የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሉ​ቃስ ወን​ጌል 10:25-37

የሉ​ቃስ ወን​ጌል 10:25-37 አማ2000

ከዚህ በኋላ አንድ ሕግ ዐዋቂ ሊፈ​ት​ነው ተነ​ሣና፥ “መም​ህር ሆይ፥ የዘ​ለ​ዓ​ለም ሕይ​ወ​ትን እወ​ርስ ዘንድ ምን ላድ​ርግ?” አለው። እር​ሱም፥ “በኦ​ሪት ምን ተጽ​ፎ​አል? እን​ዴ​ትስ ታነ​ብ​ባ​ለህ?” አለው። እር​ሱም መልሶ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አም​ላ​ክ​ህን በፍ​ጹም ልብህ፥ በፍ​ጹም ሰው​ነ​ትህ፥ በፍ​ጹም ኀይ​ልህ፥ በፍ​ጹም ዐሳ​ብህ ውደ​ደው፤ ባል​ን​ጀ​ራ​ህ​ንም እንደ ራስህ ውደድ ይላል” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “መል​ካም መል​ሰ​ሃል፤ እን​ዲሁ አድ​ርግ፤ ትድ​ና​ለ​ህም” አለው። ራሱን ሊያ​ከ​ብር ባል​ን​ጀ​ራ​ው​ንም ሊንቅ ወድዶ፥ “ባል​ን​ጀ​ራዬ ማነው?” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ እን​ዲህ አለው፥ “አንድ ሰው ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ወደ ኢያ​ሪኮ ይወ​ርድ ነበር፤ ሽፍ​ቶ​ችም አገ​ኙት፤ ደበ​ደ​ቡት፥ አቈ​ሰ​ሉት፥ ልብ​ሱ​ንም ገፍ​ፈው፤ በሕ​ይ​ወ​ትና በሞት መካ​ከል ጥለ​ውት ሄዱ። አንድ ካህ​ንም በዚ​ያች መን​ገድ ሲወ​ርድ ድን​ገት አገ​ኘው፤ አይ​ቶም አል​ፎት ሄደ። እን​ዲ​ሁም አንድ ሌዋዊ በዚያ ቦታ አገ​ኘ​ውና፥ አይቶ እንደ ፊተ​ኛው አል​ፎት ሄደ። አንድ ሳም​ራዊ ግን በዚ​ያች መን​ገድ ሲሄድ አገ​ኘው፤ አይ​ቶም አዘ​ነ​ለት። ወደ እር​ሱም ቀረበ፤ ቍስ​ሉ​ንም አጋ​ጥሞ አሰ​ረ​ለት፤ በቍ​ስሉ ላይም ወይ​ንና ዘይት ጨመ​ረ​ለት፤ በአ​ህ​ያ​ውም ላይ አስ​ቀ​ምጦ እን​ዲ​ፈ​ው​ሰው የእ​ን​ግ​ዶ​ችን ቤት ወደ​ሚ​ጠ​ብ​ቀው ወሰ​ደው፤ የሚ​ድ​ን​በ​ት​ንም ዐሰበ። በማ​ግ​ሥ​ቱም ሁለት ዲናር አው​ጥቶ ለእ​ን​ግዳ ቤት ጠባ​ቂው ሰጠ​ውና፦ ‘በዚህ አስ​ታ​ም​ልኝ፤ ከዚህ የሚ​በ​ልጥ ለእ​ርሱ የም​ታ​ወ​ጣው ቢኖር እኔ በተ​መ​ለ​ስሁ ጊዜ እከ​ፍ​ል​ሃ​ለሁ’ አለው። እን​ግ​ዲህ ሽፍ​ቶች ለደ​በ​ደ​ቡት ሰው ከእ​ነ​ዚህ ከሦ​ስቱ ባል​ን​ጀራ የሚ​ሆ​ነው ማን​ኛው ይመ​ስ​ል​ሃል?” እር​ሱም“ምሕ​ረት ያደ​ረ​ገ​ለት ነዋ” አለው፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እን​ኪ​ያስ አን​ተም ሂድና እን​ዲሁ አድ​ርግ” አለው።