ኦሪት ዘሌዋውያን 10
10
ስለ ናዳብና አብዩድ በደል
1የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ#ዕብ. “አቢሁ” ይላል። በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፤ በላዩም ዕጣን ጨመሩበት፤ በእግዚአብሔርም ፊት እግዚአብሔር ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ። 2እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ። 3ሙሴም አሮንን፥ “እግዚአብሔር፦ ወደ እኔ በሚቀርቡ እመሰገናለሁ፤ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ ብሎ የተናገረው ይህ ነው” አለው፤ አሮንም ደነገጠ። 4ሙሴም የአሮንን አጎት የአዚሔልን ልጆች ሚሳዴንና ኤልሳፍንን ጠርቶ፥ “ሂዱ፤ ወንድሞቻቸሁን ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዱአቸው” አላቸው። 5እነርሱም ገብተው አነሡአቸው፤ ሙሴም እንዳለ በልብሳቸው ከሰፈር ወደ ውጭ ወሰዱአቸው። 6ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን፥ “እንዳትሞቱ፥ በማኅበሩም ላይ ሁሉ ቍጣ እንዳይወርድ ራሳችሁን አትንጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ እግዚአብሔር ስላቃጠላቸው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ። 7የእግዚአብሔር የቅብዐት ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከምስክሩ ድንኳን ደጃፍ አትውጡ” አላቸው። ሙሴም እንዳዘዛቸው አደረጉ።
ለአሮንና ለልጆቹ የተሠሩ ሕጎች
8እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 9“እንዳትሞቱ ወደ ምስክሩ ድንኳን ስትገቡ ወይም ወደ መሠዊያው ስትቀርቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘለዓለም ሥርዐት ይሆናል፤ 10በተቀደሰውና በአልተቀደሰው፥ በርኩሱና በንጹሑም መካከል ትለያላችሁ፤ 11እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ የነገራቸውን ሥርዐት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ታስተምራቸዋለህ።”
12ሙሴም አሮንን፥ የተረፉለትን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን አላቸው፥ “ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቍርባን የቀረውን የስንዴውን ቍርባን ውሰዱ፤ ቂጣም አድርጋችሁ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት፤ 13እግዚአብሔርም እንዲህ አዝዞኛልና፥ ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቍርባን ለአንተም፥ ለልጆችህም የተሰጠ ሥርዐት ነውና በቅዱስ ስፍራ ትበሉታላችሁ። 14እነዚህም ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕቶች ለአንተና ለልጆችህ ሥርዐት እንዲሆኑ ስለ ተሰጡ፥ የመሥዋዕቱን ፍርምባና ወርች አንተ፥ ከአንተ ጋርም ልጆችህ፥ ቤተሰብህም ተለይቶ በንጹሕ ስፍራ ትበላላችሁ። 15የመሥዋዕቱን ወርችና ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት ከሚቀርበው መሥዋዕት የእሳት ቍርባን ከሆነው ስብ ጋር ያመጣሉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለአንተ፥ ከአንተ ጋርም ለወንዶችና ሴቶች ልጆችህ የዘለዓለም ሥርዐት ይሆናል።”
16ሙሴም የኀጢአቱን መሥዋዕት ፍየል እጅግ ፈለገው፤ በፈለገውም ጊዜ እነሆ ተቃጥሎ ነበር፤ ሙሴም የቀሩትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቈጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ 17“ቅዱሰ ቅዱሳን ነውና፥ የሕዝቡንም ኀጢአት እንድትሸከሙ፥ በእግዚአብሔርም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ይህን ትበሉ ዘንድ ለእናንተ ሰጥቶታልና ስለ ምን የኀጢአትን መሥዋዕት በቅዱሱ ስፍራ አልበላችሁም? 18እነሆ፥ ደሙን ወደ መቅደስ ውስጥ አላገባችሁትም፤ እኔ እንደታዘዝሁ በቅዱስ ስፍራ ውስጥ ትበሉት ዘንድ ይገባችሁ ነበር።” 19አሮንም ሙሴን ተናገረው እንዲህም አለው፥ “እነሆ፥ ዛሬ የኀጢአታቸውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት በለዩ ጊዜ፥ ይህች አገኘችኝ፤ ዛሬም የኀጢአቱን መሥዋዕት እበላ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት መልካም አይደለም።” 20ሙሴም ሰማ፤ ደስም አለው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘሌዋውያን 10: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ