ትንቢተ ኤርምያስ 16
16
ስለ ኤርምያስ ሕይወት የእግዚአብሔር ፈቃድ
1የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም አትውለድ። 3እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ስለ ተወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች፥ ስለ ወለዱአቸውም ስለ እናቶቻቸው፥ በዚህችም ምድር ስለ ወለዱአቸው ስለ አባቶቻቸው እንዲህ ይላልና፦ 4“በክፉ ሞት ይሞታሉ፤ አይለቀስላቸውም፤ አይቀበሩምም፤ ነገር ግን በመሬት ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ፤ በሰይፍም ይወድቃሉ፤ በራብም ይጠፋሉ፤ ሬሳዎቻቸውም ለሰማይ ወፎችና ለዱር አራዊት መብል ይሆናሉ።”
5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰላሜን፥ ቸርነቴንና ምሕረቴን፥#“ቸርነትንና ምሕረትን” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ከዚህ ሕዝብ አስወግጄአለሁና ልቅሶ ወዳለበት ቤት አትግባ፤ ታለቅስና ታዝንም ዘንድ አትሂድ። 6ታላላቆችና ታናናሾች በዚች ምድር ይሞታሉ ፥ አይቀበሩም#“ታላላቆችና ታናናሾች በዚች ምድር ይሞታሉ ፤ አይቀበሩም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሰዎችም አያለቅሱላቸውም፤ ስለ እነርሱም ፊት አይነጩላቸውም፤ ራስንም አይላጩላቸውም፤ 7ሰዎችም ስለ ሞቱት ለማጽናናት የእዝን እንጀራ አይቈርሱላቸውም፤ ስለ አባታቸውና ስለ እናታቸውም የመጽናናት ጽዋ አያጠጡአቸውም። 8ትበላና ትጠጣ ዘንድ ከእነርሱ ጋር ለመቀመጥ ወደ ግብዣ ቤት አትግባ።” 9ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በዐይናችሁ ፊት በዘመናችሁም የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ ከዚህ ስፍራ አስቀራለሁ።
10“ለዚህም ሕዝብ ይህን ቃል ሁሉ በተናገርህ ጊዜ፦ ይህን ሁሉ ትልቅ የሆነ ክፉ ነገርን ስለ ምን እግዚአብሔር ተናገረብን? በደላችንስ ምንድን ነው? በአምላካችንስ በእግዚአብሔር ፊት ያደረግነው ኀጢአት ምንድን ነው? ቢሉህ፥ 11አንተ እንዲህ ትላቸዋለህ፦ አባቶቻችሁ እኔን ስለ ተዉ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሌሎችንም አማልክት ተከተሉ፤ አመለኩአቸውም፤ ሰገዱላቸውም፤ እነርሱም ትተውኛል፤ ሕጌንም አልጠበቁም፤ 12እናንተም ከአባቶቻችሁ ይልቅ ክፉ አድርጋችኋል፤ እነሆም ሁላችሁ እንደ ክፉ ልባችሁ ፍላጎት ሄዳችኋል፤ እኔንም አልሰማችሁም። 13ስለዚህ ከዚች ምድር እናንተና አባቶቻችሁ ወደ አላወቃችኋት ምድር እጥላችኋለሁ፤ በዚያም ምሕረትን ለማያደርጉላችሁ ሌሎች አማልክት ቀንና ሌሊት ታገለግላላችሁ።”#ዕብ. “ምሕረትንም አላደርግላችሁምና በዚያ ሌሎችን አማልክት ቀንና ሌሊት ታመልካላችሁ” ይላል።
ከምርኮ ስለ መመለስ
14ስለዚህ እነሆ፥ “የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥” ይላል እግዚአብሔር፤ 15ነገር ግን፥ “የእስራኤልን ልጆች ከሰሜን ምድር፥ ከተሰደዱበትም ምድር ሁሉ ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን! ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።
ስለሚመጣው ቅጣት
16“እነሆ፥ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እልካለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ያጠምዱአቸዋል፤ ከዚያም በኋላ ብዙ አድዳኞችን እልካለሁ፤ እነርሱም ከየተራራውና ከየኮረብታው ሁሉ ከየድንጋዩም ስንጣቂ ውስጥ ያድድኑአቸዋል። 17ዐይኖች በመንገዳቸው ሁሉ ይመለከታሉ፤ ከፊቴም አልተሰወሩም፤ ኀጢአታቸውም ከዐይኖች አልተሸሸገም። 18ምድሬንም በተጠሉ በጣዖቶቻቸው#“በጣዖቶቻቸው” የሚለው በዕብ. ብቻ። ሬሳዎች አርክሰዋልና፥ ርስቴንም አስጸያፊ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋልና አስቀድሜ የበደላቸውንና የኀጢአታቸውን ዕዳ ሁለት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ።”
የኤርምያስ ጸሎት
19ጌታ ሆይ! አንተ ኀይሌና ረዳቴ፥ በመከራም ቀን መጠጊያዬ ነህ፤ ከምድር ዳርቻ አሕዛብ ወደ አንተ መጥተው፥ “በእውነት አባቶቻችን ውሸትንና ከንቱን ነገር ለምንም የማይረባቸውን ጣዖትን ሠርተዋል” ይላሉ። 20በውኑ ሰው አማልክት ያልሆኑትን ለራሱ አማልክትን አድርጎ ይሠራልን?
21“ስለዚህ እነሆ በዚህ ወራት አስታውቃቸዋለሁ፤ እጄንና ኀይሌንም አሳያቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ያውቃሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 16: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ