መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 18
18
የቀሪው ርስት አከፋፈል
1የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ፤ በዚያም የምስክሩን ድንኳን ተከሉ፤ ምድሩም ጸጥ ብሎ ተገዛላቸው። 2ከእስራኤልም ልጆች ርስት ያልተካፈሉ ሰባት ነገድ ቀርተው ነበር። 3ኢያሱም የእስራኤልን ልጆች አላቸው፥ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር እንዳትወርሱአት እስከ መቼ ድረስ ታቈዩአታላችሁ? 4ከየነገዳችሁ ሁሉ ሦስት ሦስት ሰዎችን አምጡ፥#ዕብ. “እኔም እልካቸዋለሁ” ብሎ ይጨምራል። ተነሥተውም ሀገሪቱን ይዙሩአት፤ ለመክፈልም እንዲያመች ገልጠው ይጻፉአት፤ ወደ እኔም ይመለሳሉ። 5በሰባትም ክፍል ይከፍሉታል፤ ይሁዳ በደቡብ በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣል፤ የዮሴፍም ልጆች በሰሜን በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣሉ። 6እናንተም ምድሪቱን በሰባት ክፍል ክፈሏት፤#ዕብ. “ ጻፉት የጻፋችሁትንም ...” ይላል። ወደ እኔም ወዲህ አምጡልኝ፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት በዚህ ዕጣ አጣጥላችኋለሁ። 7ነገር ግን የእግዚአብሔር ክህነት ርስታቸው ነውና ለሌዊ ልጆች በመካከላችሁ እድል ፋንታ የላቸውም፤ ጋድም፥ ሮቤልም፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀብለዋል።”
8ሰዎችም ተነሥተው ሄዱ፤ ኢያሱም ምድሩን ሊጽፉ የሄዱትን፥ “ሂዱ፤ ምድሩንም ዞራችሁ ጻፉት፤ ወደ እኔም ተመለሱ፤ በዚህም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ አጣጥላችኋለሁ” ብሎ አዘዛቸው። 9ሰዎቹም ሄደው ምድሩን ዞሩ፥ አዩትም፤ እንደ ከተሞችም በሰባት ክፍል ከፈሉት፤ በመጽሐፍም ጻፉት፤ ወደ ኢያሱም አመጡ።#ዕብ. “ ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ሴሎ ተመለሱ” ይላል። 10ኢያሱም በእግዚአብሔር ፊት በሴሎ ዕጣ አጣጣላቸው።#ዕብ. “በዚያም ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች እንደ ክፍሎቻቸው ምድሩን ከፈለ” የሚል ይጨምራል።
ለብንያም ነገድ የተሰጠ ርስት
11የብንያምም ነገድ ዕጣ በየወገኖቻቸው በቅድሚያ ወጣ፤ የዕጣቸውም ዳርቻ በይሁዳ ልጆችና በዮሴፍ ልጆች መካከል ወጣ። 12በሰሜን በኩል ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ጀመረ፤ ድንበሩም ከኢያሪኮ አዜብ ወደ ሰሜን ወገን ወጣ፥ ከዚያም በተራራማው ሀገር ወደ ባሕር ወጣ፤ መውጫውም የቤቶን ምድብራይጣስ ነበረ። 13ድንበሩም ከዚያ በደቡብ በኩል ቤቴል ወደምትባል ወደ ሎዛ ዐለፈ፤ ድንበሩም በታችኛው ቤቶሮን ደቡብ በኩል ባለው ተራራ ወደ ማአጣሮቶሬክ ወረደ። 14ድንበሩም ወደ ባሕር ሄደ፤ በቤቶሮንም ፊት ለፊት ካለው ተራራ ወደ አዜብ ዞረ፤ መውጫውም ቂርያታርም በምትባል በይሁዳ ልጆች ከተማ በቂርያትበኣል ነበረ፤ ይህ በባሕር በኩል ነበረ። 15የደቡብም ዳርቻ ከቅርያታርም መጨረሻ ነበረ፤ ድንበሩም በጋሲን ላይ ወደ ነፍቶ ውኃ ምንጭ ወጣ። 16ድንበሩም በሄኖም ሸለቆ ፊት ለፊት ወዳለው ተራራ መጨረሻ ወረደ፤ እርሱም በራፋይም ሸለቆ በሰሜን በኩል ነው፤ ወደ ሄኖም ሸለቆ ወደ ኢያቡስ ዳር በደቡብ በኩል ወረደ፥ ወደ ሮጌል ምንጭም ወረደ። 17ወደ ቤተሳሚስም ምንጭ ያልፋል፤ በኢታሚም አቀበት ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ኬልዩት ይገባል፤ ወደ ሮቤልም ልጅ ወደ ቤዎን ድንጋይ ይወርዳል፤ 18በሰሜንም በኩል ወደ ቤተ ራባ ጀርባ ያልፋል። በመስዕም ወደ ባሕር መንገድ ይወርዳል፤ 19የድንበራቸውም ፍጻሜ በሰሜን በኩል ወደ ጨው ባሕር ልሳን ይደርሳል፤ በደቡብም በኩል ድንበራቸው ዮርዳኖስ ነው። ይህም በደቡብ በኩል ያለው ድንበር ነው። 20በምሥራቅም በኩል ድንበሩ ዮርዳኖስ ነበረ። ይህ በዙሪያቸው ዳርቻ በየወገኖቻቸው የብንያም ልጆች ርስት ነበረ።
21የብንያምም ልጆች ነገድ ከተሞች በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ኢያሪኮ፥ ቤትሖግሊ፥ ዐመቀስስ፤ 22ቤተ ባራ፥ ሰራ፥ ቤስና፤ 23አኢን፥ ፋራ፥ ኤፍራታም፥ 24ቃራፋ፥ ቄፍራ፥ ሞኒ፥ ጋባህ፤ ዐሥራ ሁለቱ ከተሞችና መንደሮቻቸው። 25ገባዖን፥ ራማ፥ ብኤሮት፤ 26ማሴማ፥ ቤሮን፥ አሞቂ፥ 27ቤራ፥ ቃፋን፥ ናቃና፥ ሴሌቃን፥ ታራኤላ፤ 28ኢየሩሳሌም የምትባል የኢያቡሴዎን ከተማና የኢያሪሞን ከተማ ገባዖን፤ ዐሥራ ሦስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። የብንያም ልጆች ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 18: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ