ከፈሪሳውያንም አንዱ በእርሱ ዘንድ ምሳ እንዲበላ ለመነው፤ ወደ ፈሪሳዊውም ቤት ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። እነሆ፥ ከዚያች ከተማ ሰዎችም አንዲት ኀጢአተኛ ሴት በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ ዐውቃ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ገዝታ መጣች። በስተኋላውም በእግሮቹ አጠገብ ቆማ አለቀሰች፤ እግሮቹንም በእንባዋ ታርስ ነበር፥ በራስ ጠጕርዋም እግሮቹን ታብሰውና ትስመው፥ ሽቱም ትቀባው ነበር። የጠራው ፈሪሳዊም ባየ ጊዜ በልቡ ዐሰበ፤ እንዲህም አለ፥ “ይህስ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህቺ የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች፥ እንዴትስ እንደ ነበረች ባላወቀም ነበርን? ኀጢአተኛ ናትና።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው፤ እርሱም፥ “መምህር ሆይ፥ ተናገር” አለው። እርሱም እንዲህ አለው፥ “ለአንድ አበዳሪ ሁለት ባለ ዕዳዎች ነበሩት፤ በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት፤ በሁለተኛውም አምሳ። የሚከፍሉትም ባጡ ጊዜ ለሁለቱም ተወላቸው፤ እንግዲህ ከሁለቱ አብልጦ ሊወደው የሚገባው ማንኛው ነው?” ስምዖንም መልሶ፥ “ብዙውን የተወለት ነው እላለሁ” አለው፤ እርሱም፥ “መልካም ፈረድህ” አለው። ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፥ “ይህቺን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ለእግሮች ውኃ ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ እርስዋ ግን አልቅሳ በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጕርዋም አበሰች። አንተስ ሰላምታ አልሰጠኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምሮ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን እንኳ ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባችኝ። ስለዚህም እልሃለሁ፤ ብዙ ኀጢኣቷ ተሰርዮላታል፤ በብዙ ወድዳለችና፤ ጥቂት የሚወድድ ጥቂት ይሰረይለታል፤ ብዙ የሚወድድም ብዙ ይሰረይለታል።” ሴቲቱንም፥ “ኀጢኣትሽ ተሰረየልሽ” አላት። በማዕዱ የተቀመጡትም እርስ በርሳቸው፥ “ኀጢአትን የሚያስተሰርይ ይህ ማነው?” ይሉ ጀመር። ሴቲቱንም አላት፥ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ።”
የሉቃስ ወንጌል 7 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 7
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 7:36-50
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos