መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 14
14
በዮርዳኖስ ማዶ ያለው ርስት አከፋፈል
1የእስራኤልም ልጆች በከነዓን ምድር የወረሱት ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ የእስራኤልም ልጆች ነገድ የአባቶቻቸው አለቆች ያወረሱአቸው ርስት ይህ ነው። 2እግዚአብሔር በሙሴ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኢያሱ” ይላል። እጅ እንዳዘዘ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው በየርስታቸው በዕጣ አከፋፈሉአቸው። 3ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ ርስት ሰጥቶ ነበር፤ ነገር ግን በመካከላቸው ለሌዋውያን ርስት አልሰጣቸውም። 4የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ነበሩ፤ ለሌዋውያንም ከሚቀመጡባቸው ከተሞች ለእንስሶቻቸው ከሚሆን ማሰማሪያቸውና ከእንስሶቻቸውም በቀር በምድሩ ውስጥ ድርሻ አልሰጡአቸውም። 5እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፤ ምድሪቱንም ተካፈሉ።
ኬብሮን ለካሌብ እንደ ተሰጠች
6የይሁዳም ልጆች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ቄኔዛዊውም የዮፎኒ ልጅ ካሌብ አለው፥ “ለአምላክ ሰው ለሙሴ ስለ እኔና ስለ አንተ እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ የተናገረውን ቃል ታውቃለህ። 7የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ምድርን እሰልል ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ እኔ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ፤ እኔም በልቡ የነበረውን ቃል መለስሁለት። 8ከእኔ ጋር የወጡ ወንድሞች ግን የሕዝቡን ልብ አስካዱ፤ እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽሜ እከተለው ዘንድ ተመለስሁ። 9ሙሴም በዚያ ቀን፦ ‘አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽመህ ተከትለሃልና እግርህ የረገጠው ምድር ለአንተና ለልጆችህ ለዘለዓለም በርግጥ ርስት ይሆናል’ ብሎ ማለ። 10አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለሙሴ ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ፥ እስራኤል በምድረ በዳ ሲዞሩ፥ እርሱ እንደ ተናገረኝ እግዚአብሔር እነዚህን አርባ አምስት ዓመታት በሕይወት አኖረኝ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ለእኔ ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ። 11ሙሴም በላከኝ ጊዜ ጽኑዕ እንደ ነበርሁ፥ ዛሬም ገና እንዲሁ ለመዋጋት ለመውጣትም ለመግባትም ጽኑዕ ነኝ። 12አሁን እንግዲህ በዚያ ቀን እግዚአብሔር የተናገረውን ይህን ተራራማ ሀገር ስጠኝ፤ አንተ በዚያ ቀን ዔናቃውያን፥ ታላላቆችና የተመሸጉ ከተሞችም በዚያ እንዳሉ ሰምተህ ነበር፤ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን እግዚአብሔር እንደ ተናገረኝ አጠፋቸዋለሁ።”
13ኢያሱም የቄኔዝ ልጅ፥ የዮፎኒ ልጅ ካሌብን ባረከው፤ ኬብሮንንም ርስት አድርጎ ሰጠው። 14ስለዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ስለ ተከተለ ኬብሮን እስከ ዛሬ ለቄኔዛዊው ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት ሆነች። 15የኬብሮንም ስም አስቀድሞ የአርቦቅ ከተማ ትባል ነበር፤ እርስዋም የዔናቃውያን ዋና ከተማ ነበረች። ምድሪቱም ከውጊያ ዐረፈች።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 14: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ