መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 17
17
የምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት
1የምናሴ ልጆች ነገድ ድንበር ይህ ነው፤ የዮሴፍ በኵር እርሱ ነውና። የምናሴም በኵር የገለዓድ አባት ማኪር ብርቱ ተዋጊ ስለ ነበረ ገለዓድንና ባሳንን ወረሰ። 2ዕጣውም ለቀሩት ለምናሴ ልጆች በየወገኖቻቸው፥ ለኢያዜር ልጆች፥ ለቄሌዝ ልጆች፥ ለኢየዚኤል ልጆች፥ ለሴኬም ልጆች፥ ለሱማሪም ልጆች፥ ለኦፌር ልጆች ሆነ፤ ወንዶቹ በየወገኖቻቸው እነዚህ ናቸው። 3ለኦፌር ልጅ፥ ለሰለጰዓድ ግን ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ የሰለጰዐድም የሴቶች ልጆቹ ስሞች፦ መሐላ፥ ኑዓ፥ ሔግላ፥ ሚልካ፥ ቴርሳ ነበሩ። 4እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ ወደ አለቆችም ቀርበው፥ “እግዚአብሔር በወንድሞቻችን መካከል ርስት እንዲሰጠን በሙሴ እጅ አዘዘ” አሉ፤ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ከአባታቸው ወንድሞች ጋር ርስት ሰጣቸው። 5ዕጣቸውም በዮርዳኖስ ማዶ ከአለው ከገለዓድና ከባሳን ሀገር በቀር ለምናሴ ዐሥር ዕጣ ሆነ፤ 6የምናሴ ሴቶች ልጆች በወንድሞቻቸው መካከል ርስት ተቀብለዋልና፤ የገለዓድም ምድር ለቀሩት ለምናሴ ልጆች ሆኖአልና።
7የምናሴም ልጆች ድንበር በሐነት ልጆች ፊት ያለው ዴላናታ ነው። በኢያሚንና በኢያሲብ ድንበር በተፍቶት ምንጭ ላይ ያልፋል። 8የጣፌት ምድር ለምናሴ ነበረ፤ ጣፌት ግን በኤፍሬም ልጆችና በምናሴ ልጆች አውራጃ ያለ ነው። 9ድንበራቸውም በደቡብ በኩል ወዳለው ወደ ቃራና ሸለቆና ወደ ኢያሪያል ሸለቆ ይወርዳል፤ የኤፍሬም ዕጣ የሆነው ጤሬሜንቶስ የሚባለው ዛፍም በምናሴ ከተሞች መካከል አለ፤ የምናሴም ድንበር በሰሜን በኩል ወደ ወንዙ ይወርዳል፤ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። 10በደቡብ በኩል ያለው ለኤፍሬም ነበረ፤ በሰሜን በኩል ያለውም ለምናሴ ነበረ፤ ድንበሩም ባሕር ነበረ፤ በሰሜን በኩል ወደ አሴር፥ በምሥራቅም በኩል ወደ ይሳኮር ይደርሳል። 11በይሳኮርና በአሴር መካከል ቤትሳንና መንደሮችዋ፥ ዶርና መንደሮችዋ፥ መጌዶና መንደሮችዋ፥ የመፌታ ሦስተኛ እጅና መንደሮችዋ ለምናሴ ነበሩ። 12የምናሴ ልጆችም የእነዚህን ከተሞች ሰዎች ማጥፋት ተሳናቸው፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያች ሀገር ለመቀመጥ መጡ። 13የእስራኤልም ልጆች በረቱባቸው፤ ከነዓናውያንንም ገዙአቸው፤ ነገር ግን ፈጽመው አላጠፉአቸውም።
የኤፍሬምና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ተጨማሪ ርስት መጠየቃቸው
14የዮሴፍም ልጆች ኢያሱን፥ “እኛ ብዙ ሕዝብ ስንሆን እስከ አሁንም እግዚአብሔር ስለ ባረከን ለምን አንድ ክፍል፥ አንድም ዕጣ ብቻ ርስት አድርገህ ሰጠኸን?” ብለው ወቀሱት። 15ኢያሱም፥ “ብዙ ሕዝብ ከሆናችሁ፥ ተራራማው የኤፍሬም ሀገርም ከጠበባችሁ ወደ ዱር ወጥታችሁ መንጥራችሁ አቅኑአት” አላቸው። 16እነርሱም፥ “ተራራማው የኤፍሬም ሀገር አይበቃንም፤ በሸለቆው ውስጥ ለሚኖሩት፥ በቤትሳንና በመንደሮችዋ፥ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ለሚኖሩት ከነዓናውያን የተመረጡ ፈረሶችና ሰይፍ አሏቸው” አሉት። 17ኢያሱም ለዮሴፍ ልጆች፥ “እናንተ ብዙ ሕዝብ ከሆናችሁ፥ ጽኑ ኀይልም ከአላችሁ አንድ ዕጣ ብቻ አይሆንላችሁም፤ 18ነገር ግን ተራራማው ሀገር ለእናንተ ይሆናል፤ ዱር እንኳ ቢሆንም ትመነጥሩታላችሁ፤ ለእናንተም ይሆናል፤ ለከነዓናውያንም የተመረጡ ፈረሶችና የብረት ሰረገሎች ቢሆኑላቸው፥ የበረቱ ቢሆኑም እናንተ እስክታጠፉአቸው ድረስ ትበረቱባቸዋላችሁ” አላቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 17: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ