አይሁድም የዚያን ያየውን ሰው ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕዉር ሆኖ እንደ ተወለደ፥ እንዳየም አላመኑም። “ዕዉር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? እንግዲያ አሁን እንዴት ያያል?” ብለው ጠየቁአቸው። ወላጆቹም መልሰው እንዲህ አሉ፥ “ይህ ልጃችን እንደ ሆነ፥ ዕዉር ሆኖም እንደ ተወለደ እናውቃለን። አሁን ግን እንዴት እንደሚያይ ዐይኖቹንም ማን እንደ አበራለት አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ ዐዋቂ ነውና፤ ስለ ራሱም መናገር ይችላልና።” ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ፥ “እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ በእርሱ የሚያምን ቢኖር ከምኵራብ ይውጣ” ብለው አይሁድ ተስማምተው ነበርና። ስለዚህም ወላጆቹ፥ “ዐዋቂ ነውና እርሱን ጠይቁት” አሉ። ዕውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፥ “ሂድ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርብ፤ ይህ ሰው ኀጢኣተኛ እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን” አሉት። ያም ሰው መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እርሱ ኀጢኣተኛ እንደ ሆነ እኔ አላውቅም፤ እኔ ዕዉር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ብቻ አውቃለሁ።” ዳግመኛም፥ “ምን አደረገልህ? ዐይኖችህንስ እንደምን አበራልህ?” አሉት። እርሱም መልሶ፥ “አትሰሙኝም እንጂ ነገርኋችሁ፤ እንግዲህ ደግሞ ምን ልትሰሙ ትሻላችሁ? እናንተም ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ሰደቡት፤ እንዲህም አሉት፥ “አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሁን፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን። እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተነጋገረው እናውቃለን፤ ይህን ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም።” ያም ሰው መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ከወዴት እንደ ሆነ፥ አታውቁትምና ይህ እጅግ ድንቅ ነው፤ ነገር ግን ዐይኖችን አበራልኝ። እኛም እግዚአብሔርን የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እርሱን ይሰማዋል እንጂ ኃጥኣንን እንደማይሰማቸው እናውቃለን። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ዕዉር ሆኖ የተወለደውን ዐይኖች ያበራ አልተሰማም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ማድረግ ባልቻለም ነበር።” እነርሱም መልሰው፥ “ራስህ በኀጢኣት የተወለድህ አንተ እኛን ታስተምረናለህን?” አሉት፤ ወደ ውጭም አወጡት። ጌታችን ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ፤ አገኘውምና፥ “አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” አለው። ያ ሰውም፥ “አቤቱ፥ አምንበት ዘንድ እርሱ ማነው?” ብሎ መለሰለት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “የምታየው፥ ከአንተ ጋርም የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው። እርሱም፥ “አቤቱ፥ አምናለሁ” ብሎ ሰገደለት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ የማያዩት እንዲያዩ፥ የሚያዩትም እንዲታወሩ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቻለሁ” አለው። ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሲናገር ሰምተው፥ “እኛ ደግሞ ዕዉሮች ነን?” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ዕዉሮችስ ብትሆኑ ኀጢኣት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ትላላችሁ፤ አታዩምም፤ ስለዚህም ኀጢኣታችሁ ጸንቶ ይኖራል” አላቸው።
የዮሐንስ ወንጌል 9 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 9:18-41
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች