ትንቢተ ኤርምያስ 18
18
የሸክላውና የሸክላ ሠሪው ምሳሌ
1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል፥ እንዲህም አለው፦ 2“ተነሥተህ ወደ ሸክላ ሠሪው ቤት ውረድ፤ በዚያም ቃሌን አሰማሃለሁ።” 3ወደ ሸክላ ሠሪውም ቤት ወረድሁ፤ እነሆም ሥራውን በዓለት ላይ ሲሠራ አገኘሁት። 4ከጭቃም ይሠራው የነበረው ዕቃ ከሸክላ ሠሪው እጅ ወደቀ፤ ሸክላ ሠሪውም እንደ ወደደ ዳግመኛ ሌላ ዕቃ አድርጎ ሠራው።
5የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። 6“የእስራኤል ቤት ሆይ! ይህ ሸክላ ሠሪ እንደሚሠራ በውኑ እኔ በእናንተ ዘንድ መሥራት አይቻለኝምን? እነሆ ጭቃው በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ፥ እንዲሁ እናንተ በእኔ እጅ አላችሁ። 7አጠፋቸውና እደመስሳቸው ዘንድ በሕዝብ ላይና በመንግሥት ላይ ቍርጥ ነገርን ተናገርሁ፤ 8ስለ እነርሱ የተናገርሁባቸው ሕዝብ ከክፋታቸው ቢመለሱ፥ እኔ አደርግባቸው ዘንድ ካሰብሁት ክፉ ነገር እጸጸታለሁ። 9በሕዝብም በመንግሥታትም ላይ እሠራቸውና እተክላቸው ዘንድ ቍርጥ ነገርን እናገራለሁ፤ 10በፊቴ ክፉን ነገር ቢያደርጉ ቃሌንም ባይሰሙ፥ እኔ አደርግላቸው ዘንድ ስለ ተናገርሁት መልካም ነገር እጸጸታለሁ።”
11አሁን እንግዲህ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ ክፉ ነገር እፈጥርባችኋለሁ፤ ምክርንም እመክርባችኋለሁ፤ አሁንም ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ መንገዳችሁንና ሥራችሁንም አቅኑ ብለህ ተናገራቸው።” 12እነርሱ ግን፥ “እንጨክናለን፤ ክዳታችንን ተከትለን እንሄዳለን፥ ሁላችንም ክፉ ልባችንን ደስ የሚያሰኛትን እናደርጋለን” አሉ።
13ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእስራኤል ድንግል ያደረገችውን በጣም የሚያስደነግጠውን ነገር የሚሰሙት እንዳለ አሕዛብን ጠይቁ።” 14ምንጭ ከዓለት ይጠፋልን? በረዶስ ከሊባኖስ ይጠፋልን? ወራጅ ውኃስ በኀይለኛ ነፋስ ይመለሳልን?#ዕብ. “በውኑ የሊባኖስ በረዶ የምድረ በዳውን ድንጋይ ይተዋልን? ወይስ ከሩቅ የምትመጣው ቀዝቃዛዪቱ ፈሳሽ ውኃ ትደርቃለችን” ይላል። 15ሕዝቤ ግን ረስተውኛል፤ ለከንቱ ነገርም አጥነዋል፤ የቀድሞውን ጐዳና ትተው ወደ ጠማማውና ወደ ሰንከልካላው መንገድ ለመሄድ በመንገዳቸው ተሰናከሉ። 16ምድራቸውን ለጥፋትና ለዘለዓለም ማፍዋጫ አድርገዋል፤ የሚያልፍባት ሁሉ ይደነቃል፤ ራሱንም ያነቃንቃል። 17በጠላት ፊት እንደ በረሃ ዐውሎ#ዕብ. “ምሥራቅ” ይላል። ነፋስ እበትናቸዋለሁ፤ በጥፋታቸውም ቀን ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አላሳያቸውም።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የጥፋት ቀናቸውን አሳያቸዋለሁ” ይላል።
በኤርምያስ ላይ የተደረገ ሴራ
18እነርሱም፥ “ሕግ ከካህን፥ ምክርም ከጠቢብ፥ ቃልም ከነቢይ አይጠፋምና ኑ፤ በኤርምያስ ላይ ምክርን እንምከር። ኑ፤ በምላስ እንምታው፤ ቃሉንም ሁሉ አናዳምጥ” አሉ።
19“አቤቱ! አድምጠኝ፤ የክርክሬንም ቃል ስማ። 20ለሰውነቴ ጕድጓድን ቈፍረዋል፤ በውኑ በመልካም ፈንታ ክፉ ይመለሳልን? ስለ እነርሱ በመልካም እናገር ዘንድ፥ ቍጣህንም ከእነርሱ ትመልስ ዘንድ በፊትህ እንደ ቆምሁ አስብ። 21ስለዚህ ልጆቻቸውን ለራብ ስጥ፤ ለሰይፍም እጅ አሳልፈህ ስጣቸው፤ ሚስቶቻቸውም የወላድ መካንና መበለቶች ይሁኑ፤ ወንዶቻቸውም በሞት ይጥፉ፤ ጐልማሶቻቸውም በጦርነት ጊዜ በሰይፍ ይመቱ። 22ሊይዙኝ ጕድጓድ ቈፍረዋልና፥ ለእግሮችም ወጥመድ ሸሽገዋልና፥ በቤታቸው ጩኸት ይሰማ፤ ድንገትም በላያቸው ወንበዴን አምጣባቸው። 23አንተ ግን አቤቱ! ይገድሉኝ ዘንድ በላዬ የመከሩትን ምክር ሁሉ ታውቃለህ፤ በደላቸውንም ይቅር አትበል፤ ኀጢአታቸውንም ከፊትህ አትደምስስ፤ በፊትህም ይውደቁ፤ በቍጣህ ጊዜ እንዲሁ አድርግባቸው።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 18: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ