ዮሐንስ 9:18-41
ዮሐንስ 9:18-41 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አይሁድም የዚያን ያየውን ሰው ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕዉር ሆኖ እንደ ተወለደ፥ እንዳየም አላመኑም። “ዕዉር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? እንግዲያ አሁን እንዴት ያያል?” ብለው ጠየቁአቸው። ወላጆቹም መልሰው እንዲህ አሉ፥ “ይህ ልጃችን እንደ ሆነ፥ ዕዉር ሆኖም እንደ ተወለደ እናውቃለን። አሁን ግን እንዴት እንደሚያይ ዐይኖቹንም ማን እንደ አበራለት አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ ዐዋቂ ነውና፤ ስለ ራሱም መናገር ይችላልና።” ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ፥ “እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ በእርሱ የሚያምን ቢኖር ከምኵራብ ይውጣ” ብለው አይሁድ ተስማምተው ነበርና። ስለዚህም ወላጆቹ፥ “ዐዋቂ ነውና እርሱን ጠይቁት” አሉ። ዕውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፥ “ሂድ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርብ፤ ይህ ሰው ኀጢኣተኛ እንደ ሆነ እኛ እናውቃለን” አሉት። ያም ሰው መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “እርሱ ኀጢኣተኛ እንደ ሆነ እኔ አላውቅም፤ እኔ ዕዉር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ብቻ አውቃለሁ።” ዳግመኛም፥ “ምን አደረገልህ? ዐይኖችህንስ እንደምን አበራልህ?” አሉት። እርሱም መልሶ፥ “አትሰሙኝም እንጂ ነገርኋችሁ፤ እንግዲህ ደግሞ ምን ልትሰሙ ትሻላችሁ? እናንተም ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁን?” አላቸው። እነርሱም ሰደቡት፤ እንዲህም አሉት፥ “አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሁን፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን። እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተነጋገረው እናውቃለን፤ ይህን ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም።” ያም ሰው መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ከወዴት እንደ ሆነ፥ አታውቁትምና ይህ እጅግ ድንቅ ነው፤ ነገር ግን ዐይኖችን አበራልኝ። እኛም እግዚአብሔርን የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እርሱን ይሰማዋል እንጂ ኃጥኣንን እንደማይሰማቸው እናውቃለን። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ዕዉር ሆኖ የተወለደውን ዐይኖች ያበራ አልተሰማም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ማድረግ ባልቻለም ነበር።” እነርሱም መልሰው፥ “ራስህ በኀጢኣት የተወለድህ አንተ እኛን ታስተምረናለህን?” አሉት፤ ወደ ውጭም አወጡት። ጌታችን ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ፤ አገኘውምና፥ “አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” አለው። ያ ሰውም፥ “አቤቱ፥ አምንበት ዘንድ እርሱ ማነው?” ብሎ መለሰለት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “የምታየው፥ ከአንተ ጋርም የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው። እርሱም፥ “አቤቱ፥ አምናለሁ” ብሎ ሰገደለት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ የማያዩት እንዲያዩ፥ የሚያዩትም እንዲታወሩ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቻለሁ” አለው። ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሲናገር ሰምተው፥ “እኛ ደግሞ ዕዉሮች ነን?” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ዕዉሮችስ ብትሆኑ ኀጢኣት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ትላላችሁ፤ አታዩምም፤ ስለዚህም ኀጢኣታችሁ ጸንቶ ይኖራል” አላቸው።
ዮሐንስ 9:18-41 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አይሁድ ወደ ወላጆቹ ልከው እስኪያስጠሯቸው ድረስ፣ ሰውየው ዐይነ ስውር እንደ ነበረና እንዳየ አላመኑም ነበር። እነርሱም፣ “ዐይነ ስውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” አሏቸው። ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ልጃችን መሆኑንና ዐይነ ስውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ አሁን ግን እንዴት ማየት እንደ ቻለና ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም። ሙሉ ሰው ስለ ሆነ፣ ስለ ራሱ መናገር ይችላልና እርሱን ጠይቁት።” ኢየሱስን፣ ክርስቶስ ነው ብሎ የመሰከረ ሁሉ ከምኵራብ እንዲባረር አይሁድ አስቀድመው ወስነው ስለ ነበር፣ ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁድን ፈርተው ነው። ስለዚህ ወላጆቹ፣ “ሙሉ ሰው ስለ ሆነ እርሱን ጠይቁት” አሉ። ዐይነ ስውር የነበረውንም ሰው ዳግመኛ ጠርተው፣ “አንተ ሰው፤ እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። እርሱም፣ “ኀጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ ነገር ግን ዐይነ ስውር እንደ ነበርሁ፤ አሁን ግን እንደማይ ይህን አንድ ነገር ዐውቃለሁ!” አለ። እነርሱም፣ “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይንህን ከፈተ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፣ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አላዳመጣችሁኝም፤ ለምን እንደ ገና መስማት ፈለጋችሁ? እናንተም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትሻላችሁ?” አለ። ከዚህ በኋላ በርሱ ላይ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ አሉት፤ “የዚህ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛስ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን! እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ መጣ እንኳ አናውቅም።” ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እናንተ ከየት እንደ መጣ አለማወቃችሁ የሚያስደንቅ ነው፤ ይሁን እንጂ እርሱ ዐይኖቼን ከፈተልኝ። እግዚአብሔር የሚሰማው፣ የሚፈራውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን እንጂ፣ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዐይን የከፈተ አለ ሲባል፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ማንም ሰምቶ አያውቅም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ይህን ማድረግ ባልቻለ ነበር።” እነርሱም፣ “ሁለንተናህ በኀጢአት ተነክሮ የተወለድህ፣ አንተ እኛን ለማስተማር እንዴት ትደፍራለህ?” ሲሉ መለሱለት፤ አባረሩትም። ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ፣ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታዬ፤ አምንበት ዘንድ እርሱ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አይተኸዋል፤ አሁንም ከአንተ ጋራ የሚነጋገረው እርሱ ነው” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም፣ “ዕውሮች እንዲያዩ፣ የሚያዩም እንዲታወሩ፣ ለፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ። ከርሱ ጋራ ከነበሩት ፈሪሳውያን አንዳንዶቹ ይህን ሰምተው፣ “ምን ማለትህ ነው? ታዲያ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነው?” አሉት። ኢየሱስም፣ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኀጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፣ ኀጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።
ዮሐንስ 9:18-41 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አይሁድ የዚያን ያየውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ ዕውር እንደ ነበረ እንዳየም ስለ እርሱ አላመኑም፥ እነርሱንም፦ “እናንተ ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል?” ብለው ጠየቁአቸው። ወላጆቹም መልእሰው፦ “ይህ ልጃችን እንደ ሆነ ዕውርም ሆኖ እንደ ተወለደ አናውቃለን፤ ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፥ ወይም ዓይኖቹን ማን እንደ ከፈተ እኛ አናውቅም፤ ጠይቁት እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ ራሱ ይናገራል” አሉ። ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህን አሉ፤ እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ክምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና። ስለዚህ ወላጆቹ፦ “ሙሉ ሰው ነው፥ ጠኡቁት” አሉ። ስለዚህ ዕውር የነበረው ሰው ሁለተኛ ጠርተው፦ “እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። እርሱም መልሶ፦ “ኃጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ ይህን አንድ ነገር አውቃለሁ” አለ። ደግመውም፦ “ምን አደረገህ? እንዴትስ ዓይኖችህን ከፈተ?” አሉት። እርሱም መልሶ፦ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ አልሰማችሁምም፤ ስለ ምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትወዳላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ልትሆኑ ትወዳላችሁን?” አላቸው። ተሳድበውም፦ “አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ፥ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፥ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም” አሉት። ሰውዬው መለሰ እንዲህም አላቸው፦ “ከወዴት እንደ ሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፥ ዳሩ ግን ዓይኖቼን ከፈተ። እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን። ዕውር ሆኖ የተወለደውን ዓይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር።” መልሰው፦ “አንተ ሁለንተናህ በኃጢአት ተወልድህ፥ አንተም እኛን ታስተምረናለህን?” አሉት። ወደ ውጭም አወጡት። ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ ያገኘውም፦ “አንተ በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህን?” አለው። እርሱም መልሶ፦ “ጌታ ሆይ፥ በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” አለ። ኢየሱስም፦ “አይተኸዋልም ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው” አለው። እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ አምናለሁ” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም፦ “የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ” አለ። ከፈሪሳውያንም ከእርሱ ጋር የነበሩት ይህን ሰምተው፦ “እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን?” አሉት። ኢየሱስም አላቸው፦ “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን፦ ‘እናያለን’ ትላላችሁ፤ ኃጢአታችሁ ይኖራል።
ዮሐንስ 9:18-41 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህ ሰው ዕውር እንደ ነበረና ዐይኖቹም በኋላ እንዴት እንደ ተከፈቱ ወላጆቹን ጠርተው እስከ ጠየቁአቸው ድረስ የአይሁድ ባለ ሥልጣኖች አላመኑም ነበር። ስለዚህ ወላጆቹን፥ “ዕውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? አሁንስ እንዴት ማየት ቻለ?” ሲሉ ጠየቁአቸው። ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይህ ሰው ልጃችን መሆኑንና ዕውር ሆኖ መወለዱን እናውቃለን፤ ነገር ግን አሁን እንዴት እንደሚያይና ዐይኖቹንም ማን እንደአበራለት አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ እርሱ በዕድሜው ሙሉ ሰው ስለ ሆነ ስለ ራሱ መናገር ይችላል።” ወላጆቹ ይህን ያሉት ኢየሱስን “መሲሕ ነው” የሚል ሰው ቢኖር የአይሁድ ባለሥልጣኖች ከምኲራብ ሊያስወጡት ተስማምተው ስለ ነበረ እነርሱን በመፍራት ነበር። ስለዚህ ወላጆቹ፥ “እርሱ በዕድሜው ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱን ጠይቁት” አሉ። በዚህ ምክንያት ዕውር የነበረውን ሰው እንደገና ጠርተው “አንተ እውነቱን በመናገር እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን” አሉት። ዕውር የነበረውም ሰው፥ “እርሱ ኃጢአተኛ መሆኑን እኔ አላውቅም፤ አንድ ነገር ዐውቃለሁ፤ ይኸውም እኔ ዕውር እንደ ነበርኩና አሁን ማየት እንደ ቻልኩ ብቻ ነው” ሲል መለሰ። እነርሱም “ምን አደረገልህ? ዐይኖችህንስ ያዳነው እንዴት ነው?” አሉት። እርሱም “አስቀድሜ ነገርኳችሁ፤ እናንተ ግን መስማት አልፈለጋችሁም፤ ታዲያ፥ ስለምን እንደገና መስማት ትፈልጋላችሁ? እናንተም የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆን ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። እነርሱም እንዲህ እያሉ ሰደቡት፦ “የእርሱስ ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳነጋገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደ ሆነ አናውቅም።” ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ይህ ሰው ከየት እንደ ሆነ አለማወቃችሁ ያስደንቃል! ነገር ግን ዐይኖቼን የአበራ እርሱ ነው። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን እንደማይሰማ የታወቀ ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚያመልክና ፈቃዱንም የሚፈጽም ሰው ሲኖር እርሱን እግዚአብሔር ይሰማዋል። ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዐይኖች ያበራ አለ ሲባል ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም። ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ለማድረግ ባልቻለም ነበር።” እነርሱም “ሁለንተናህ በኃጢአት ተወርሶ የተወለድክ! አንተ እኛን ልታስተምር ነውን?” አሉና ከምኲራብ አስወጡት። ሰውየውን ከምኲራብ እንዳስወጡት ኢየሱስ ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ “በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! በእርሱ እንዳምን እርሱ ማን ነው?” አለ። ኢየሱስ “ከዚህ በፊት አይተኸዋል፤ አሁንም የሚያነጋግርህ እርሱ ነው” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! አምናለሁ” ብሎ ሰገደለት። ኢየሱስም “የማያዩ እንዲያዩ፥ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጥቼአለሁ” አለ። በዚያን ጊዜ በኢየሱስ አጠገብ የነበሩ ፈሪሳውያን ይህን ሰምተው “ታዲያ፥ እኛም ዕውሮች መሆናችን ነውን?” አሉት። ኢየሱስም “ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁም ነበር፤ አሁን ግን እናያለን ስለምትሉ፥ ኃጢአተኞች ሆናችሁ ትቀራላችሁ” አላቸው።
ዮሐንስ 9:18-41 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አይሁድ የዚያን ማየት የቻለውን ወላጆች እስኪጠሩ ድረስ፥ ዐይን ሥውር እንደ ነበረና ማየትም እንደ ጀመረ አላመኑም፤ እነርሱንም “እናንተ ዐይን ሥውር ሆኖ ተወለደ የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነውን? ታድያ አሁን እንዴት ያያል?” ብለው ጠየቁአቸው። ወላጆቹም መልሰው “ይህ ልጃችን እንደሆነ ዐይነ ስውርም ሆኖ እንደ ተወለደ እናውቃለን፤ ዳሩ ግን አሁን እንዴት ማየት እንደቻለ አናውቅም፤ ወይም ዐይኖቹን ማን እንደ ከፈተለት እኛ አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፤ እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱ ስለ እራሱ መናገር ይችላል፤” አሉ። ወላጆቹ አይሁድን ስለ ፈሩ ይህንን አሉ፤ “እርሱ ክርስቶስ ነው፤” ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት አይሁድ ከዚህ በፊት ተስማምተው ነበርና። ስለዚህ ወላጆቹ “ሙሉ ሰው ነው፤ እርሱን ጠይቁት፤” አሉ። ስለዚህ ዐይን ሥውር የነበረውን ሰው ለሁለተኛ ጊዜ ጠርተው “እግዚአብሔርን አክብር፤ ይህ ሰው ኀጢአተኛ መሆኑን እኛ እናውቃለን፤” አሉት። እርሱም መልሶ “ኀጢአተኛ መሆኑን አላውቅም፤ ዐይን ሥውር እንደ ነበርሁ፥ አሁንም እንደማይ፥ ይህንን አንድ ነገር አውቃለሁ፤” አለ። ደግመውም “ምን አደረገልህ? እንዴትስ ዐይኖችህን ከፈተ?” አሉት። እርሱም መልሶ “አስቀድሜ ነገርኋችሁ፤ አልሰማችሁምም፤ ስለምን ዳግመኛ ልትሰሙ ትፈልጋላችሁ? እናንተ ደግሞ ደቀመዛሙርቱ ልትሆኑ ትፈልጋላችሁን?” አላቸው። ተሳድበውም “አንተ የእርሱ ደቀመዝሙር ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደ ተናገረው እኛ እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከወዴት እንደሆነ አናውቅም፤” አሉት። ሰውዬው መለሰ፤ እንዲህም አላቸው “ከወዴት እንደሆነ እናንተ አለማወቃችሁ ይህ ድንቅ ነገር ነው፤ ዳሩ ግን ዐይኖቼን ከፈተ። እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር፥ ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኀጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን። ዐይን ሥውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዐይኖች ማንም እንደ ከፈተ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም፤ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ምንም ሊያደርግ ባልቻለ ነበር።” መልሰው “አንተ ሙሉ በሙሉ በኃጢአት ተወልድህ፤ እኛን ታስተምረናለህን?” አሉት። ወደ ውጭም አወጡት። ኢየሱስም ወደ ውጭ እንዳወጡት ሰማ፤ ሲያገኘውም “አንተ በሰው ልጅ ታምናለህን?” አለው። እርሱም መልሶ “ጌታ ሆይ! በእርሱ አምን ዘንድ ማን ነው?” አለ። ኢየሱስም “አይተኸዋል፤ ከአንተ ጋርም የሚናገረው እርሱ ነው፤” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! አምናለሁ፤” አለ፤ ሰገደለትም። ኢየሱስም “የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዲታወሩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ፤” አለ። ከእርሱ ጋር ከነበሩት ፈሪሳውያንም መሀል ይህንን ሰምተው “እኛ ደግሞ ዕውሮች ነንን?” አሉት። ኢየሱስም አላቸው “ዕውሮችስ ብትሆኑ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር፤ አሁን ግን ‘እናያለን’ ትላላችሁ፤ ኀጢአታችሁም በዚያው ይኖራል።