የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሉቃስ 7:36-50

ሉቃስ 7:36-50 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ ምግብ አብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ጋበዘው፤ እርሱም ወደ ፈሪሳዊው ቤት ሄዶ በማእድ ተቀመጠ። በዚያ ከተማ የምትኖር አንዲት ኀጢአተኛ ሴት፣ ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት በማእድ መቀመጡን በሰማች ጊዜ አንድ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ሽቶ ይዛ መጣች። ከበስተ ኋላው እግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች እግሩን በእንባዋ ታርስ፣ በራሷም ጠጕር ታብሰው ጀመር፤ እግሩንም እየሳመች ሽቱውን ቀባችው። የጋበዘውም ፈሪሳዊ ይህን ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፣ የነካችው ሴት ማን እንደ ሆነች፣ ደግሞም ምን ዐይነት ሰው እንደ ሆነች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና” ብሎ በልቡ ዐሰበ። ኢየሱስም፣ “ስምዖን ሆይ፤ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው። እርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ንገረኝ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንደኛው አምስት መቶ ዲናር፣ ሁለተኛው ደግሞ አምሳ ዲናር ነበረበት። የሚከፍሉትም ቢያጡ ዕዳቸውን ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ አበዳሪውን አብልጦ የሚወድደው የትኛው ነው?” ስምዖንም፣ “ብዙው ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” ሲል መለሰ። ኢየሱስም፣ “ትክክል ፈርደሃል” አለው። ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፤ “ይህችን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ አንተ ለእግሬ ውሃ እንኳ አላቀረብህልኝም፤ እርሷ ግን እግሬን በእንባዋ እያራሰች በጠጕሯ አበሰች። አንተ ከቶ አልሳምኸኝም፤ እርሷ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባህም፤ እርሷ ግን እግሬን ሽቶ ቀባች። ስለዚህ እልሃለሁ፤ እጅግ ወድዳለችና ብዙው ኀጢአቷ ተሰርዮላታል፤ በትንሹ የተሰረየለት ግን የሚወድደው በትንሹ ነው።” ኢየሱስም ሴቲቱን፣ “ኀጢአትሽ ተሰርዮልሻል” አላት። አብረውት በማእድ ተቀምጠው የነበሩ እንግዶችም፣ “ይህ ኀጢአትን እንኳ የሚያስተሰረይ እርሱ ማን ነው?” ብለው በልባቸው አሰቡ። ኢየሱስም ሴቲቱን፣ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።

ሉቃስ 7:36-50 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች። የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ፦ ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ። ኢየሱስም መልሶ፦ ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው። እርሱም፦ መምህር ሆይ፥ ተናገር አለ። ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ። የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው? ስምዖንም መልሶ፦ ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል አለ። እርሱም፦ በእውነት ፈረድህ አለው። ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች። አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል። እርስዋንም፦ ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት። ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው፦ ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው? ይሉ ጀመር። ሴቲቱንም፦ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።

ሉቃስ 7:36-50 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከፈሪሳውያን አንዱ ኢየሱስን ምሳ ጋበዘው፤ ኢየሱስም ወደ ፈሪሳዊው ቤት ገብቶ ምሳ ለመብላት ወደ ማእድ ቀረበ። በዚያች ከተማ አንዲት ኃጢአተኛ ሴት ነበረች፤ እርስዋም ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት ምሳ መጋበዙን በሰማች ጊዜ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ መጣች። ከኢየሱስ በስተኋላ በእግሮቹ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች እግሮቹን በእንባዋ ታርስና በጠጒርዋ ታብስ ነበር፤ እግሮቹን እየሳመች ሽቶ ትቀባቸው ነበር። ምሳ የጋበዘው ፈሪሳዊ ይህን ባየ ጊዜ፥ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነችና ምን ዐይነት ኃጢአተኛ እንደ ሆነች ባወቀ ነበር፤” ሲል በልቡ አሰበ። ኢየሱስም፦ “ስምዖን ሆይ፥ አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ፤” አለው። እርሱም፦ “መምህር ሆይ! እሺ ንገረኝ!” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል ንግግሩን ቀጠለ፤ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንዱ አምስት መቶ ዲናር ሌላው ደግሞ ኀምሳ ዲናር ተበደሩ፤ ሁለቱም የተበደሩትን መክፈል ቢያቅታቸው አበዳሪው ዕዳቸውን ተወላቸው፤ ታዲያ፥ ከሁለቱ ባለዕዳዎች፥ አበዳሪውን አብልጦ የሚወድ የትኛው ይመስልሃል?” አለው። ስምዖንም፦ “ብዙ ዕዳ የቀረለት ሰው አብልጦ የሚወደው ይመስለኛል፤” ሲል መለሰ። ኢየሱስም “መልስህ ልክ ነው፤” አለው። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ሴትዮዋ መለስ ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ስገባ አንተ ውሃ እንኳ ለእግሬ አላቀረብክልኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን በእንባዋ አጥባ በጠጒርዋ አበሰችው። አንተ ስትቀበለኝ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን እኔ ወደ ቤትህ ከገባሁ ጀምሮ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም፤ አንተ ራሴን ዘይት እንኳ አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሮቼን ሽቶ ቀባች፤ ስለዚህ ብዙ ስለ ወደደች ብዙ ኃጢአትዋ ይቅር ተብሎላታል እልሃለሁ፤ ኃጢአቱ በጥቂት ይቅር የሚባልለት ግን የሚወደውም በጥቂቱ ነው።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሴትዮዋን፥ “ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል፤” አላት። ከእርሱ ጋር በማእድ ይበሉ የነበሩትም “ኃጢአትን እንኳ ይቅር የሚል ይህ ማነው?” እያሉ በልባቸው ያስቡ ጀመር። ኢየሱስ ግን ሴትዮዋን፥ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ!” አላት።

ሉቃስ 7:36-50 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከፈ​ሪ​ሳ​ው​ያ​ንም አንዱ በእ​ርሱ ዘንድ ምሳ እን​ዲ​በላ ለመ​ነው፤ ወደ ፈሪ​ሳ​ዊ​ውም ቤት ገብቶ በማ​ዕድ ተቀ​መጠ። እነሆ፥ ከዚ​ያች ከተማ ሰዎ​ችም አን​ዲት ኀጢ​አ​ተኛ ሴት በፈ​ሪ​ሳ​ዊው ቤት በማ​ዕድ እን​ደ​ተ​ቀ​መጠ ዐውቃ ሽቱ የሞ​ላ​በት የአ​ል​ባ​ስ​ጥ​ሮስ ቢል​ቃጥ ገዝታ መጣች። በስ​ተ​ኋ​ላ​ውም በእ​ግ​ሮቹ አጠ​ገብ ቆማ አለ​ቀ​ሰች፤ እግ​ሮ​ቹ​ንም በእ​ን​ባዋ ታርስ ነበር፥ በራስ ጠጕ​ር​ዋም እግ​ሮ​ቹን ታብ​ሰ​ውና ትስ​መው፥ ሽቱም ትቀ​ባው ነበር። የጠ​ራው ፈሪ​ሳ​ዊም ባየ ጊዜ በልቡ ዐሰበ፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “ይህስ ነቢይ ቢሆን ኖሮ ይህቺ የም​ት​ዳ​ስ​ሰው ሴት ማን እንደ ሆነች፥ እን​ዴ​ትስ እንደ ነበ​ረች ባላ​ወ​ቀም ነበ​ርን? ኀጢ​አ​ተኛ ናትና።” ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ስም​ዖን ሆይ፥ የም​ነ​ግ​ርህ ነገር አለኝ” አለው፤ እር​ሱም፥ “መም​ህር ሆይ፥ ተና​ገር” አለው። እር​ሱም እን​ዲህ አለው፥ “ለአ​ንድ አበ​ዳሪ ሁለት ባለ ዕዳ​ዎች ነበ​ሩት፤ በአ​ንዱ አም​ስት መቶ ዲናር ነበ​ረ​በት፤ በሁ​ለ​ተ​ኛ​ውም አምሳ። የሚ​ከ​ፍ​ሉ​ትም ባጡ ጊዜ ለሁ​ለ​ቱም ተወ​ላ​ቸው፤ እን​ግ​ዲህ ከሁ​ለቱ አብ​ልጦ ሊወ​ደው የሚ​ገ​ባው ማን​ኛው ነው?” ስም​ዖ​ንም መልሶ፥ “ብዙ​ውን የተ​ወ​ለት ነው እላ​ለሁ” አለው፤ እር​ሱም፥ “መል​ካም ፈረ​ድህ” አለው። ወደ ሴቲ​ቱም ዘወር ብሎ ስም​ዖ​ንን እን​ዲህ አለው፥ “ይህ​ቺን ሴት ታያ​ታ​ለ​ህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ለእ​ግ​ሮች ውኃ ስንኳ አል​ሰ​ጠ​ኸ​ኝም፤ እር​ስዋ ግን አል​ቅሳ በእ​ን​ባዋ እግ​ሬን አራ​ሰች፤ በጠ​ጕ​ር​ዋም አበ​ሰች። አን​ተስ ሰላ​ምታ አል​ሰ​ጠ​ኸ​ኝም፤ እር​ስዋ ግን ከገ​ባሁ ጀምሮ እግ​ሬን ከመ​ሳም አላ​ቋ​ረ​ጠ​ችም። አንተ ራሴን እንኳ ዘይት አል​ቀ​ባ​ኸ​ኝም፤ እር​ስዋ ግን እግ​ሬን ሽቱ ቀባ​ችኝ። ስለ​ዚ​ህም እል​ሃ​ለሁ፤ ብዙ ኀጢ​ኣቷ ተሰ​ር​ዮ​ላ​ታል፤ በብዙ ወድ​ዳ​ለ​ችና፤ ጥቂት የሚ​ወ​ድድ ጥቂት ይሰ​ረ​ይ​ለ​ታል፤ ብዙ የሚ​ወ​ድ​ድም ብዙ ይሰ​ረ​ይ​ለ​ታል።” ሴቲ​ቱ​ንም፥ “ኀጢ​ኣ​ትሽ ተሰ​ረ​የ​ልሽ” አላት። በማ​ዕዱ የተ​ቀ​መ​ጡ​ትም እርስ በር​ሳ​ቸው፥ “ኀጢ​አ​ትን የሚ​ያ​ስ​ተ​ሰ​ርይ ይህ ማነው?” ይሉ ጀመር። ሴቲ​ቱ​ንም አላት፥ “እም​ነ​ትሽ አድ​ኖ​ሻል፤ በሰ​ላም ሂጂ።”

ሉቃስ 7:36-50 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከፈሪሳውያንም አንዱ ኢየሱስን ከእርሱ ጋር እንዲበላ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። እነሆም፥ በዚያች ከተማ ኀጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፥ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቶ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብልቃጥ አምጥታ ነበር። በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ፥ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፤ በራስ ጠጉርዋም ታብሰው፥ እግሩንም ትስመው፥ ሽቶም ትቀባው ነበረች። የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ፦ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች፥ እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና፤” ሲል በልቡ አሰበ። ኢየሱስም መልሶ፦ “ስምዖን ሆይ! አንድ የምነግርህ ነገር አለኝ፤” አለው። እርሱም፦ “መምህር ሆይ! ተናገር፤” አለ። “አንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት፤ አንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት፤ ሌላው ደግሞ አምሳ። የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ዕዳቸውን ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው?” ስምዖንም ሲመልስ፦ “ብዙ የተወለትን ይመስለኛል፤” አለ። እርሱም፦ “በትክክል ፈረድህ፤” አለው። ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፦ “ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ ውሃ እንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርሷ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጉርዋም አበሰች። አንተ አልሳምኸኝም፤ እርሷ ግን ከገባሁ ጊዜ ጀምሮ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርሷ ግን እግሬን ሽቶ ቀባች። ስለዚህም እጅግ ወዳለችና ብዙ ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል እልሃለሁ፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል።” እርሷንም፦ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል፤” አላት። ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው፦ “ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው?” ይሉ ጀመር። ሴቲቱንም፦ “እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤” አላት።