33ነገም ፀሐይ በወጣች ጊዜ ማልደህ ተነሣ፤ ከተማዪቱንም ክበባት፤ እነሆም፥ እርሱና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብ በአንተ ላይ በወጡ ጊዜ እጅህ እንዳገኘች አድርግበት።”
34አቤሜሌክና ከእርሱም ጋር ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሌሊት መጡ። ሰቂማንም በአራት ወገን ከበቡአት። 35በነጋም ጊዜ የአቤድ ልጅ ገዓል ወጥቶ በከተማዪቱ መግቢያ በር ቆመ፤ አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉት ሕዝብም ከሸመቁበት ስፍራ ተነሡ። 36የአቤድ ልጅ ገዓልም ሕዝቡን ባየ ጊዜ ዜቡልን፥ “እነሆ፥ ከተራሮች ራስ ሕዝብ ይወርዳል” አለው። ዜቡልም፥ “ሰዎችን የሚመስለውን የተራሮችን ጥላ ታያለህ” አለው። 37ገዓልም ደግሞ፥ “እነሆ፥ ሕዝብ በባሕር በኩል ወደ ምድር መካከል ይወርዳል፤ የአንድም አለቃ ሠራዊት በአድባሩ ዛፍ መንገድ አንጻር ይመጣል” ብሎ ተናገረ። 38ዜቡልም፥ “እንገዛለት ዘንድ አቤሜሌክ ማን ነው? ያልህበት አፍህ አሁን የት አለ? ይህ የናቅኸው ሕዝብ አይደለምን? አሁንም ወጥተህ ከእነርሱ ጋር ተዋጋ” አለው። 39ገዓልም በሰቂማ ሰዎች ፊት ወጣ፤ ከአቤሜሌክም ጋር ተዋጋ። 40አቤሜሌክም አሳደደው፤ በፊቱም ሸሸ፤ እስከ ከተማው በርም አደባባይ ድረስ ብዙዎች ተጐድተው ወደቁ።
41አቤሜሌክም በአሪማ ተቀመጠ፤ ዜቡልም ገዓልንና ወንድሞቹን በሰቂማ እንዳይኖሩ ከለከላቸው። 42በነጋውም ሕዝቡ ወደ እርሻ ወጡ፤ ለአቤሜሌክም ነገሩት። 43ሕዝቡንም ወስዶ በሦስት ወገን ከፈላቸው፤ በሜዳም ሸመቀ፤ ተመለከተም፤ እነሆም፥ ሕዝቡ ከከተማ ወጡ፤ ተነሣባቸውም፤ ገደላቸውም። 44አቤሜሌክም ከእርሱም ጋር ያሉት ሠራዊት በከተማዪቱ መግቢያ በር ሸምቀው ቆሙ። እነዚያ ሁለቱ ሠራዊት ግን ወደ ጫካው ተበትነው አጠፉአቸው። 45አቤሜሌክም በዚያ ቀን ሁሉ ከከተማዪቱ ጋር ተዋጋ፤ ከተማዪቱንም ይዞ በእርስዋ የነበሩትን ሕዝብ ገደለ፤ ከተማዪቱንም አፈረሰ፤ ጨውም ዘራባት።
46በሰቂማም ግንብ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ በዓል ቤት#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ቤትኤልብሪት” ይላል። ወደ ምሽጉ ውስጥ ገቡ። 47ለአቤሜሌክም በሰቂማ ግንብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው እንደ ተሰበሰቡ ነገሩት። 48አቤሜሌክና ከእርሱ ጋር ያሉትም ሕዝብ ሁሉ ወደ ሄርሞን#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሰልሞን” ይላል። ተራራ ወጡ፤ አቤሜሌክም በእጁ መጥረቢያ ወስዶ የዛፉን ቅርንጫፍ ቈረጠ፤ አንሥቶም በጫንቃው ላይ ተሸከመው፤ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሕዝብ፥ “እኔ ሳደርግ ያያችሁትን፥ እናንተም ፈጥናችሁ እኔ እንዳደረግሁ አድርጉ” አላቸው። 49ሕዝቡም ሁሉ እንዲሁ እያንዳንዳቸው የዛፉን ቅርንጫፎች ቈረጡ፤ አቤሜሌክንም ተከትለው በምሽጉ ዙሪያ አኖሩአቸው፤ ምሽጉንም በላያቸው በእሳት አቃጠሉት፤ የሰቂማም ግንብ ሰዎች ሁሉ ደግሞ አንድ ሺህ የሚያህሉ ወንድና ሴት ሞቱ።
50አቤሜሌክም ወደ ቴቤስ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከቤትኤልብሪት ሄደ” ይላል። መጣ። 51በእርስዋም ተቀመጠ፤ እጅም አደረጋት። በከተማዪቱም ውስጥ ብርቱ ግንብ ነበረ፤ የከተማዪቱም ሰዎች ሁሉ፥ ወንዱና ሴቱ ሁሉ፥ ወደዚያ ሸሹ፤ ደጁንም በኋላቸው ዘጉ፤ ወደ ግንቡም ሰገነት ላይ ወጡ። 52አቤሜሌክም ወደ ግንቡ ሄደ። እነርሱም ተዋጉት። አቤሜሌክም በእሳት ሊያቃጥለው ወደ ግንቡ ደጅ ቀረበ። 53አንዲትም ሴት በአቤሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ ጣለችበት፤ አናቱንም ሰበረችው። 54እርሱም ፈጥኖ ጋሻ ዣግሬውን ጠርቶ፥ “ሴት ገደለችው እንዳይሉ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ” አለው፤ ጐልማሳውም ወጋው፤ አቤሜሌክም ሞተ። 55የእስራኤልም ሰዎች አቤሜሌክ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እያንዳንዱ ወደ ስፍራው ተመለሰ። 56እንዲሁ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል አቤሜሌክ በአባቱ ቤት ላይ ያደረገውን ክፋት እግዚአብሔር መለሰበት። 57እግዚአብሔርም የሰቂማን ሰዎች ክፋት ሁሉ በራሳቸው ላይ መለሰባቸው፤ የይሩበኣል ልጅ የኢዮአታምም ርግማን ደረሰባቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 9: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ