የሉቃስ ወንጌል 7
7
የመስፍኑ ሎሌ እንደ ዳነ
1ለሕዝቡም ቃሉን ነግሮ ከፈጸመ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። 2አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ አገልጋዩም ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር፤ እርሱም በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነበር። 3የጌታችን የኢየሱስንም ነገር በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ አገልጋዩን እንዲያድንለት ይማልዱት ዘንድ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከ። 4ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስም መጥተው ማለዱት፤ እንዲህም አሉት፥ “ፈጥነህ ውረድ፤#“ፈጥነህ ውረድ” የሚለው በግሪኩ የለም። ይህን ልታደርግለት ይገባዋልና። 5እርሱ ወገናችንን ይወዳልና፤ ምኵራባችንንም ሠርቶልናልና።” 6ጌታችን ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ፥ የመቶ አለቃዉ ወዳጆቹን እንዲህ ብሎ ላከ፥ “አቤቱ፥ አትድከም፤ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና። 7እኔም ወደ አንተ ልመጣ አይገባኝም፤ ነገር ግን በቃልህ እዘዝ፤ ብላቴናዬም ይድናል። 8እኔም እኮ ገዢ ሰው ነኝ፤ ወታደሮችም አሉኝ፤ አንዱን ሂድ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ና ብለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም እንዲህ አድርግ ብለው ያደርጋል።” 9ጌታችን ኢየሱስም ይህን ከእርሱ በሰማ ጊዜ አደነቀው፤ ዘወር ብሎም ይከተሉት ለነበሩት ሕዝብ፥ “እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው ሰው አላገኘሁም” አላቸው። 10የተላኩትም በተመለሱ ጊዜ ብላቴናውን ድኖ አገኙት።
ስለ መበለቲቱ ልጅ መዳን
11በማግሥቱም ናይን ወደምትባል ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ሕዝብም አብረውት ሄዱ። 12ወደ ከተማው በር በደረሰ ጊዜም እነሆ፥ ያንዲት መበለት ሴት ልጅ ሙቶ ሬሳውን ተሸክመው ሲሄዱ አገኘ፤ ይኸውም ለእናቱ አንድ ነበረ፤ ብዙዎችም የከተማ ሰዎች አብረዋት ነበሩ። 13ጌታችንም በአያት ጊዜ አዘነላትና፥ “አታልቅሺ” አላት። 14ቀርቦም ቃሬዛውን ያዘ፤ የተሸከሙትም ቆሙ፤ እርሱም፥ “አንተ ጐበዝ ተነሥ እልሃለሁ” አለው። 15የሞተውም ተነሥቶ ተቀመጠ፤ መናገርም ጀመረ፤ ለእናቱም ሰጣት። 16ሁሉም ፈሩ፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ እንዲህም አሉ፥ “ታላቅ ነቢይ ተነሣልን፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐብኝቶአልና።” 17ይህም የእርሱ ዜና በይሁዳ ሀገሮች ሁሉና በአውራጃዋ ሁሉ ተሰማ።
ከዮሐንስ ስለ ተላኩት መልእክተኞች
18ይህንም ሁሉ ደቀ መዝሙርቱ ለዮሐንስ ነገሩት። 19ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ፥ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ?” ብሎ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ላካቸው። 20መልእክተኞችም ወደ እርሱ ደርሰው፥ “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ? ብሎ መጥምቁ ዮሐንስ ወደ አንተ ልኮናል” አሉት። 21ያንጊዜም ብዙዎችን ከደዌአቸውና ከሕመማቸው ከክፉዎች አጋንንትም ፈወሳቸው፤ ለብዙዎች ዕውራንም እንዲያዩ ብርሃንን ሰጣቸው። 22#ኢሳ. 35፥5-6፤ 61፥1። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶችም ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል። 23በእኔም የማይሰናከል ብፁዕ ነው።”
ጌታ መጥምቁ ዮሐንስን ስለ ማመስገኑ
24የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ከሄዱ በኋላ ለሕዝቡ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እንዲህ ይላቸው ጀመር፥ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ከነፋስ የተነሣ የሚወዛወዝ ሸንበቆን ነውን? 25ወይስ ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ቀጭን ልብስ የለበሰውን ሰው ነውን? እነሆ፥ በክብር ልብስ ያጌጡስ በነገሥታት ቤት አሉ። 26ወይስ ምን ልታዩ ወጥታችኋል? ነቢይን ነውን? አዎን፥ እላችኋለሁ፤ ከነቢይም ይበልጣል። 27#ሚል. 3፥1። እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፥ ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈለት ይህ ነው። 28እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም አልተነሣም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን የሚያንሰው ይበልጠዋል።” 29#ማቴ. 21፥32፤ ሉቃ. 3፥12። ሕዝቡም ሁሉ ቀራጮችም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን ጻድቅ ነው አሉት፤ የዮሐንስን ጥምቀት ተጠምቀው ነበርና። 30ፈሪሳውያንና የሕግ ጻፎች ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ#በግሪኩ “ምክር” ይላል። ተቃወሙ፤ በእርሱ አልተጠመቁምና።
31“እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን እመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? 32በገበያ ተቀምጠው ባልንጀሮቻቸውን ጠርተው፥ “አቀነቀንላችሁ፥#በግሪኩ “እምቢልታ ነፋንላችሁ” ይላል። አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾም አወጣንላችሁ፥ አላለቀሳችሁምም የሚሉአቸው ልጆችን ይመስላሉ። 33መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይበላ ወይንም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና ጋኔን አለበት አላችሁት። 34የሰው ልጅም እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እናንተ ግን እነሆ፥ በላተኛና ወይን ጠጪ ሰው፥ የኃጥኣንና የቀራጮች ወዳጅ አላችሁት። 35ጥበብም ከልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች።”
ስለ ፈሪሳዊውና ስለ ኀጢአተኛዪቱ ሴት
36ከፈሪሳውያንም አንዱ በእርሱ ዘንድ ምሳ እንዲበላ ለመነው፤ ወደ ፈሪሳዊውም ቤት ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። 37እነሆ፥ ከዚያች ከተማ ሰዎችም አንዲት ኀጢአተኛ ሴት በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ ዐውቃ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ገዝታ መጣች። 38#ማቴ. 26፥7፤ ማር. 14፥3፤ ዮሐ. 12፥3። በስተኋላውም በእግሮቹ አጠገብ ቆማ አለቀሰች፤ እግሮቹንም በእንባዋ ታርስ ነበር፥ በራስ ጠጕርዋም እግሮቹን ታብሰውና ትስመው፥ ሽቱም ትቀባው ነበር። 39የጠራው ፈሪሳዊም ባየ ጊዜ በልቡ ዐሰበ፤ እንዲህም አለ፥ “ይህስ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህቺ የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች፥ እንዴትስ እንደ ነበረች ባላወቀም ነበርን? ኀጢአተኛ ናትና።” 40ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው፤ እርሱም፥ “መምህር ሆይ፥ ተናገር” አለው። 41እርሱም እንዲህ አለው፥ “ለአንድ አበዳሪ ሁለት ባለ ዕዳዎች ነበሩት፤ በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት፤ በሁለተኛውም አምሳ። 42የሚከፍሉትም ባጡ ጊዜ ለሁለቱም ተወላቸው፤ እንግዲህ ከሁለቱ አብልጦ ሊወደው የሚገባው ማንኛው ነው?” 43ስምዖንም መልሶ፥ “ብዙውን የተወለት ነው እላለሁ” አለው፤ እርሱም፥ “መልካም ፈረድህ” አለው። 44ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፥ “ይህቺን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ለእግሮች ውኃ ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ እርስዋ ግን አልቅሳ በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጕርዋም አበሰች። 45አንተስ ሰላምታ አልሰጠኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምሮ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። 46አንተ ራሴን እንኳ ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባችኝ። 47ስለዚህም እልሃለሁ፤ ብዙ ኀጢኣቷ ተሰርዮላታል፤ በብዙ ወድዳለችና፤ ጥቂት የሚወድድ ጥቂት ይሰረይለታል፤ ብዙ የሚወድድም ብዙ ይሰረይለታል።”#“ብዙ የሚወድድ ብዙ ይሰረይለታል” የሚለው በግሪኩ የለም። 48ሴቲቱንም፥ “ኀጢኣትሽ ተሰረየልሽ” አላት። 49በማዕዱ የተቀመጡትም እርስ በርሳቸው፥ “ኀጢአትን የሚያስተሰርይ ይህ ማነው?” ይሉ ጀመር። 50ሴቲቱንም አላት፥ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ።”
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 7: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ