መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 20
20
መማፀኛ ከተሞች
1እግዚአብሔርም ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፦ በሙሴ ቃል የነገርኋችሁን የመማፀኛ ከተሞችን ስጡ። 3ባለማወቅ ሳይወድድ ሰውን የገደለ በዚያ ይማፀን ዘንድ፥ ለእናንተ የመማፀኛ ከተሞችን ሥሩ፤ ነፍስ የገደለ ሰውም በአደባባይ ለፍርድ እስኪቀርብ ድረስ በደም ተበቃዩ አይገደል። 4ከእነዚህም ከተሞች በአንዲቱ ይማፀናል፤ በከተማዪቱም በር አደባባይ ቆሞ ለከተማዪቱ ሽማግሌዎች ነገሩን ይናገራል፤ እነርሱም ወደ ከተማዪቱ ያገቡታል። የሚቀመጥበትም ስፍራ ይሰጡታል። 5ባለ ደሙ ቢያሳድደው፥ አስቀድሞ ሳይጠላው ባልንጀራውን በስሕተት ስለ ገደለው ነፍሰ ገዳዩን በእጁ አሳልፈው አይስጡት። 6በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ ፥ በዚያም ወራት ያለው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያች ከተማ ይቀመጥ፤ ከዚያም ወዲያ ነፍሰ ገዳዩ ይመለሳል፤ ወደ ከተማውም፥ ወደ ቤቱም ሸሽቶ ወደ ወጣበትም ከተማ ይገባል።”
7በንፍታሌም ባለው በተራራማው ሀገር በገሊላ ቃዴስን፥ በኤፍሬምም ባለው በተራራማው ሀገር ሴኬምን፥ በይሁዳም ባለው በተራራማው ሀገር ኬብሮን የምትባለውን የአርቦቅን ከተማ ለዩ። 8በዮርዳኖስም ማዶ ከኢያሪኮ ወደ ምሥራቅ ከሮቤል ነገድ በምድረ በዳው በደልዳላው ስፍራ ቦሶርን፥ ከጋድም ነገድ በገለዓድ ኤርሞትን፥ ከምናሴም ነገድ በባሳን ጎላንን ለዩ። 9በማኅበሩ ፊት እስኪቆምና እስኪመረመር ድረስ ባለደሙ እንዳይገድለው ሳያውቅ ሰውን የገደለ ወደዚያ እንዲማፀን፥ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ፥ በመካካላቸውም ለሚቀመጥ መጻተኛ የተመረጡ ከተሞች እነዚህ ናቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 20: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ